>

ምጧ የበዛባት ሀገር  - ኢትዮጵያ!  (ኤልያስ ደግነት)

ምጧ የበዛባት ሀገር  – ኢትዮጵያ!

ኤልያስ ደግነት

አሜሪካ እጅ ጥምዘዛዋን ጀመረች!

ኢትዮጵያ ምጧ እንደረዘመ ጣሯ እንደበዛ  ድርስ  ሴት ሁናለች፡፡መንታ ልጆች አርግዛለች፡፡ አንደኛው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ደግሞ 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ፡፡ ከወሊዷ በኃላ እንዴት ሆና ትቀጥል ይሆን ..የሚለው ጥያቄ አሳሳቢ ነው፡፡ በእርግጥ ድህረ ምርጫ በየትኞቹም የአፍሪካ ሀገራት ላይ ጓ ገጭ ሳይል አልፎ አያውቅም፡፡ ምርጫውን ጊዜዋን ጠብቃ በምጥ እንደምትወልድ ሴት ጌዜዬን ጠብቄ ነው የምወልደው ብትልም ያልበላቸውን የሚያኩቱ የአውሮፓና የአሜሪካ አሀገራት ሰዎች በቀዶ ጥገና እናዋልድሽ …እኛ ያላዋለድነው አያድም አይነት ጨዋታ ይዘዋል፡፡ እልፍ ሲልም በአገም ጠቀም የተሳሰረ ወዳጅነታቸው በአንድ ነጠላ ካላስቀደስን እያሰኛቸው  በዓባይ ጉዳይ  ከግብፅ ወግነው በቀጭን ትዕዛዝ እንዲህ አድርጉ እንዲያ እናዳታደርጉ በሚል ፈልጭ ቆራጭ ሊሆኑ ሲዳዳቸው አይተናልም ሰምተናልም፡፡ከዚህ እልፍ ሲልም ማዕቀብ ሊያስጥሉብን ችግራችን ላይ ሊሳለቁብን ያልጣሉብን ደንቃራ ….ያልሰቀሉብን ኮረሪማ የለም፡፡ ኢትዮጵያ የሰው አልነካም የኔንም አላስነካም ባለች ሀያላኑ በተለይም አሜሪካውያኑ ኢትዮጵያን ማዕከል ባደረገ ጉዳይ ብቻ  በዝግ መክረው የአሜሪካ ሴኔትና የምዕራባዊያኑ ተመሳሳይ ጥምረት ታክሎበት ይችን የድሃ ቀብራራ ሀገር እንደምን እናፍርሳት ከሚል ሞኣጢሳዊ  አስተሳሰበ ተነስታ የፈለገችውን ዓይነት ጫና ለመፍጠር የሚያስችላትን ሪሾሉሽን 97 የተሰኘ ሕግ አፅድቃለች፡፡
እንግዲህ በዚህም እጅ የመጠምዘዙን ነገር ሀ ብላ መጀመሯ ነው ማየት የምንችለው፡፡ ሕዝቤ አሁን ነቅቶ በአንድ ካልቆመ አደጋው ከባድ ነው፡፡ ሀገር እንዲህ ምጧ በዝቶ ሳለ ደም በለመደ እጃቸው ቀደን አዋልደን እንጠግናለን የሚሉ ሀገራት እሷንም ፅንሷንም ሊያጨናግፉ ሾተላቸውን መዘዋልና ልባችንን ከአንደበታችን አሰናስነን NO አይሆንም…..”Hands off Ethiopia” እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ ልንል ይገባናል!!! ዛሬ በአንድ መቆም ግድ ነው! የነገ ብርሃናችንን ሊቀሙን ….የኩሌታ መብታችንን ሊነፍጉን …ለእጅ አዙር ቅኝ ግዥነት እንቢኝ ማለታችንን ሊሰልቡብን ተነስተዋል እና ጎበዝ በአንድ ልንቆም ይገባናል፡፡ ዘር በሉት ኃይማኖት …ፀብ በሉት ፍቅር ሁሉ የሚያምረው በእናት ጓዳ ነው! 
ኢትዮጵያ ትቅደም  እስከ ዘለዓለም!! 
Filed in: Amharic