>

አንድነት ይበጀናል ዛሬ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


እንደ መንደርደሪያ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ ኢትዮጵያ የተረጋጋች ሀገር እንድትሆን፣ሰላሟ የተጠበቀ እና የምጣኔ ሀብት እድገቷ አስተማማኝ እንዲሆን ከተፈለገ አንድነቷ የተጠበቀ መሆን እንዳለበት ማሳሰብ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የአንድነት መላላት እና ለመለያየት የሚያዘንብሉ አስተያየቶችና ገቢራዊ እንቅስቃሴዎች አይምሮን የሚረብሹ ወይም እረፍት የሚያሳጡ ብቻ አይደሉም፡፡ ምናልባትም ኢትዮጵያን ከከሸፉ ሀገራት ተርታ ሊያሰልፋት የሚያስችል ነው፡፡ ስለሆነም ሁለቱንም ነጥቦች መመርመር እጅጉን አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ( የአንድነትን ጥቅምና የመለያየትን ጉዳት ማለቴ ነው፡፡) ለምንድን ነው ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀች ሀገር እንድትሆን የሚፈለገው ? የኢትዮጵያን አንድነት በአጭር ግዜ እና በረጅም ግዜ ውስጥ ለመጠበቅ ሁነኛ መፍትሔው ምን ይሆን ?

የኢትዮጵያ አንድነት ለምን ? ( አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር ለምን ? )

ጀርመን ከአውሮፓ ሀገራት ሁሉ በኢንዱስትሪ የእድገት ደረጃ ግንባር ቀደም መሆን የጀመረችው ምስራቅ ጀርመንና ምእራብ ጀርመን በሰለጠነ መንገድ ከተዋሃዱ በኋላ ነው፡፡ የአንድነትን ጥቅም የተረዱት የካቶሊኒያን የመገንጠል ጥያቄ በሰከነ መንፈስ ለመመለስና የአንድነትን ጥቅም ለማስረዳት የሄዱበት መንገድ ርቀት አለው፡፡ እጅግ የበለጸገችውና ሀብታሟ ስኮትላንድ በታላቋ ብሪታኒያ የግዛት አንድነት ስር መሆኗ እንደሚጠቅማት ካወቀች ሰነበተች፡፡ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ በሀብትና እውቀት ፊትአውራሪ በሆነችው ካናዳ የምትገኘው የኩቤክ ተገንጣይ ሀይሎችን በጥበብ ስለያዘቻቸው አንድነቷ አልተናጋም፡፡ የሩሲያ ወደ ቀድሞው ሃያልነቷ ለመመለስ ስትል በዙሪያ ያሉ አንዳንድ ሀገራትን የተለያዩ ዘዴዎችን ገቢራ ለማድረግ የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው የ3000 አመታት ታሪክ ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞው አንድነቷ መመለስ ያቃታት ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ለማጥበቅ ለምን መንፈሳዊ ወኔ ከዳቸው ግራም ነፈሰ ቀን አንድነት ለኢትዮጵያውያን የቀንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በአለም ላይ በድህነት ስማቸው ከሚነሱ ዋና ዋና የሆነችው ሀገር ኢትዮጵያ የሚያዋጣት አንድነቷ ብቻ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት እውን ማድረግ የሚቻለው ግን በግድ በጡንቻና በብረት ሀይል አይደለም፡፡ ይህ በፍጹም የሚሳካ አይደለም፡፡ ብዙ ግዜ ተሞክሮ አይተነዋል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻነት ሳይገፈፍ በእውነት መሰረት ላይ ስለ አንድነት ጥቅምና ስለ መለያየት ጠንቅ በተለያዩ ዘዴዎችና የመገናኛ አውታሮች ማስተማር ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ ፡፡ ውጤቱን በተመለከተ የሚጥመውን ለሚያውቀው ህዝብ ውሳኔውን መተው ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የኢትዮጵያ አንድነት መከበር አለበት በማለት የተነሳሁት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡ በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘርዘር ቢቻልም ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶቼን ለአንባቢው አቀርባለሁ፡፡

1.የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ አለበት ፡፡ወይም ኢትዮጵያ አንደነቷ የተጠበቀና የታፈረች ሀገር መሆን አለባት ተብሎ ሲጻፍ ወይም ሲነገር ለላንቲካ አይደለም( ወሬ ለማሳመር አይደለም) ኢትዮጵያ አንድ ሀገርና አንደነቷ የተጠበቀ መሆነረ ያለባት የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት አብሮ የኖረ በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ ታሪክ ፍንትው አድርጎ እንደሚስተምረን የኢትዮጵያ ህዝብ በማህበራዊ ኑሮ፣ በመልክአምድራዊ አቀማመጥ ለዘመናት የሚገናኝ ነው፡፡ ተገንጣይ ሀይሎች ወይም አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ከሚያስቡት( ለተከታዮቻቸው ከሚሰብኩት ) በተቃራኒው እውነት እንደምትነግረን ከመለያየት(ከጥላቻ) ይልቅ መተባበር በኢትዮጵያ ምድር ሁነኛ ስፍራ ነበረው፡፡ እኔ አሁን እየጻፍኩት ያለሁት በታሪክ የተጠቀሰውን ለመከለስ አይደለም፡፡ ወይም በታሪክ ውስጥ የነበሩትን እውነቶች ለመካድም አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ ጦርነቶች ተካሂደዋል፡፡ ጦርነቶቹ ደግሞ ከውጭ ወራሪ ሃይላት ጋር እና የርስበርስ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ የተደረጉት ጦርነቶች ግን (የርስበርስም ይሁን ከውጭ ወራሪ ሃይላት ጋር ማለቴ ነው) የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ ሊጥሉት አይገባም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ የተደረጉ የጎሳ ግጭቶች( ጦርነቶች) በተለይም ባለፉት አርባ አመታት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ወንድማማቾች ጎራ ለይተው (በጎሳ ወይም በብሔር ጥላ ስር ሆነው፣ እኛና እነርሱ በመባባል፣ በሃይማኖት ተከፋፍለው ወዘተ ) ያደረጉት ግጭቶቸ፣ አሁንም በዚህ ዘመን የሚያደርጉት ፍልሚያ፣ ዜጎችን በብሔራቸው ማንነት ብቻ መሰረት የሚፈጸመው ግፍ የኢትዮጵያን አንድነት ያናጋዋል፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ ይወስደዋል፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ ጎሳዎች ወይም ብሐየሮች ሁሉ የራሳቸው ቋንቋ፣ባህል፣ሙዚቃ ወዘተ ወዘተ ያላቸው ናቸው ፡፡ ለዘመናትም በራሳቸው የኑሮ ዘዬ ህይወታቸውን የመሩ ናቸው፡፡ ዛዲያ ለምን አሁን ወደ ግጭት ውስጥ ይዶላሉ፡፡ በእኔ አስተያየት ኢትዮጵያውያን ወደ ግጭትና ትርምስ ውስጥ መግባት ፍላጎታቸው አይደለም፡፡ ርስበርሳቸው እንዲጋጩ እንዲገዳደሉ የሚያደርጓቸው የስልጣን ጥማት ያሰከራቸው የየጎሳው አምበሎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ተከባብረው የኖሩ ናቸው፡፡ አክራሪ የጎሳ ፖለቲከኞች እኛና እነርሱ በሚል መርዘኛ ቃል ተጠቀመው ልዩነትን ያራግባሉ፡፡የሀሰት ትርክት በማራገብ ፣ዜጎችን የጎሳ ፖለቲካ መርዝ በመጋት ግጭቶች እንዲቀጣጠሉ ማድረጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ የሚኖረው ለምን ያህል አመት ይሆን ? በዚች ምድር ላይ ውለን እናድራለን እንጂ ዘላለም አንኖራትም፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው ? በሚያልፍ ህይወት የማያልፍ ታሪክ ሰርተን ለማለፍ መንፈሳዊ  ወኔ የከዳን  ለምንድን ነው አክራሪ ብሔረተኞች በውይይት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን ወይም ልዩነቶችን በሃይል በግልበት ለመፍታት የሞከሩት፣ ለምንድን ነው ከውይይት ይልቅ ብረት አንሰተው ጫካ የሚገቡት/?፣ ወደ ጦርነት የሚገቡት ?  ( የሚሞክሩት፣ ለአብነት ያህል ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሲሉ ዜጎችን የእኛ አይደላችሁም በሚል ምክንያት እትብታቸው ከተቀበረበት፣ ለዘመናት ወልድ ከከበዱበት ቀዬ አፈናቅለዋል፡፡ ክቡር የሰው ህይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆነዋል፡፡ የፈጸሙት ግፍ ታሪክ በጥቁር መዝገቡ ውስጥ ያስቀምጠዋል፡፡) ለማናቸውም አስቲ ቁጭ ብለን በሰከነ መንፈስ እንወያይበት ፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጽናት፣ ከጎሳ ፖለቲከኞች ጋር በሰከነ መንፈስ ስለመነጋገር ማለቴ ነው፡፡ በእኔ በኩል ከባድ ፍርሃት ውስጥ እና ጥርጣሬ ውስጥ ወድቄአለሁ፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር የበቀሉ አብዛኞቹ የብሔር ነጻ አውጪ ድርጅቶች አባላት ከመስራቾቹ በበለጠ ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ የነጻ አውጪ ድርጅቶች መስራቾች የነበሩት ተከፋን፣ተጨቁነናል በሚል ትርክት ወዘተ ነበር ወደ ትግሉ የገቡት፡፡ ጥያቄዎቻቸውም በዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚፈቱ ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን ችግሮቹ ወይም ጥያቄዎቻቸው የተወሳሰቡ ሆነዋል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰለጠነ መንገድ፣ በሰከነ መንፈስ፣ አንቺ፣ትብሽ፣ አንተ ትብስ በመባባል መነጋገር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ውስብስብ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሚለያያቸው ነገሮች ይልቅ ወደ አንድነት ወደ የሚወስዳቸው መንገድ እንዲያተኩሩ እማጸናለሁ፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ ኢትዮጵያን በሚያህል ትልቅ ሀገር ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ያላቸው ልዩነት  የትዬየሌሌ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አይሆንልም እንጂ በሰላም መለያየቱ እውን ቢሆን እዳው ገብስ ነበር፡፡ ግን አይሆንም፡፡ እውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የነበሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( አፈሩን ገለባ ድርግላቸው) ከአንጋፋዋ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደጠቀሱት የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቁ አማራጭ የለውም ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር መሰባሰብ የማይፈልጉ የነጻ አውጪ ግምባሮች ከኢትዮጵያ ፍቺ ቢጠይቁ እንኳን አፈጻጸሙ እንዲህ ቀላል አይሆንም፣ በርካታ ያልተፈቱ እንቆቅልሾች በተለይ የድንበር ጥያቄዎች አሉ ነገሩ ብዙ መዘዝ እንደሚያመጣ አስጠንቅቀው ነበር፡፡ ሰሚ አድማጭ ሰው አግኝተው ይሆን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ኢትዮጵያውያን ትቼዋለሁ፡፡

2.ሁለተኛው ምክንያቴ መጀመሪያ ካቀረብኩት ጋር የሚመሳሰል ላይሆን ይችላል አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው እንደ ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ፣ ፕሮፌሰር እሸቱ ጮሌ፣ ዶክተር በፍቃዱ በቀለ፣ ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ የመሰሉ ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሀብት ጠበብት በተለያዩ የጥናት ወረቀቶቻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ መሰረት አሁን ባለው ሁኔታ ማናቸውም የኢትዮጵያ ክልል ብቻውን እንደ አንድ ጠንካራ፣ሉአላዊ ሀገር መቆም የሚያስችል የምጣኔ ሀብት ቁመና ላይ አልደረሰም፡፡ መማር ብንችል ከእናት ሀገሯ 1000 ኪሎሜትር የባህር በር በመያዝ ተገንጥላ ሉአላዊ ሀገር ለመባል ወግ የደረሳት ( እንደ ወግ ከተቆጠረ ማለቴ ነው) ኤርትራ ያለችበትን (   የደረሰችበትን) አስከፊ የእድገት ደረጃ ማየቱ በቂ ነው፡፡ የኤርትራ ወጣት ፓስፖርት አውጥቶ ወይም በህገወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች በአለም ላይ እንደ ጨው ዘር መበተኑ እንደ ስልጣኔ ከተቆጠረ እድገት ሊባል ይችላል፡፡ እርግጥ ነው በግለሰብ ደረጃ ሀብት ያፈሩ ኤርትራውያን መኖራቸው ሀቅ ነው፡፡ በእኔ የግል አስተያየት ግን ይህ ለእብዝሃው የኤርትራ ህዝብ ውድቀት ነው፡፡ አፍሪካ ሲንጋፖር እንደርጋታለን የነበረው የህልም እንጀራ ህልም ሆኖ ቀርቷል፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ክልሎች የምጣኔ ሀብት ድህነት ሁላችንም የምናውቀው መራር ሀቅ ነው፡፡ አዲስ አይደለም በሁሉም የሀገሪቱ ግዛቶች በሚገኙ ትንንሽ ከተሞች ውስጥ ሳይቀር የስራፈት ወጣቶች ቁጥር አስፈሪና እንቅልፍን የሚነሳ ነው፡፡ ሆኖም ግን አክራሪ ጎሰኞች ይህን እውነት መጋፈጥ አይፈልጉም፡፡ ስለሆነም ምኞታቸውን እውን ለማድረግ የጦርነት ታምቡር መምታታቸውን ቀጥለውበታል፡፡ ይህ ድርጊታቸው ሃላፊነታቸውን አለመወጣትም ብቻ አይደለም፡፡ በግልጽ እንደሚታየው ወንጀልም ጭምር ነው፡፡ ምኞታቸውንና አላማቸውን በሰላማዊ መንገድ መፈጸም ሲገባቸው ምስኪን የኢትዮጵያ ገበሬዎችን መጤ በሚል የዘረኞች ፍልስፍና ማፈናቀል፣ መግደል፣ መዝረፍ ሰብኣዊነት አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከጦርነት የሚገኝ ውጤት የለም፡፡ ከጦርነት የሚጠቀሙት የጦር መሳሪያ ደላሎችና ሻጮች ብቻ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ቁጥራቸው ቀላል ማይባል የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን መራር ሀቅ ይክዱታል፡፡ እነርሱ አላማችንን በሃይል ጭምር ማሳካት እንችላለን ባዮች ናቸው፡፡ አንዳንዶች ጠንካራ የምጣኔ ሀብት መገንባት የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት አለን ይላሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ባለፉት አርባ አመታት ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ፍላጎት እና አቅድ እንዳላቸው በነቢብም ፣በገቢርም አሳይተውናል፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት እድገት መሰረቱ የኢትዮጵያ አንድነት ነው፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው ‹‹ የራበኝ ፍቅር ነው ›› በሚለው ግሩም ሙዚቃ እንዳዜመችው ኢትዮጵውያን ሁሉ ወደ ላቀ እድገት ደረጃ  መድረስ  አይደለም፣ በህይወት ለመቆየት የንግድ ትሰስር እጅጉን አስፈላጊና ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ አሳዛኙ ሁነት እና ዚቅ ግን በኢትዮጵያ ሰማየ ሰማያት ላይ ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ አብዛኛው የአለም ክፍል  ወደ የበለጠ ትብብርና አንድነት በሚያመራበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ በተቃራኒው መንገድ በአክራሪ ብሔርተኞች ሴራና ግፊት ተቃራኒውን መንገድ  መከተሏ ሲታይ እድሏን አሳዘኝ ያደርገዋል፡፡

በመጨረሻም አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ በወዳጆቿም ሆነ በታሪካዊ ጠላቶቿ ፊት ተከብራ እንደምትኖር፣ ከሀገራት ጋር የምታደርገው ውይይትና ስምምነት በመከባበር ላይ፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን እንደሚችል ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድነታችንን ካለስጠበቅን መዳከምና የወደቀች ሀገርን ያስከትላል፡፡ የራስን ትንሽዬ ሀገር መመስረት ትርፉ በቅርቡም ይሁን በረጅም ግዜ ውስጥ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥቃትና መዳፍ ስር መውደቅን ያስከትላል፡፡ አያድረገውና  አክራሪ ብሔረተኞች ህልማቸው ተሳክቶ ከኢትዮጵያ ተለይተው የራሳችንን መንግስት መሰረትን ባሉ ማግስት  ከላይ ለመጠቃቀስ የሞክርኩት መራር እጣ ፈንታን እንዴት መቋቋም ይሆንላቸዋል ? ይህን ሀቅ ለማየት ወይም ለማስረገጥ እሩቅ ምስራቅ መሄድ አይጠበቅብንም፡፡ እዚሁ አፍንጫችን ስር ያሉ ጎረቤት ሀገራት ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡

እነኚህ በተለያዩ ምሳሌዎች ለማቅረብ የሞክርኩት ቁምነገሮች በአንድም ሆነ በሌላ ሁኔታ ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር መሆኗን ለማሳየት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ አንድነት መከበር አለበት የሚለውን የግል እምነቴን ወይም አስተያየት ከማቅረቤ በፊት አክራሪ ብሔረተኞች ወይም የነጻ አውጪ ድርጅቶች ጩሀትና ቀረርቶ ለምን ዛሬ ከመቼውም ግዜ በላይ ጎልቶ ይሰማል ለሚለው የግል ሃሳቤን ለአንባቢው ማካፈል ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ በቅድሚያ መገንጠል ሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ላስረዳ፡፡

መገንጠል ምን ማለት ነው ? መገንጠል የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በአጭሩ ‹‹ የራስን እድል በራስ ለመወሰን ›› ፍላጎት ማሳየት ነው፡፡ ‹‹Separatism, i.e. the desire for self-determination ›› ማንም ሰው እንደሚረዳው ይህ ጽንሰ ሃሳብ ( የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን ማለቴ ነው) በኢትዮጵያ ምድር መቀንቀን ከጀመረ ግማሽ ክፍለ ዘመን አለፈው፡፡ በእኔ በኩል ጽንሰ ሃሳቡ መቀንቀኑ ችግር የለብኝም፡፡ በተለይም ሁሉም ማህበረሰቦች እኩል መብት፣ባህላቸውና ቅርሳቸው እኩል በሚጠበቅበት መልኩ፣ እኩል የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ መብት በሚያጎናጽፍ መልኩ፣ እንዲሁም በህግና እውነት መሰረት ላይ የራስን እድል በራስ መወሰን መብት ገቢራዊ ቢሆን ክፋት ያለው አይመስለኝም፡፡ ለእኔ እንደ መሰረታዊ ችግር የሚሆነው፣ የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለው ጽንሰ ሃሳብ አዲስ ሉአላዊ ሀገር ለመመስረት በሚስችል መልኩ መለጠጡ ነው፡፡ ይህ በማንም ሀገር የሌለ መብት በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ ሳይቀር መግባቱ እጅጉን ያሳስበኛል፡፡ ቀደም ብዬ በጨረፍታ ለመነካካት እንደሞከርኩት መገንጠል የሕዘብ ፍላጎት ሳይሆን የአክራሪ ብሔረተኞች ፍላጎት ነው፡፡ ወከለነዋል የሚሉት ብሔር ፍላጎት ምን እንደሆነ አሁን ድረስ በውል አይታወቅም፡፡ በነጻነት መድረክ ላይ ቆሞ ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ እድሉን ላገኘም፡፡ የበርካታ ብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችና አቀንቃኝ ምሁራን ግን እስኪያንገሸግሸን ነግረውናል፡፡( በነገራችን ላይ ሁሉም በጎሳ ስም የተደራጁ ፖለቲካ ድርጅቶች በግልጽ ምኞታቸውን አልነገሩንም፡፡ ሆኖም ግን አንዳንዶች በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር መኖር ምኞታቸው እንደሆነ በአደባባይ ሲናገሩ ይሰማል፡፡  ) ለአብነት ያህል ከትፍራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መማር ለብን ነገር ቢኖር ( ቁምነገር ከተገኘበት ማለቴ ነው) የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ወክዬዋለሁ የሚለውን መላውን የትግራይ ህዝብ ፍላጎትና ህልም ያሟላ አለመሆኑ ነው፡፡( እርግጥ ነው በርካታ አባላቶቹንና ደጋፊዎቹን ከትቢያ አንስቶ ወደ የላቀ የኑሮ ደረጃ ላይ እንዳወጣቸው ክርክር የሚያጭር አይመስለኝም፡፡) በተቃራኒው የትገራይ ነጻ አውጪ ድርጅት በትግራይ ህዝብ ስም ፣ ማንኛውንመ ዋጋ በመክፈል፣ የማካያቬሊን ሴራ ገቢራዊ በማድረግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጀርባ ላይ የወጣ  እባጭ ወይም ቡግንጅ ነበር፡፡ ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ብዙ ርቀት ሄደው ነበር፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ከዚህም እልፍ በማለት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መሪዎች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ብቻ የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ለማቃቃር ያልማሱት አፈር ፣ ያልበጠሱት ቅጠል የለም፡፡

 ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብ በቃኝ በማለቱ ከ27 አመታት በኋላ የማእከላዊ መንግስት ስልጣናቸውን መልቀቅ ግድ ብሏቸዋል፡፡ ይህ ታላቅ ትምህርት ሊሆነን ይገባል፡፡ ዛሬም ቢሆን የምነወክለውን ህዝብ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ የሚያራምዱ የብሔር ድርጅቶች የትግራዩን ነጻ አውጪ ድርጅት መንገድ እተከተሉ ስለመሆኑ ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ ( በብዙ የፖለቲካ ተንታኞችና ኢትዮጵያዊ የታሪክ ጸሃፊዎች በጥናት እንደተረጋገጠው የወያኔ አላማና የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ፍጹም የተለያየ ነው፡፡ አብዝሃው የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር አንድ ላይ በመሆን በብዙ ጦር ሜዳዎች መስእዋትነት የከፈለ ነው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡) የኢትዮጵያ ህዝብ መንቃት፣ ሞኝ መሆን የለበትም፡፡ በጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች ቅስቀሳ መታለል የለበትም፡፡ እንዴት ነው አብረን መኖር የምንችለው በማለት የኢትዮጵያ ህዝብ በየሰፈሩ መወያየት አለበት፡፡ እድል ፈንታችን አንድ ላይ ነው፡፡ በአንዱ የሀገሪቱ ክፍል የሚፈጠሩ ችግሮች የሁላችንም ችግር መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡

የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ መንገዱ በየት ይሆን ?

አሁን ወደ ዛሬው ጽሁፌ ዋና ነጥብ እወስዳችኋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ነው አንደነቷ የተጠበቀ፣የተረጋጋች ፣ሰላሟ የተረጋገጠ፣ እና በምጣኔ ሀብት ያደገች ሀገር መሆን የምትችለው ?  መልሱን በተመለከተ በስራ ገበታችሁ፣ በማኪያቶ ወግ ላይ፣ በሰፈራችሁ ጭምር እንድተወያዪበት ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ይሆናል፡፡ በእኔ በኩል ግን ከላይ ላቀርብቁት ጥያቄ መልስ የመሰሉኝን አራት መሰረታዊ ነጥቦችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ እነኚህም አራት ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • በጎሳ ወይም ቋንቋ ላይ የተመሰረቱት ክልሎች በሌላ ለአንድነት በሚበጅ የፌዴራል ቅርጽ እውን መሆን አለባቸው
  • በጎሳ የፖለቲካ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ስያሜ በሌላ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲ ስያሜ ቢቀየር 
  • የከልል ልዩ ሀይል አባላት ወደ መከላከያ ሰራዊት አባልነት የሚቀየሩበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው
  • የኢትዮጵያን አንድነት ለማስከበር እና ለማሳለጥ ይረዳ ዘንድ አንድ ጠንካራ ብሐራዊ ተቋም ቢቋቋም መልካም ነው፡፡

1.በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርአት ስለመከተሏ ጠቃሚነት ብዙም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርአት የተዋቀሩ ክልሎች ቋንቋን ወይም ጎሳን መሰረታቸውን ማድረጋቸው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ አንዱን ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጎሳ ክልሎች ለኢትዮጵያ ችግርን ስለመቀፍቀፋቸው በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ አንዱን ኢትዮጵያዊ የክልሉ ተወላጅ አይደለህም በሚል ምክንያት በርካታ መብቶችን የሚነፍጉ ክልሎች አወቃቀር ለኢትዮጵ አንድነት አይበጅም፡፡ ክልሎች በመልክአምድራዊ ወይም በሌላ የአከላል ዘዴ እውን የሚሆኑበት ዘዴ በባለሙያዎች ተጠንቶ ለህዝብ ውሳኔ ቢቀርብ ከገባንበት ውጥንቅጥ ለመውጣት እንችል ይሆን ብዬ እራሴን ሰርክአዲስ እጠይቃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለውን መብት የሚቃወም ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የራስን እድል በራስ ለመወሰን ብቸኛው መፍትሔ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ብቻ አይደለም፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ገቢራዊ ለማድረግ ሌሎች በርካታ የፌዴራል ስርአት አይነቶች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል መሰረቱን መልክአ ምድራ ላይ ያደረገ የፌዴራል ስርአት ይጠቀሳል፡፡ ሌሎችም የፌዴራል ስርአት አይነቶች አሉ፡፡ በዚህ መንፈስ መሰረት በዲሞክራሲና በእኩልነት መንፈስ ክልሎችም ሆኑ ወረዳዎች የራስን እድል በራ መወሰን መብታቸው መከበር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን የራስን እድል በራስ መወሰን የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የኢትዮጵያን አንድነት ማናጋት የለበትም፡፡ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር፣ በክልላቸው ጉዳይ የፌዴራል መንግስቱ ጣልቃ ሳይገባ በክልላቸው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በእኩልነት መንፈስ ማስተዳደር ከቻሉ እዳው ገብስ ነው፡፡ በአጭሩ ለወደፊቱ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት መንፈስ የሚያይ የክልል አወቃቀር እውን እንዲሆን በሰለጠነ መንገድ መነጋገር አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

  1. በሁለተኛው ነጥቤ ላይ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ያለመረጋጋት እንዳይኖር ስለማድረጉ፣ ጥላቻን ስለመቀፍቀፉ ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡ የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሰላምን አሰፍኗል ብሎ የሚከራከር ይኖር ይሆን ሊኖር ይችላል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ሰላምን የሚያደፈርስ ነው ተብሎ ለምን ይጻፋል የሚል ሰውም ሞልቶ ተርፏል፡፡ ሃሳብን በሃሳብ መሞገት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ህገመንግሰት ሳይቀር መሰረታቸውን በጎሳ ላይ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲደራጁ የሚፈቅድ ቢሆንም የጎሳ ፖለቲካ ካደረሰብን ጉዳት በመማር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ወደ መሃል የሚያቀራርብ የፖለቲካ ስርአት ለማምጣት ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አዋቂዎች አንድ የሚያስማማ ሰነድ አዘጋጅተው ይወያዩበት ዘንድ እማጸናለሁ፡፡ በቅርቡ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያቀረቡት የፖለቲካ ሰነድ አርአያነት ያለው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

3.`በ1983 ዓ.ም. በወያኔ ቂም በቀል የደርግ ሰራዊት በሚል ግልብ ውሳኔ የኢትዮጵያ የጦር ሀይል ቢፈርስም ወይም የተበተነ ቢሆነም የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል ወይም የጦር ሰራዊት ከተመሰረተ ከ70 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡. ኢትዮጵያ በወታደራዊ ተቋማት ግንባታ እረዥም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም ከራሷ አልፋ በተባበሩት መንግስታት የጋራ ጸጥታ ፕሮግራም ስር የክቡር ዘበኛ እና የጦር ሰራዊት አባላት በኮሪያ ልሳነምድርና በኮንጎ ካታንጋ ግዛት በወርቅ ቀለም የተጻፈ ታሪክ አስመዝግበው አልፈዋል፡፡ ዛሬ ወያኔ ከማእከላዊ መንግስት ስልጣኑ ተሸቀንጥሮ ወድቋል፡፡ ስለሆነም ከ 3 አመት ወዲህ ማእከላዊ መንግስቱን የጨበጠው ፓርቲ ካለፈው የወያኔ ከባድ ስህተት በመማር የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት በሕብረብሔራዊ ስሜት በማደራጀት ኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ በታሪክ ፊት ቆሟል፡፡ በተለይም የክልል ልዩ ሀይል አባላት ወደ መከላከያ ሰራዊት አባልነት ስለሚቀየሩበት ሁኔታ ቁጭ ብሎ እንዲያስብ እንማጸናለን፡፡ የክልል ሚሊሻዎች ዛሬ በግዜው መፍትሔ ካልተበጀለት በአደጋ ግዜ ለማእከላዊ መንግስቱ የእግር ውስጥ እሳት መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡

ለኢትዮጵያ መረጋጋትና አንድነት ይበጅ ዘንድ የኢትዮጵያ መከላኬ ሰራዊት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች የተወጣጣ ስለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህ ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርብ አንድነታቸውን የሚያጸና ነው፡፡ የመከላከያ ሰራዊት ጠንካራ መሆን ለኢትዮጵያ አንድነት መተኪያ የለውም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዘመኑ የዋጀውን የጦር መሳሪያ መታጠቅና በሚሊተሪ ሳይንስ የዳበረ እውቀት ሊኖረው ግድ ነው፡፡

በመጨረሻም ብሔራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ የሚረዱ ብሔራዊ ተቋማት ማቋቋም እጅጉን ጠቃሚ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንኚህ ተቋማት ለአንድ ሀገር አንድነት ጠቃሚ እንደሆነ ሚያስረዱ ወይም የሚስተምሩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያዘጋጃሉ፡፡ ነጻ የወይይ መድረክ እንዲከፉ አበርክቷቸው የትዬየሌሌ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሁሉም የአፍሪካ ሀገሮች በተለየ ሁኔታ እንዲህ አይነት ተቋማት ያስፈልጓታል፡፡ እነኚህ ተቋማት አንድን የፖለቲካ ድርጅት በመቃወም ወይም በመደገፍ ላይ ሳይቆሙ ለህዝብ አንድነት የሚበጁ ሃሳቦችን ማንሸራሸር ዋነኛ አላማቸው መሆን ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ ለአብነት ያህል በደርግ ዘመን መሃይምነትን ለማጥፋት እንደተደረገው ‹‹ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ›› አይነት ‹‹ ብሔራዊ የጤና ፕሮግራም ›› የሚል ፕሮግራም በመፍጠር ዜጎች ሁሉ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ጥቅም ወይም ጉዳት አለው የሚሉ ኢትዮጵያዊ ወንድሞች ካሉ ድምጻቸው የሚሰማበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ቢችሉ ለብሔራዊ አንድነታችን ይበጃል ባይ ነኝ፡፡

ከመደበኛው ጦር ሰራዊት አባልነት ባሻግር ኢትዮጵያውያን ወጣጦች በራሳቸው ፍላጎት፣ ያለምንም አስገዳጅነት የብሔራዊ አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ ቢጠና እና ገቢራዊ ቢሆን  ወጣቶቹ የባህል፣የቋንቋና ማህበራዊ ግንኙነት ልውውጥ ያደርጋሉ ብዬ አስባለሁ ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያጠናክራል የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር በአጼ ሀይለስላሴ ዘመን እንደተደረገው የዩነቨርስቲ ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ በመሄድ ማስተማር፣ በደርግ ዘመን የእድገት በህብረት አይነት ዘመቻ በዚህ ዘመን ገቢራዊ ለማድረግ ቢሞከር አንድነት ጠቀሜታው የጎላ ነው ባይ ነኝ፡፡ እንዲህ አይነት ‹‹ ብሔራዊ ፕሮጄክቶች ›› እርስበርስ  ለመተዋወቅ ብቻ የሚረዱ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያውያን መሃከል የነበረውን የዘመናት ትብብርና አንድነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው፡፡ ሰላም፣ፍቅርና አንድነት ለኢትዮጵያና ህዝቧ ይሁን፡፡ አበቃሁ፡፡

 

Filed in: Amharic