>

የምዕራባዊያን ውትወታ፤ ከህውሃት ጋር ተደራደሩ - የሞኝ ፈሊጥ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የምዕራባዊያን ውትወታ፤ ከህውሃት ጋር ተደራደሩ – የሞኝ ፈሊጥ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ህውሃት በከፍተኛ እና በአለም አቀፍ የሰቆቃ (atrocity) ወንጀሎች መጠየቅ ካለባቸው እኩይ ቡድኖች አንዱ ነው። ለረዥም ዓመታት ህውታት ከነተባባሪዎቹ የፈጸሟቸው የመብት ጥሰቶች በአግባቡ ተሰንደዋል። የተጠያቂነት ባህል በአገር ደረጃ ማስፈን ባለመቻሉ ነው እንጂ ህውሃት ድሮ ነበር እንደ ድርጅትም፤ አመራሮቹም እንደ ግለሰብ ለፍርድ መቅረብ የነበረባቸው። ይህን ክፍተት በመጠቀምም ህውሃት ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥም እጅግ ዘግናኝ የሆኑ የመብት ጥሰቶች ሲፈጽም እና የሚፈጽሙ አካላትንም በይፋ ሲደግፍ ቆይቷል። በተለይም የትግራይን ሕዝብ አሁን ላለበት አስከፊ ስቃይ መዳረጉ ህውሃትን በሕግ እንዲፈርስ እና በሕይወት የተረፉትንም አመራሮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያስደርግ ሁኔታ ከበቂ በላይ ተሟልቷል።
ምዕራባዊያን በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት እና ሰቆቃ የሚያሳዩት ተቆርቋሪነት ከመስመር አልፎ ህውሃትን ለድርድር እንዲመጣ የመጣር አዝማሚያ ማሳየታቸው በምንም መስፈርት ቢሆን አግባብነት ያለው አይደለም። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መዳፈሩ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃም ወንጀልን እና ህውሃት መሰል ወንጀለኛ ድርጅቶችንም የሚያበረታታ አጉል አድራጎት ነው። እንደ ህውሃት ያሉ በንጹሐን ደም የጨቀዩ ድርጅቶችንም ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ በር ይከፍታል። ህውሃትን የኢትዮጵያ መንግስት ብቻ ሳይሆን የአለም አቀፍ ማህበረሰቡም ጭምር ተጠያዊ ሊያደርገው የሚገባ ቡድን ነው።
ለበርካታ አመታትም የታገልነው ይህ ቡድን ከነአባሪዎቹ በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን ነበር። የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለማስተካከል፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ የመብት ጥሰቶችን ለማስቆም እና በመብት ጥሰት የተሳተፉ አካላትን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት፣ ግፊት እና ውትወታ አግባብነት ያለው ነው። ከዛ ባለፈ ህውሃት ነፍስ እንዲዘራ የሚደረገው ጥረት ግን በህውሃት የወንጀል አድራጎት ባለቁ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ህይወት መቀለድ ነው። ህውሃት እንደ ድርጅት መፍረስ፤ አመራሮቹ ደግሞ እንደ የኃላፊነት ደረጃቸው ለፍርድ መቅረብ ነው ያለባቸው።
Filed in: Amharic