>

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲሁም በህወሀት ባለስልጣናት ላይ እቀባ ጣለች...!!! (መርእድ እስጢፋኖስ)

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ እንዲሁም በህወሀት ባለስልጣናት ላይ እቀባ ጣለች…!!!
መርእድ እስጢፋኖስ

 

  በኢትዮጵያና በኤርትራ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ኃይሎችና በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሉን አሜሪካ አስታወቀች!!!
 
ይህ የጉዞ ዕቀባ ውሳኔ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ እንዲፈጠር ያደረጉ ወይም የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ እንዳይሳካ ያደናቀፉ የአገራቱን የደኅንነት ኃይል አባላትን ወይም የአማራ ክልልና ኢመደበኛ ኃይሎችንና ሌሎች ግለሰቦች እንዲሁም የህወሓት አባላትን የሚያካትን መሆኑ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ ላይ “ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃ መውሰድ ያለበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ የጉዞ እገዳ በተጨማሪ አሜሪካ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው የምጣኔ ሀብትና የደኅንነት ድጋፍ ላይ መጠነ ሰፊ ዕቀባ ማድረጓን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።
ነገር ግን አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጣቸው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቁልፍ የሆኑ ድጋፎችና የሰብአዊ እርዳታዎች እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
ኤርትራንም በተመለከተ ከዚህ በፊት ጥላቸው የነበሩ ሠፊ ዕቀባዎች ባሉበት እንደሚቀጥሉ ተነግሯል።
መግለጫው በማጠቃላያው ላይ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ ለተከሰተው ቀውስ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፤ ለዚህም ጥረት አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጿል።
የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ መፍትሔ እንዲገኝ በከፍተኛ ባለሥልጣናቱ በኩል ጥረት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ልዩ መልዕከተኞች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።
አሜሪካ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ቀውስና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጉዳይን በቅረበት እንዲከታተሉላት አንጋፋውን ዲፕሎማት ጄፍሪ ፊልትማንን በልዩ መልዕክተኝነት ሰይማ ከሳምንታት በፊት በአካባቢው ጉብኝት አድርገዋል።
የአሜሪካ በተለያዩ አገራት ላይ የተለያየ ማእቀብ ጥላለች

አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ኃያላን አገራት የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ ግንኙነት፣ የንግድ፣ ወታደራዊ፣ እርዳታ የማቆም እና ሌሎችም ማዕቀቦች በተለያየ ምክንያት ይጥላሉ።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል ሲባል፣ በአንድ አገር ውስጥ በተለያየ መንገድ አፈና ሲካሄድ ወይም ደግሞ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚተላለፍ ተግባር ተከናውኗል በሚባልባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ኃያላን አገራት ማዕቀብ ይጥላሉ።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ በወታደራዊና የደኅንነት አባሎች፣ በአማራ ክልል ኃይሎች እንዲሁም በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች።

ለዚህም በምክንያትነት የቀረበው በትግራይ ክልል የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል፣ የግጭቱ ተሳታፊ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት አለማግኘቱ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ መግባታቸውን ጠቅሶ በማንኛውም መንገድ ጫና ለማሳደር መሞከሩን እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ አስታውቋል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ማዕቀብ ከጣለችባቸው አገሮች ጥቂቱን እንመልከት።

ከተለያዩ ድረ ገጾች የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ አሜሪካ እስከ አውሮፓውያኑ 2020 ማዕቀብ ከጣለችባቸው አገሮች መካከል ቤላሩስ፣ ብሩንዲ፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ኒካራግዋ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶርያ፣ ዩክሬን፣ ሩስያ፣ ቬንዝዌላ፣ የመን እና ዚምባብዌ ይጠቀሳሉ።

የአሜሪካ እንዲሁም የሌሎችን አገራት ማዕቀብ መጣል በአሉታዊም በአወንታዊም መንገድ የሚተነትኑ አሉ። በእርግጥ ሁሉንም አይነት ማዕቀብ በአንድ መመዘኛ ለመለካት አይቻልም።

ማዕቀቡ የተጣለበትን አገር እውነታ፣ ማዕቀቡ የተጣለበትን ምክንያት፣ ማዕቀቡን የጣለው አገር እና የተጣለበት አገር የሚያቀርቡትን መከራከሪያ እንዲሁም ማዕቀቡን በመጣል ለማግኘት የታለመው ነገር ከግምት መግባት አለበት።

በአንድ በኩል አገራት ማዕቀብ በመጣል የአገራቸውን ጥቅም ለማስጠበቅና ኃያልነታቸው ጎልቶ እንዲታይ ማድረጋቸውን የሚተቹ አሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ አገራት ላይ በማዕቀብ ጫና በማሳደር የሰብዓዊ መብት እንዲከበር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንዳይጣሱ ማረቅ ይቻላል ብለው የሚከራከሩም አሉ።

ማዕቀብ መጣል ምን ያህል ውጤት ያመጣል?

የአገራትን ምጣኔ ሀብት እና የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ማሽመድመድ ዋጋ አለው? ማዕቀብ የሚጥሉ አገራት የምጣኔ ሀብት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ቢኖራቸውም ሌሎች አገራት ላይ ማዕቀብ የመጣል የሞራል ልዕልና አላቸው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ይሰነዘራሉ።

ዘለግ ላለ ጊዜ ማዕቀብ ከተጣለባቸው አገራት አንዷ ኩባ ስትሆን፤ ማዕቀቡ የተጣለው በአሜሪካ መንግሥት የሚደገፈው አስተዳደር በፊደል ካስትሮ ከተሸነፈ በኋላ ነው።

አሜሪካ ኩባ ላይ የጣለችው የንግድ ማዕቀብ ነው።

ሌላዋ አገር ኢራን ናት። እአአ ከ1979ቱ አብዮት በኋላ ከምዕራባውያን ጋር ወዳጅ የነበሩት የኢራኑ ሻህ ከሥልጣን ተወግደዋል።

አሜሪካ ኢራን ላይ የጣለችው ማዕቀብ ዛሬም ድረስ በሁለቱ አገራት ለሚስተዋለው ውጥረት አስተዋጽኦ አበርክቷል። አሜሪካ ኢራንን “ሽብርን በመደገፍ” እንዲሁም ከዩራንየም ማበልጸግ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ትወነጅላለች።

ኢራንም ብትሆን አሜሪካን በበጎ አትመለከትም። በሁለቱ አገራት ያለው ውጥረት ዓመታትን ተሻግሮ ዛሬም ድረስ እንዳለ ነው።

አሜሪካ ማዕቀብ ከጣለችባቸው አገሮች ሌላዋ ሰሜን ኮርያ ናት። እአአ በ1950 የተቀሰቀሰው የሁለቱ አገራት አለመግባባት እስከዛሬም ውጥረት አንግሶ ዘልቋል።

የአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ማዕቀብ ሰሜን ኮርያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢያሳድርም፤ ሰሜን ኮርያ በምዕራባውያን ዘንድ የሚሰጣት ስም እምብዛም የሚያሳስባት አይመስልም።

ማዕቀብ የሚጥሉ አገራትን ያለፈ ታሪክ እንዲሁም በአገራቸው ውስጥ የሚገኝ ነባራዊ ሁኔታን በማጣቀስ ማዕቀብን የሚኮንኑ አሉ። አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ደግሞ መንግሥታት ለሚፈጽሙት ወንጀል ተጠያቂ ከሚደረጉበት መንገድ አንዱ ማዕቀብ ነው ይላሉ።

አሜሪካ የምትጥላቸው ማዕቀቦች አገራት ላይ ብቻ ያነጣጠሩ አይደሉም። በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች እና የፖለቲካ ተቋማት ላይም እገዳ ይጣላል።

ለምሳሌ እአአ በ2017 ሚያንማር ውስጥ ከተፈጠረው ውዝግብ ጋር ተያይዞ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የቪዛ እገዳ ተጥሏል።

የአሜሪካ ማዕቀብ ከሚያካትታቸው መካከል የጦር መሣሪያ ንግድ እገዳ፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እገዳ፣ የንግድ ዝውውር እገዳ ይገኙበታል።

በተጨማሪም አገራት ብድር እንዳያገኙ ማድረግ፣ ማዕቀብ የተጣለባቸውን ግለሰቦች ቪዛ መከልከል እንዲሁም የገንዘብ ዝውውር ላይ እገዳ መጣልም ይጠቀሳሉ።

Filed in: Amharic