>

ኢትዮ-ቴሌኮም ሙሉ በሙሉ ተሸጠ!

ኢትዮ-ቴሌኮም ሙሉ በሙሉ ተሸጠ!

አሰፋ ሀይሉ


በሀገር ሻጩ በወያኔ ዘመን እንኳ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ሀብት ሆኖ የቆየውን ቴሌን ኦሮሙማው የአብይ አህመድ መንግሥት እፍኝ የማይሞሉ ተጫራቾችን አወዳድሮ ባለቤትነቱን ሙሉ በሙሉ ለመልታይናሽናል ካምፓኒዎች እንደሸጠው የዛሬው ፋይናንሺያል ታይምስ ዘገባ ይፋ አውጥቶታል፡፡ አብይ አህመድና ግብረ አበሮቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይፈቅድና፣ በህዝብ ሳይመረጡ፣ በየትኛው ሥልጣናቸው እነዚህን ግዙፍ የህዝብና የመንግሥት ሀብቶች ለውጪ መልታይናሽናል ካምፓኒዎች እንደሚቸረችሩት ምንም የሚታወቀው ነገር የለም፡፡
በሽያጩ መሰረት እስከዛሬ መንግሥት በሞኖፖል ይዞት የቆየውን የኢትዮ ቴሌኮም በኬንያ ለሚንቀሳቀሰው ሳፋሪኮም 62 በመቶውን የባለቤትነት ድርሻ፣ በደቡብ አፍሪካ ለሚንቀሳቀሰው ቮዳፎን 6 በመቶውን ድርሻ፣ ለጃፓኖቹ መልታይናሽናል ለሱሚቶሞ ኩባንያ 25 በመቶውን እንዲሁም የእንግሊዝ መንግሥት መልታይናሽናል ኩባንያ ለሆነው ሲዲሲ የ10 በመቶ ድርሻ በመሸጥ ቴሌን ከኢትዮጵያ ህዝብ ሀብትነት ከሀገር ሀገር ትርፍ እያሳደዱ ለሚሰሩ የውጪ ሀገራት አትራፊ ድርጅቶች ቸብችቦታል፡፡
ይህ ሽያጭ ተረኛ ገዢነቱን ለማረጋገጥ ሀገርንም ህዝብንም ከመሸጥ ወደ ኋላ በማይለው የአብይ አህመድ ኦሮሙማዊ መንግሥት በሀያላኑ ሀገራት ፊት፣ የመንግሥትን ድርጅቶች ወደ ውጪ የግል ባለሀብቶች በማዞር ቁርጠኛ የካፒታሊስት የነጻ ገበያ ሥርዓት አራማጅ የሚል ስም እንዲያሰጠውና፣ የፈለገውን ያህል ሰብዓዊ መብት ረገጣና ጅምላ ጭፍጨፋ በሀገሪቱ ላይ ቢያካሂድ፣ ጥቅማቸውን እስካስከበረላቸው ድረስ ተላላኪነቱን ተቀብለው የሥልጣኑ ተባባሪ እንዲሆኑ የታለመ፣ የመጨረሻው ድፍረት የተሞላበት ድርጊት እንደሆነ በቀላሉ ማወቅ አያዳግትም፡፡
የአብይ አህመድ መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ከ4 ቀናት በኋላ ከአሸናፊዎቹ ጋር ውል እንደሚዋዋል ያሳወቀ ሲሆን፣ የቴሌን ባለቤትነት ሼር የተቀራመቱት ገዢዎች በበኩላቸው አንድ በጋራ ተጣምሮ የሚሰራ የሽርክና ኮንሶርቲየም መመሥረታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ስለሆነም፣ ልክ ከአብይ አህመድ ጋር የቴሌን ግዢ ውል እንደተዋዋሉ፣ የአሜሪካ የዓለም ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይዲኤፍ) ከ500 ሚሊየን እስከ 1 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ በረዥም ጊዜ ተከፍሎ የሚያልቅ (እስከ 25 ዓመት) ብድር ሊለቅላቸው ተስማምቷል፡፡ እንግዲህ ድርጅቶቹ የቴሌን መሠረተ ልማት ተረክበው፣ በአሜሪካ ብድር፣ በኢትዮጵያ 117 ሚሊየን ህዝብ (ግማሹን እንኳ ሞባይል ተጠቃሚ ቢያደርጉት) የአየር በአየር የቴሌ ሽቀላቸውን ያጧጡፉታል ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ለውጥ አሸጋግራለሁ ያለው አብይ አህመድ ኢትዮጵያን በተረኛ የኦሮሙማ ጥፍሮች ፈጥርቆ ይዞ፣ ከአጫፋሪዎቹ ጋር ሀገሪቱን በሌላ ሀገር በኤርትራ አስወርሮ፣ በሱዳን አስወርሮ፣ ሀገሪቱንና ህዝቡን ጦርነት እሳት ውስጥ ጨምሮ፣ በየዕለቱ የአማራውን ሕዝብ በየሰፈረበት ሀገርና ቀዬ እያረደና እያፈናቀለ፣ የሀገርንና የህዝብን ሀብት ያለከልካይ እየቸበቸበ፣ አዲስ ገንዘብ እያተመ፣ ያሻውን እየፈለጠ እየቆረጠ ያለምንም ከልካይና ጠያቂ ተረጋግቶ መጓዙን ቀጥሏል፡፡
በዓለም (ሌላ ቀርቶ በአፍሪካችን) ታሪክ ሀገሪቱን የአራጅ ሚሊሻዎች መፈንጫ አድርጎ፣ ሉዓላዊነቷን አስደፍሮ፣ ያሻውን የሀገሬውን ሀብትና ንብረት ለውጪ ግዙፍ ነጋዴ ኩባንያዎች እየቸበቸበ፣ አዳዲስ ገንዘብ እያተመ፣ ከሀገሬው ህዝብ ምንም ተቃውሞ ሳይቀርብበት፣ በህዝብም ሳይመረጥ፣ የሰብዓዊና መንግሥታዊ ተቋማትን ሁሉ በእጁ አስገብቶ የይስሙላ ታዛዥ መጫወቻው አድርጓቸው ሲያበቃ፣ ሰጥ ለጥ አድርጎ ከመቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ለመግዛት የተሳካለት ሀይል ቢኖር – በአብይ አህመድ የሚመራው ይኸው የጊዜያችን የኦሮሙማ ሀይል ነው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ በኋላ ሀገሪቱ ራሷ ዋጋ ካወጣች ብትሸጥ ቀና ብሎ ለመጠየቅና መብቱን ለማስከበር ምንም ዓይነት ርዝራዥ ሀሳብ ያለውም አይመስልም፡፡ ለሀገሩና ለሉዓላዊነቱ፣ ለመብቱና ለህዝቡ ሲል የገዛ ጎጆውን ጥሎ ለሀገሩ ሟች በመሆን የሚታወቀው ያላለፈለት የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እንዴት እንዲህ በሀገሩ ተስፋ እንደቆረጠና፣ እንዴት እንዲህ ወደ ገደል ይወሰድ፣ ለባርነት ተላልፎ ይሰጥ፣ ሀብቱ ይመዝበር፣ ማንም ይግዛው፣ ማንም ይውረረው፣… እንዴት እንዲህ አጎንብሶ በዝምታ ወደ ሀገራዊ ሞቱ መጓዝን የሙጥኝ እንዳለ፣ ብዙዎችን የሀገራችንን ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ የሚሄድ ሁኔታ የሚከታተሉ የውጪ ታዛቢዎችን ሳይቀር እጅግ የገረመና ግራ ያጋባ የ21ኛው ክፍለዘመን እንግዳ ክስተት ሆኗል፡፡
ገና አገልግሎት መስጠት ያልጀመረውን የአባይ ወንዝ ግድብ (ህሳሴውን) የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ሼር ከአሁኑ የሚገዛኝ ካለ እደራደራለሁ ብሎ ለጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት ድምጽ አልባ ጨረታ ያወጣው የአብይ አህመድ መንግሥት – ሁሉን ነገር ሸጦ – መጨረሻ ላይ ህዝቡንና መንግሥቱን ምን አድርጎ ሊያስተዳድረው እንደሆነ ፍጹም ግራ አጋቢ ነገር ሆኗል በእውነት፡፡ ፈጣሪ አለሁ ይበለን እንጂ የእኛ ነገር ከድጡ ወደ ማጡ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ የህዝባችንን ሞራል ወደ ዜሮ ተቋቋሚነት ደረጃ እንዴት ማውረድ እንደተሳካላቸው አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
ዛሬ ቴሌ ያለ ኢትዮጵያ ህዝብ ፈቃድ በላያችን ላይ ተሸጧል፡፡ ትናንት 70ሺህ ህዝብ ያለቀበት ባድሜ ሽራሮ ያለ ኢትዮጵያ ህዝብ እውቅናና ይሁንታ ለኤርትራ ተሰጥቷል፡፡ ዛሬ ዓይናችን እያየ ሀገር ሉዓላዊ ሀገር መሆኗ ቀርቶ በስም ብቻ ያለች በዓለም አበዳሪዎች ሀይል የምትንቀሳቀስ ህግና መንግሥት የሌለባት ዜጋ እንደ ጉድ በቀን ጠራራ ፀሐይ የሚታረድባት ዳግማዊ ሶማሊያን ልትሆን እየዳዳት ያለች ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያችን፡፡ ይህ የማይቆጨውና የማያስቆጣው ህዝብ ምን እንደሚያስብ በበኩሌ አይገባኝም፡፡
ፈጣሪ ልቦናውንና እንዲህ በዝምታችን የቆለልነውንና ኋላ በላያችን ላይ የሚመጣብንን የጋራ መከራ ለመቀበል ብርታቱን ይስጠን ማለት ነው፡፡ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፡፡ እውነት ከመደጋገሙ የተነሳ የተለመደ ማላዘን ይመስላል፡፡ በምን ቃል ቢነገረው ኦሮሙማው ህዝባችንን ወደየት እየመራው እንዳለ እንደሚገለጽለት አይገባንም፡፡ ፈጣሪ ያዘጋጀልን የራሱ መንገድ ይኖራል እንግዲህ፡፡ ፈጣሪ እውነቱን ይግለጽልን፡፡ ፈጣሪ አለኋችሁ ይበለን፡፡ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን፣ እና ኢትዮጵያውያንን ይህን ክፉ ጊዜ በኪነጥበቡ ያሻግረን! 
Filed in: Amharic