(አቶ ክርስቲያን ታደለ፦ የአብን ፖ/ጉዳዮች ኃላፊ)
አቶ ክርስቲያን ታደለ ኮከብ ሆኖ ባመሸት የፋና ቴቪ የክርክር መድረክ አብን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ መግዛት የሚችል ሀቀኛ ፓርቲ መሆኑን አስመስክሯል። በመድረኩ ካነሳቸው ዋና ዋና ሀሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
1ኛ. በኢትዮጵያ ያሉ መገፋፋቶች መነሻቸው በህገ መንግስቱ ያለ የተሳሳተ ትርክት ነው ብለን እናምናለን። የህዝብን አንድነት ለማጠናከር ይህን የተሳሳተ ትርክት በውይይት በማረም በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ህብረት መፍጠር ይገባል ብለን እናምናለን።
2ኛ. ተቋማትን ከፓርቲና ከመንግስት መዋቅር ውጪ ራሳቸውን ችለው መቆም የሚችሉ እንዲሆኑ በማድረግ ነፃ እናደርጋቸዋለን።
3ኛ. መነሻችን የአማራ ህዝብ እንደመሆኑ ስለ አማራ ህዝብ በደል ሳንታክት ሞግተናል፤ ብልፅግና ግን የህዝቡን ደህንነት ባለማስጠበቁ ማፈር ሲገባው አብን ለአማራ ህዝብ ድምፅ የሆነባቸውን መግለጫዎች ለመተቸት ይቸኩላልአሳውቀናል።
4ኛ. ብልፅግና “ግጭቶችን ስልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት ትጠቀማላችሁ” ይለናል፤ መንግስት እንደ መንግስት ተቀዳሚ ስራው የህዝብን ደህንነት መጠበቅ መሆን ሲገባው የእኛን መግለጫ መተቸት ሆኗል፤ ብልፅግና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ቢችል እኛ ስልጣኑ ቢቀርብን እንመርጣለን።
5ኛ. ብልፅግና በአማራ ህዝብ ላይ ከሚደርሰው በደል ይልቅ “ሞቱን የሚያወግዝ ህዝብ ፕሬዝዳንታችንን ተቃወመብን” ብሎ የሚያኮርፍ ፓርቲ ነው፤ ወይ “የአማራ ህዝብ ጉዳይ አይመለከተንም” የምትሉ ከሆነ ንገሩን፤ ህዝባችን በራሱ ለራሱ መሆን አያቅተውም።
6ኛ. ብልፅግና የአማራን ህዝብ ደህንነት ማስጠበቅ ባይችል፤ ሌላው ቢቀር ለጠፋው ነፍስ ማዘን የሚችል ልብ ቢያጣ እንዴት አስከሬን እንኳን ባግባቡ መቅበር ያቅተዋል?! በጅምላ በግሬደር ሰብስቦ የቀበረ ፓርቲ ነው ብልፅግና። ይህ ሊያሳስበው የሚገባው አብንን ብቻ መሆን አልነበረበትም። የአማራ ህዝብ መገፋት የሚያሳስበው ቢኖር ኖሮ ብልፅግናን ጨምሮ ሁላችንም ልንታገልለት ይገባ ነበር።
7ኛ. አብን የጋሞ ወገኖቻችን በቡራዩ ጥቃት ሲደርስባቸው ከማንኛውም ፓርቲና መንግስታዊ አካል በፊት ድምፅ የሆነ ፓርቲ ነው፤ ጋሞዎች አማራ ስለሆኑ አይደለም።
8ኛ. የጌዲዖ ህዝብ በደል በብልፅግና ሴራ ታፍኖ በረሃብ ሲቀጣ ከማንም ቀድሞ በመግለጫ ያወገዘና ድጋፍ አሰባስቦ የላከው አብን ነው፤ ጌዲዖ አማራ ስለሆነ ግን አይደለም።
9ኛ. የአዲስ አበባ ወጣቶች ያላግባብ እየተጋዙ ሲታሰሩ ቀድሞ ያወገዘው አብን ነው፤ ይህንንም ተከትሎ ፖሊስ ጣቢያዎች ወጣቶቹን በማግስቱ እንዲለቁ አድርጓል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው አብን መነሻውን የአማራ ህዝብ ያድርግ እንጂ ሀገር አቀፍ እሳቤን ይዞ የሚታገል መሆኑን ነው።
10ኛ. አሁን እየታዩ ያሉ መፈናቀሎችና ጅምላ ግድያዎች በብልፅግና ድክመት ሳቢያ የሚከሰቱ ብቻ ሳይሆኑ የብልፅግና አመራሮች ሳይቀሩ የሚሳተፉባቸው ናቸው፤ የአፋርና ሶሜሌ ድንበር ላይ ያለውን ግጭት ማንሳት እንችላለን፤ የ “ሰበርናቸውን” ትርክት ማንሳት እንችላለን፤ ራሱ ብልፅግናም “ከ 1200 በላይ አመራሮችን አስረናል” ብሎ ያመነበት ነው።
11ኛ. በአብን እምነት በልዩ ሃይሎች መካከል የሚፈጠሩ መካረሮችና ግጭቶች መነሻቸው የተሳሳተ ትርክት ነው ብለን እናምናለን። የተሳሳቱ ትርክቶችን በታሪክ ባለሙያዎች አርመን ፖለቲካዊ መቀራረብ ስንፈጥር መካረሮች ይረግባሉ ብለን እናምናለን።
12ኛ. ትህነግን ከዛሬ ሁለት አመት በፊት “በሽብርተኝነት ይፈረጅ” ብለን ስንጠይቅ የብልፅግና አመራሮች “ትህነግን በሽብርተኝነት ይፈረጅ አላችሁ” ብለው ለሰላምታ እንኳን ይሽቆጠቆጡ ነበር። ህግ በማስከበር በኩል በስተቀሮችን አናስቀምጥም።
13ኛ. እኛ መንግስት ብንሆን ሌሎችን የሚቆጣጠሩ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን እኛን ጭምር ተጠያቂ ማድረግ የሚችሉ ተቋማትን እንፈጥራለን፤ ወንጀለኛ ባጠፋው ወንጀል ልክ እንዲጠየቅ ማድረግ የሚችል መዋቅር እንፈጥራለን እንጂ እንደ ብልፅግና በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ የሚገባውን ግለሰብ አሳድገን ሹመት አንሰጥም።
14ኛ. ብልፅግና ሀሳብ እንዳለው ፓርቲ እኛን “ሀሳብ የላችሁም” ይለናል። እኛ ግን ግጭቶች እንደ አሁኑ ከመባባሳቸው በፊት የተሳሳቱ ትርክቶች የሚስተካከሉበትንና እንደ አማራጭ የሚያገለግሉ ህገ መንግስታዊ አማራጮችን ጭምር በገፃችንም ቤተ መንግስት ድረስ ተገኝተን አሳውቀናል።
15ኛ. እኛ ያዘጋጀነው የህገ መንግስት አማራጭ ብቻ ጥቅም ላይ ይዋል አንልም፤ ነገር ግን የሚመለከተው ሁሉ አማራጩን ይዞ እንዲቀርብ እና ተወያይተንበት ስምምነት ላይ የተደረሰበት ህገ መንግስት ይኑረን ነው የምንለው።
16ኛ. “የተሳሳተ ትርክት የለም” ብሎ ለአማራ ህዝብ በደል መነሻ የሆነውን ሀሳብ የሚቀበለው ብልፅግና ለቀጣይ አመታት በስልጣን ላይ እንዲቆይ አንፈቅድም። የብልፅግና ፓርቲ የቀጣይ አመቶች ያለፉት ሶስት አመታት ነፀብራቆች ናቸው፤ ምንም አዲስ ነገር የለውም፤ የተጨባጩን ዛሬን ማስተካከል ያልቻለ ነገን አሳምራለሁ ብሎ ሊያታልለን አይችልም።
17ኛ. ስለሆነም መላው ህዝባችን በመግባባት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖረን፤ ሀገርን ከመፍረስና ህዝብን ከመፍለስ እንድናድን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን (አብንን) ምረጡ፤ አብንን መምረጥ ኢትዮጵያን መምረጥ ነው፤ ምልክታችን ሰዓትን ነው፤ ሰዓትን ምረጡ።
አመሰግናለሁ!”
[ክርስቲያን ታደለ፦ በፋና ቴቪ]