ዘሪሁን ገሠሠ
በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ ወረዳ እየደረሰ ባለው ጥቃት እስካሁን 40ሺህ የአማራ አርሷደሮች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሠደዋል፡፡ ሰሞኑን በነበረው መጠነ ሰፊ ጥቃት 4 አርሷደሮች መገደላቸው ታውቋል፡፡ ጥቃት ሸሽተው ወደአጎራባች አካባቢዎች የተሠደዱት አርሷደሮች ከብቶቻቸውንና ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው በየከተማውና በየጫካው ተበትነው በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ከስፍራው ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ተጠናክሮ የቀጠለው የተቀናጀ ጥቃት ፥ መረጃዎችን በማፈንና የነዋሪዎችን የስልክ ግንኙነት በማቋረጥ ጭምር እየተካሄደ መሆኑንና ነዋሪዎቹ ተስፋ ቆርጠው ሞትን ቁጭ ብለው ከመጠበቅ የዘለለ ራሳቸውን ለመታደግ የማይችሉበት ሁኔታ መፈጠሩ ተገልጿል ፡፡
የስልክ ግንኙነቶችን በማቋረጥ ረገድ መንግስት በቀጥታ እንደሚሳተፍበት ለማረጋገጥ ከዚህ ቀደም መረጃዎችን ወደሚያደርሱኝ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ ከ15 የሚልቁ የእጅ ስልኮች ላይ በተደጋጋሚ ያደረኩት ሙከራ << ጥሪዎ ወደተቀባዩ አድራሻ መድረስ አይችልም! >> የሚል መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የኔትወርክ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ስልኮች በተጠና መልኩ የግንኙነት መስመራቸው ተቋርጧል፡፡ ይህንን ገለልተኛና ሀላፊነት የሚሠማው አካል ማጣራት ቢያደርግ በቂ መረጃ ማግኘት ይችላል፡፡
በምስሉ የሚታዩት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱት አርሷደሮችና ህፃናት ልጆቻቸውን ነው!