>

"የወልቃይት እውነት ቅድመ ሕወሃት"  (በታርቆ ክንዴ) 

“የወልቃይት እውነት ቅድመ ሕወሃት” 

በታርቆ ክንዴ

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ታሪክ ባይፃፍ፣ ሰዎች ባይናገሩ፣ ከቦታው የማይለቀው፣ ሄዶ የማያልቀው፣ ታላቁ ወንዝ ተከዜ ይመሰክራል ይላሉ አበው። ተከዜ ከስፍራው አይለቅም፣ አይዋሽም፣ አያስዋሽም በተቀመጠበት አለና።
ኢትዮጵያውያን–ከሀገር በቀደመች፣  የሰው ዘር ምንጭ በሆነች፣ የጨለማውን ዘመን መርታ ባሻጋረች፣ መንግሥትነትን መሥርታ ባሳዬች፣ ፊደል በቀረፀች፣ ቀመር በቀመረች፣ ተፈጥሮን በቅጡ በተረዳችና በመረመረች፣  ወራትን በጥበብ በከፋፈለች፣ ታሪክ ሠርታ ቀለም በጥብጣ  ሌጦ አለዝባ ታሪክ በከተበች፣ የሥልጣኔ መግቢያ  በር፣ መፍቻ ቁልፍ በሆነች፣ ግርማ  ባላት፣  ሞገስ በተቸራት፣  ጠላት  በፈራት፣ ፈጣሪ ባከበራትና አብዝቶ በጠበቃት ሀገር ነው የሚኖሩት።
በመልካሟ ምድር መልካም ነገር እየሠሩ፣ ለመልካም ነገር እየተባበሩ፣ ሕግና ሥርዓትን እያከበሩ፣  ፈጣሪያቸውን እየፈሩ፣ ማንነታቸውን ለመንካት የከጀለውን ሁሉ ከባሕር ማዶ እያስቀሩ፣ የሕይወትን መንገድ በጥበብ እያሰመሩ ይኖራሉ ኢትዮጵያዊያን።
መልካሞቹ ኢትዮጵያውያን ከእኛ ምድር ተነስታ ለሰፋች ዓለም አንጠብም መቆያችን ምድር፣ ዘላለማዊ ማረፊያችን ሰማይ ነው ይላሉ። የሰው ዘር ሁሉ መነሻው ከእነርሱ ነውና። የሰው ልጅ በተፈጠረበትና በተፈጠረለት ምድር የምድርንም የሰማይንም ሕግጋት አክበሮ የትም ይሥራ ይላሉ። ቀዳሚዎች ናቸውና በዘገዬ አመለካከት ጊዜ አያጠፉም። ኢትዮጵያውያን ሚስጥር በሆነች ምድር የሚኖሩ ሚስጥር የሆኑ ናቸው። ዓለም በኢትዮጵያ ይቀናል እንጂ ኢትዮጵያ በዓለም አትቀናም።
በሚያስደንቀው የመንግሥትነት ታሪኳ የሚያስደንቅ አሻራ አስቀምጣለች። በዘገዬው ዘመን ቀድማ ተገኝታለች። ብርሃን በጠፋበት ዘመን ብርሃን ሆናለች። ተስፋ በታጣበት ዘመን ተስፋ ሆናለች። ጉልበተኞች ከልካይ ባጡ ዘመን ተው ብላ አደብ አስይዛለች። በገዘፈው ታሪኳ የሚገጥማትን ችግር በልጆቿ  እየነቀለች ተጉዛለች። የሚገጥማትን ችግር የምትፈታበትን ኀያል ጀብዱ በዓለም መዝገብ ውስጥ እንዳይጠፋ አድርጋ አስመዝግባለች።
የመንግሥትነት ታሪኳም ዘመንን አሻግሮ ዛሬ አድርሷታል። ኢትዮጵያ በዘመናት ቅብብሎሽ ካየቻቸው ሥርዓቶች መካከል በቅርቡ ያከተመለት የሕወሃት መራሹ መንግሥት አንደኛው ነበር። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ፈተናዎችን አይታለች። ለዘመናት እንደውቂያኖስ የሰፋው ልባቸው፣ እንደ አለት የጠጠረው አንድነታቸው፣ እስከ ሞት የሚያስጉዘው ኢትዮጵያዊነታቸው ተፈትኖ ነበር። በፈተናው ሳይወድቅ ተሻገረው እንጂ።
በሕወሃት ዘመን በጉልህ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የወልቃይት ጠገዴ የነፃነት ጥያቄ ነበር። ሕወሃት በበረሃ ውስጥ ካሰመራቸው መስመሮቸ አንደኛው የግዛት ማስፋፋት ነበር። ይህም ከተከዜ ተሻግሮ ወልቃይት ጠገዴን ወደ ትግራይ ክልል  ማካለል ነበር።
በክፍለ ሀገር  የነበረውን አስተዳደር በድብቅ ዓላማ ክልል ተብሎም ተከለለ። ከተከዜ ወዲያ  በክፍለ ሀገር ተካሎ የማያውቀውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አካባቢን ከተከዜ ወዲያ ወስዶ ከለለው። ይህም ድብቅ ዓላማ ከመነሻው ጀምሮ የሕዝብን ቁጣ ያስነሳ በመሆኑ በሀገሪቱ ፖለቲካ ከፍተኛውን ሥፍራ ያዘ። በዚህም ብዙዎች ሞቱ፣ ተንገላቱ፣ ተሰደዱ።
የወልቃይት እውነት ቅድመ ሕወሃት ምን ይመስል ነበር?  በሥራ ዘመናቸው የመጀመሪያ ዓመታት  የሠሩት በጎንደር ክፍለ ሀገር በሑመራ ነው። ስለ አካባቢው የሚያውቁት እውነት አላቸው። የቀድሞው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የአሁኑ  የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ።
“በ1972 ዓ.ም በጎንደር ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ በአካባቢ ጤና አጠባበቅ ትምህርቴን ጨረስኩ። በዚህ ሙያም ሥራ ለመያዝና የቦታ ምርጫ ለማወቅ ወደ ሀገሪቱ ጤና ጥበቃ  አዲስ አበባ ሄድን። በአዲስ አበባ እጣ አወጣን። በወቅቱ የጎንደር ጠቅላይ ግዛት ኢሃፓ ይንቀሳቀስበት ስለ ነበርና ስጋት ስለነበር  ከሌሎች ክፍለ ሀገራት የመጡ ተመራቂዎች እኛ በምናውቀው እንድንሄድ ጠየቁን። እኛም ጥያቄያቸውን ተቀበልን”  ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
በወቅቱ በጎንደር ክፍለ ሀገር እጣ የምናወጣው ሶስት ልጆች ነበርን።  እኔ ስማዳ፣ ሁለቱ ጓደኞቼ ደግሞ ጭልጋና ሑመራ ደረሳቸው። እኔም የሑመራውን ልጅ ቀይሬ  “ሑመራ ሄድኩኝ። ሑመራ ያን ጊዜ በዳባት አውራጃ ሥር ነበር የሚተዳደረው። ጊዜውም 1973 ዓ.ም ነበር። በዚያ ጊዜ ኢትዮጵያ ከነበሯት አሥራ አራት ክፍለ ሀገራት መካከል የጎንደር ክፍለ ሀገር በሑመራ በኩል የሚዋሰነው ከኤርትራ ክፍለ ሀገር ነበር” ብለውናል።
እሳቸው በሑመራ ጤና ጣብያ እያሉ  በኤርትራ ክፍለ ሀገር እምናኻጅር ጤና ጣብያ የነበሩ ታካሚዎችን ለማከም ከጎንደር ክፍለ ሀገር ሑመራ ተሻግረው የህክምና እርዳታ መስጠታቸውንም አስታውሰዋል። ከአስመራ መጥቶ የህክምና እርዳታ ለመስጠት ተሰነይ ላየ የፀጥታ ሥጋት ስለነበር በቅርብ የሚገኘው የጎንደር ክፍለ ሀገሩ ሑመራ ጤና ጣብያ  የህክምና እርዳታ እንዲያደርግ ተብሎ ነዉ ። ይህ ብቻ ሳይሆን በሡዳን ጠረፍ አምዳይት ላይ ይኖሩ በነበሩ ዘላኖች “መርበርግ” የሚባል ወረርሽኝ ተነስቶ የሑመራ ጤና ጣብያ እርዳታ ማድረጉንም ነግረውኛል።
የጎንደር ክፍለ ሀገር በሑመራ በኩል ከትግራይ ጋር የሚያዋስን ነገር የለውም ነው ያሉኝ ፕሮፌሰሩ። የጎንደርን ክፍለ ሀገር ከኤርትራ እና ከትግራይ ክፍለ ሀገራት ጋር የሚለየው ተከዜ ነውም ነው ያሉት። ሑመራ የሚገናኘው ከቀድሞው የኤርትራ ክፍለ ሀገር ከአሁኗ ኤርትራ ጋር እንደሆነ አስረድተዋል። አካባቢው የተመቼ ስለነበር ከኤርትራ፣ ከትግራይና ከሌሎች አካባቢዎች እየመጡ ከአማራው ማኅበረሰብ ጋር አብረው ይኖሩ እንደነበርም ነግረውኛል። የዛን ጊዜ እንኳን የአንድ ሀገር ሕዝብ ቀርቶ የሱዳን ሰዎችም መጥተው በሑመራ ይኖሩ ነበር ብለዋል። የበረሃው ሰው ለጋራ ኖሮ የተመቼ ስለሆነ  ብቻን መብላትም ሆነ መኖር አይታወቅም ነበር።  ሁሉም በፍቅር ነበር የሚኖረው፣ መሬቱ ግን የጎንደር ክፍለ ሀገር  ነው። መግባቢያውም አማርኛ ነበር።  ለሥራ የሚመጡ ሰዎች በቋንቋቸው ይናገሩም ነበር ነው ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ።
ተከዜ ግልፅ የሆነ  ወሰን ነው፣ ከተከዜ  ወዲያ በሑመራ በኩል የኤርትራ፣ በላይ በኩል ደግሞ የትግራይ ነው ብለውኛል ፕሮፌሰሩ።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ጉዳይ ታቅዶበት የመጣ ነው፣ ሰው ግን በየዋህነት እንደዚህ ይሆናል ብሎ አልገመተም ነበር፣ መዘዙ እየታወቀ የመጣው ቆይቶ ነው፣ ታቅዶ የተሠራበት ስለ ነበር ትውልዱን ለስቃይ የሚዳርግ ሆኖ መጣ ነው ያሉት። በሆድ አደሮች የመጣው ችግር እዚህ ድረስ መድረስ አይገባውም ነበር ብለዋል።
እውነት  እውነት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ልክ አለመሆኑን ማስገንዘብ ይገባል፣ ይህ ሉዓላዊነትን መዳፈር ነውም ብለዋል።
የአካባቢው ጉዳይ ከአንድ ትውልድ በላይ ሲሠራበት መቆየቱን የተናገሩት ፕሮፌሰር መንገሻ ትውልዱን እውነተኛውን ነገር ለማስያዝ ሥራ ቢጠይቅም እውነት እውነት ነው፣ እውነት ተክዶ ሊወሰድ የሚችል ነገር የለም ነው ያሉት። አማራጩ እውነታውን መቀበል ነው፣ እውነታውን ከተቀበሉ በኋላ ዘር ሳይቋጠሩ በጋራ መኖር ነው የሚሻለውም ብለዋል። ኢትዮጵያዊያን ወደ ቀደመው መልካም ባሕል መመለስ እንዳለባቸውም መክረዋል።
ወጣቱ ትውልድ ብዙ የተወናበደ ችግር አለበት ያሉት ፕሮፌሰር መንገሻ ታሪክና ባሕሉን የሚያውቁ ሰዎች ማስረዳት አለባቸው፤ ራስን ማታለል አያስፈልግም፣ ለአከባቢው ጉዳይ መፍትሔ የሚሆነው የውስጥ ጉዳይ ነውም ብለዋል።
የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያ እንድትኖር የማይፈልጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካ በቀኝ ግዛት  እንዳትሆን ያደረገችና ጣልያንን አሸንፋ ለውጩ ዓለም መጥፎ ተምሳሌት ስለሆነች ኢትዮጵያ መኖር የለባትም የሚሉ ብዙዎች መሆናቸውን ነው የተናገሩት። የቀኝ ግዛት ዘመን አለቀ የሚባል አይደለም አሁንም ምኞት አላቸው፣ ኢትዮጵያ ባትኖር አፍሪካን ተቆጣጥረን እንቀጥል ነበር የሚለው ቁጭት አልበረደም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ  እንኮራለን፣ ራስን መሆን ይጠይቃል፣ በስሜት መነዳት አያስፈልግም፣ ዓላማን ማወቅና ለዓላማ በፅናት መቆም ይገባልም ብለዋል ፕሮፌሰር መንገሻ።
በምድር የምንኖረው አንድ ጊዜ ነው፣ ምን ያክል ጊዜ እንደምንኖርም አናውቅም፣ በምንኖርበት ጊዜ ግን መልካም ነገር መሥራት ይገባናል ነው ያሉት። ሌሎቸ የራሳቸውን ጨርሰው አፍሪካን ለመጠቀም ነው የሚጥሩት። ዓለም የሚቀናበትንት የኢትዮጵያን ባሕል፣ ወግና ታሪክ ማክበርና መጠበቅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
Filed in: Amharic