>

ምክር ለጠቅላይ ሚንስትሬ ...!!! (ዘመድኩን በቀለ)

ምክር ለጠቅላይ ሚንስትሬ …!!!

ዘመድኩን በቀለ

… ጡረተኛ ነፍሰ በላ የህወሓት ቅጥቅጥ ካድሬ ሁላ ዲፕሎማት… አምባሳደር አድርገህ ሹመህ… የሃይስኩል መምህር ሁሌ ምክትል የሆነም ሰው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አድርገህ ሹመህ… በተፈጥሮው ገበሬ እና ሲፈጥረው ሚኒሻ ሆኖ የተፈጠረ ሰው የክልል ፕሬዘዳንት አድርገህ ሹመህ… በዲፕሎማሲ መስክ ጥርሳቸውን የነቀሉትን ጎምቱ ስመጥር ዲፕሎማቷን ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን ደግሞ የሟቾቹ ፕሬዘዳንቶች የመለስ ዜናዊ፣ የዶር ነጋሶ ጊዳዳ እና የመቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን አልጋ ወርሰው እንግዳ ሲሸኙና ሲቀበሉ እንዲውሉ የቤተ መንግሥት ጡረተኛ አድርገህ ስታበቃ መጨረሻ ላይ እንዲህ ባታዝን ነበር የሚደንቀው።
… ደግሞስ ከየጂም ቤቱ ስፖርት ስትሠራ ያገኘሃቸውን ሞዴላሞዴል በሜካፕ ብዛት ሰው የሚመስሉ… አንተን ከማምለክ ውጪ ሌላ ሥራ የማይሠሩ የተለጎሙ ወይዛዝርትን በየቦታው ሹመህ ስታበቃ… የሃገሪቱን በብድር እና በእርዳታ የተገኘ ብር በድግስ… በቢሮ እድሳት… በፓርክና በመዝናኛ ግንባታ ስም የትም ስትበትነው ከርመህ… ገበሬ ሲታረድ… እህል ከማሳም፣ ከጎተራም ሲቃጠል ጮጋ ብለህ ከርመህ… ብሔራዊ እርቅ ፍጠር… እንደ አዋቂ… እንደ ትልቅም ሰው ሁን ስትባል… ተው ኧረ ተው ኧረ ተው አንተ ሰው የ3ሺ ዘመን ሥርዓተ መንግሥት ያላትን ሃገር በጩጬነት ዘመንህ የመምራት ዕድሉን ስላገኘህ በአግባቡ ምራ… እንድታድግም ሁን ስትባል… አንተ ግን የሃሰተኛ ነቢያቱን የማይደርስ ትንቢት አምነህ… የደጋጎቹን ኢትዮጵያውያን ምክር አልሰማ ብለህ ስታበቃ ይሄ ውርደት ባይገጥምህ ነበር የሚደንቀው። ኮሎኔል ነኝ፣ ዶክተር ነኝ ስትለን መቼ? እንዴት? በየት በኩል? ወላጅ አምጣ? ምስክር ቁጠር ሳንል የነገርከንን ሁሉ አምነን ተቀብለን ስናበቃ መካድህ ሳያንስ ጠላት አታብዛብና ኦቦሌሶ።
… ፌስቡክ ላይ የምትፖስተውን ፖስት እየተከታተሉ…  ልክ እንደፍቅረኛህ… እንደሚስትህ እንደ ወ/ሮ ዝናሽ እንደውዷ ባለቤትህ… የእኔ ውድ፣ የእኔ ቆንጆ፣ የእኔ ስጦታ፣ ማሬ… ሆዴ… አንጀቴ… ጉበቴ… ኩላሊቴ… ምንጥስዮ ቅብጥርስዮ የሚሉህን አናኒመስ ጋለሞታ የፌስቡክ ላይክ ኮመንት አቅራቢ ፈዳላዎችን እህ ብለህ ሰምተህ… እንደ አድናቂ… እንደ እውነተኛም ዜጋ፣ እንደ ህዝብም ቆጥረህ… 120 ሚልየን ህዝብን ሳይሆን የ3 ሚልየን የፌስቡክ ላይ የጦዘ አድናቂ ጭብጨባ በልጦብህ ያለ እኔ አዋቂ ላሳር ስትል ከርመህ አሁን ቀን ባይጨልምብህ ነበር የሚገርመው። አዝማሪ አዝማሪ ነው። የተዘጋ ጭፈራ ቤት ቢያስከፍት እንጂ እግዚአብሔር የዘጋውን በርማ አያስከፍትም።
… እነ ታዬ ደንደአን የመሰለ በጥራቃ… እነ ሽመልስ አብዲሳን የመሰሉ እንደልቡ ተናጋሪ ፀረ ህዝብ፣ ፀረ አንድነት የሆኑ ነውረኞችን በህዝብ አንድነት ላይ እንዲያቀረሹ ፈቅደህ ስታበቃ… የህወሓት ካድሬ የቀድሞው የብአዴን አባሉን በፌክ መምህሩ በአውርቶ አደሩ በእነ ታዬ ቦጋለ ከንቱ ብርጥቅ ውዳሴ… በእነ መስፍን ፈይሳ ኦነጋዊ የይሁዳ ሰላምታ… የእነ ናትናኤል መኮንንን ኢዜማዊ የወንድኛ አዳሪ አክቲቪዝም እንደ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ድል ቆጥረህ… ተው ኧረ ተው አቢቹ የሚሉህን በሙሉ እንደ ጠላት ቆጥረህ… ግማሹን በጥይት… ግማሹን በዘብጥያ ከፊትህ ገለል አድርገህ ስታበቃ አሁን ባይጨንቅህ ነበር የሚገርመው። ከቪዛው ክልከላ በኋላ ከንቲባዋም ሚኒስከርት ለብሰው በየመድረኩ ጠዋት ማታ መታየታቸውም ቀረ።
… ለሚታረዱ ካህናት… ለሚቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ” ምን በወጣኝና ነው ይቅርታ የምጠይቀው ብለህ” ተብተህ… አባቶችንም አዋርደህ… አንገትም አስደፍተህ… በመላ ሃገሪቱ ነውጠኛ የሆነ ሥርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር አድርገህ ስታበቃ መጨረሻ ላይ ባትጨነቅ፣ ባትጠበብ ነበር የሚገርመው። የወጣት… የጎረምሳ ምክር… የሆዳም የደርግ… የኢህአፓ ትራፊዎችን… በድዳቸው እየበሉ… በዳዴ እየሄዱም በክፋት ተፀንሰው በክፋት በግድያ፣ በሴራ አድገው፣ በመጨረሻው የህይወት ዘመናቸውም ላይ ልጣቸው ተርሶ፣ ጉዳጋዳቸውም ተምሶ፣ መቃብራቸው ጫፍ ላይ ተቀምጠው አብዮታዊ ክፋታቸው የማይለቃቸውን ደውያን ፀረ ሃገርና ፀረ ህዝብ ሁላ ከየትም ቃርመህ አምጥተህ አማካሪህም አድርገህ ስታበቃ በመጨረሻ እንዲህ ባታዝን ነበር የሚገርመው።
… ተው አቢቹ የኢሳያስ አፈወርቂ ምክር አይጠቅምህም። ከዘንዶ ጋር ጓደኝነት ይቅርብህ። ኢሱ ይውጥሃል። ባይችል ያስውጥሃል። ኢሳይያስ 3 ሚልየን ህዝብ በባርነት እንዲገዛ በእነ አማሪካ የተፈቀደለት… የማይከሰስ የማይወቀስ… በማዕቀብ የኖረ… ሕገ መንግሥት… ምርጫ የማያውቅ… ወጣቱን አፍልሶ እንዲሰደድ አድርጎ ኤርትራን የአሮጊቶችና የሽማግሌዎች መጦሪያ መቄዶንያ ያደረገ ክፉ ሰው ነው። 100 ሚልየን ህዝብ ይዘህ 3 ሚልየን ህዝብ በቅጡ ማስተዳደር ከማይችል ሰው ጋር ወዳጅነት አትጀምር ስትባልም አልሰማ አልከን። መጨረሻህን ያሳምርልህ።
… ለድሀ ሉዓላዊነት ምን ያደርግለታል ብለህ በኤርትራ አስወረርከን…በሱዳን አስወረርከን… በዲፕሎማሲያችን ገጠር ከሌላት አንድ ከተማ ብቻ ካላት ከጅቡቲ ጋር ተደመርን… ሱዳን ናቀችን… ኬንያ ገላመጠችን… ሶማሊያ ሳቀችብን… ሽፈራው ሽጉጤን አምባሳደር አድርገህ ስትልከው ደቡብ ሱዳን ተደመመችብን… በሁሉም መስክ ድንኮች ሆንን… ወሬህ… ሰበካህ ከተሞችን ከውድመት… ዜጎችን ከሞት ከስደት አላድን አለ። ዝናብ አዘንማለሁ… መና አወርዳለሁ ብትልም አሁን የሚሰማህ ጠፍቷል። ኮቴ መናና… ዕድለ ቢስ… ኮቴ ደረቅም ሆንክብን። እናም ወንድምዓለም ውለታ ዋልልን። በጊዜም ንቃ። ሰበካህን… ፉገራ እና ድራማህን ትተህ ለሚችል ሰው አቅም ላለው ቦታውን ልቀቅ። እባክህ ታልቅ ውለታ ለሃገርህ ዋልላት። አጠገብህ ቁጭ ብለው አንተን ከፊት አፍ አድርገው የደም እንጀራ የሚበሉ ቡልጉዎችን አትስማቸው።
…”የነቀዘ ስንዴዋ እኮ ነው የሚቀርብን… አሜሪካ የራሷ ጉዳይ የሚሉ… ሱሉልታን አልፎ ገብረጉራቻ ኩዩ መሄድ የማይቻልበትን ሃገር እየመሩ “እኔ ቪዛ ምን ያደርግልኛል ሞያሌና ዓድዋ ከሄድኩ በቂዬ ነው።” የሚሉ… በጠላት በተከበበች ሃገር መሃል… ወደብ የባህር በር በሌላት ሃገር ላይ ተቀምጠው…ዓመታዊ በጀቷን በአሜሪካና በአውሮጳ እርዳታ ላይ አንጠላጥላጥላ በምትኖር ደሃ ሃገር ላይ ተከምረው… በደሃ ጉሮሮ ላይ የሚቀልዱ መሪዎችን ተሸክመህ እንዲህ ባታዝን ነበር የሚገርመው። ዓድዋን እየሰደቡ የጨነቀለት እኔ የምኒልክ ዘር ማለትም ያስተዛዝባል። ቪዛ ስትከለከሉ ስንዴ ተከለከልን ብላችሁ ህዝቡን ከአማሪካ ጋር አታላትሙ። በዚህ ዲፕሎማሲ አጠር ትእቢታችን…  ስንዴ መከልከላቸውም የሚቀር አይመስልም። ወዳጄ ይሄ ቁማር ዓባይ ማዶዎች ላይ እንደሠራችሁት እንዲህ ቀላል አይደለም። አማሪካም አውሮጳም ስለ ግድቡ እስከአሁን በግልፅ ተቃውመው አላወሩም። በእሱም አታሳብቡ። ኤርትራን አስወጣ… ሱዳንን ተመለሽ በላት… በኦሮሚያ ዐማራን ማረድ አቁም። የትግሬን ሰው መድፈር… መረሸን… በረሃብ መቅጣት አቁም። የተባልከው ይሄንኑ ነው። የሳቱት… ያልተረዱት ነገር ካለም ቀርቦ ማስረዳት ነው እንጂ በባዶ ሜዳ መፎግላቱ አይመስጥም። ወዳጄ የዚህ ዘመን ውጊያ እንደ ዓድዋ ዘመን አይደለም። የረቀቀ ነው። እናም በጥበብ… በአርቆ አስተዋይነት… በብልጠት ማሸነፍ እየተቻለ… ይሄ ጫታም የእኔ ዘመን ትውልድ… ርችት ሲተኮስ… ጎማ ሲፈነዳ አቅሉን ስቶ ፈርጥጦ ጉድጓድ የሚገባ የፌስቡክ ላይ አርበኛ ምክር መስማቱን ትተህ አዋቂዎችን ስማ። … በዚያ ላይ የብዙዎች ደም እጅህ ላይ ይጮሃል። ይሄንንም አትርሳ።
… ንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ አስቦ… አጼ ዳዊት ሞክረው… ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ አቅም አጥተው የግብጽ አብዮት ፈንድቶ… አሜሪካ የግብፅን ህዝብ እጁን ለመጠምዘዝ ስትል መለስ ዜናዊን ማታ ነገራው ድንገት ጠዋት ያስጀመረችውን… ለግብፅና ለሱዳን ጭምር ጠቀሜታው ከፍ ያለው የህዳሴው ግድብም ፈቃደ እግዚአብሔር ከሆነ ይገነባል። ህወሓትም የ40 ቀን ዕድል ፈንታዋ… ጽዋ ተርታዋ… እህል ውኃዋም ያለቀ ስለሆነ ከእንግዲህ ወዲህ በኢትዮጵያ ዙፋን አትመለስም። በእሱ በኩልም አትስጋ… አንተ ግን አንተ ኢትዮጵያን የምትወድ ከሆነ… አንተ ብቻ ሁልጊዜ እንደምትለው… እንደምትናገረውም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የምትፈልግ ከሆነም… ቢመር፣ ቢያንገሸግሽህም እንደ አንድ ዜጋ እንደወንድምም ልምከርህ… ሃገሪቷ እጅህ ላይ እንደጨው ሳትሟሟ፣ የአንተም መጨረሻ በአሳፋሪ ሁኔታ ሳይጠናቀቅ… ብሔራዊ እርቅ የሚፈጠርበትን መንገድ ፈልግ። በህዝብ መሃል የተዘፈዘፈውን የመለያየት ዐለት አንሣ… አይ ብለህ የእነ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን… የኢቲቪ… የዋልታና የፋናን ከንቱ ውዳሴ… የእነ አንዳርጋቸው ጽጌን… የእነ ፓስተር ዮናስን የነተበ… የዛገ ምክር እየሰማህ በዚሁ የምትል ከሆነ አሹ መርጫው የአንተ ነው። እግረመንገድህን ግን ባልንጀራህ … ኮሎኔል ጋዳፊ… እሳዳም ሁሴንም… ትዝ ይበሉህ። ጃንሆይንም አስታውሳቸው። ምክር ነው።
… ይሄም ይመዝገብልኝ።
Filed in: Amharic