>
5:18 pm - Saturday June 15, 6137

ለመሆኑ አገዛዞች ከጣሉብን ‹ማዕቀብ› ወጥተን እናውቃለን? (ከይኄይስ እውነቱ)

ለመሆኑ አገዛዞች ከጣሉብን ‹ማዕቀብ› ወጥተን እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ አህያ ጆሮ

ከይኄይስ እውነቱ


በአገራችን የአህያን ጆሮ ያሻው ሰው ይጎትተዋል፡፡ ባለቤት መሆን አይጠበቅም፡፡ ዘመነ ግርምቢጥ ላይ ስለምንገኝ ይሄም ተቀይሮ እንደሁ ወይም አህያ አትንኩኝ ብላ መራገጥም ጀምራ እንደሆነ አላውቅም፡፡ መቼም ለሰብአዊ ፍጡር መብትና ነፃነት በሌለበት አገር የአህያ ጆሮ ለምን ይጎተታል ብሎ ስለ እንስሳት መብት ለጊዜው የሚከራከር ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ የኢትዮጵያም ፖለቲካ እንደዛ የሆነ ያህል ይሰማኛል፡፡ ያሻው ሁሉ ፖለቲካን እንደ አህያ ጆሮ ይጎትታል፡፡ ከደቂቅ እስከ ልሂቅ የፖለቲካ ተንታኝ ሆኗል፡፡ ማይሙም፣ ፊደል የቈጠረውም ለሙያው ተራ ተርታ የሆነውም፡፡ ጊዜ መድረክ ያስገኘለት የዕውቀት ጦመኛ ካድሬውም ሆነ ዕድሜው በሕይወት ልምድ ያልለዘበው ጨቅላው ፖለቲካ ‹በላችነቱ› ከእኔ ወዲያ ላሳር ነው ሲል ይሰማል፡፡ እውነት ያገር ያለህ ብላ በምትጣራበት አገር ‹ተንታኙ› ሁሉ መዘባረቁ ሳያንሰው እውነትም መንገድም እኔ ብቻ ነኝ ማለቱ ደግሞ ችግሩን ወደ ዕብደትነት ከፍ ያደረገው ይመስለኛል፡፡

ባንፃሩም በመደበኛውም ሆነ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ራሱን የፖለቲካ ተንታኝ ብሎ የሰየመው አንዳንድ ‹‹ፖለቲከኛም› ጅምላውን ሕዝብ ፖለቲካ አታውቁም አልገባችሁም እያለ ተመጻዳቂ ግብዝ ሆኗል፡፡ የገባቸው ‹ምሁራኑ› ምን እያደረጉ እንደሆነ ባናውቅም፡፡ ይህንን ስል ላገር አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም፣ ለሕዝብ አብሮነት፣ ላገራዊ የህልውናና ጸጥታ ሥጋት፣ ለብሔራዊ ፖሊሲ፣ ለብሔራዊ መግባባት፣ ለዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ፣ ወዘተ. የሚረዳ ሙያዊ ትንተናን ማለቴ እንጂ እንደ ግለሰብ ማንም ሰው ስለ አገሩም ሆነ ስለ አስተዳደሩ የራሱ ሃሳብና አስተያየት አለው፡፡ ያንንም በሥርዓት ማንፀባረቁ ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው፡፡ ይህንን መብቱን ሥራ ላይ ለማዋል የፖለቲካ ሳይንቲስት መሆን አይጠበቅበትም፡፡ እኔም በዚህ በኋለኛው መንፈስ ነው ስለ አገሬ እና ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ህልውና፣ ስለ ተገፋው ወገኔ እና ስለ ራሴ የመኖር ዋስትና አሳስቦኝ ብቅ ጥልቅ እያልሁ አስተያየት የምጫጭረው፡፡

በሕወሓት የበላይነት የጐሣ ሥርዓት ተክሎ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ የሲዖል በርን በርግዶ የከፈተውን ቀዳማዊው ኢሕአዴግን ዘመን ወደ ኋላ ትተን በኦሕዴድ የበላይነት ኢትዮጵያን  ገሃነመ እሳት እያደረገ ባለው ካልዓይ ኢሕአዴግ ሦስት የሰቈቃ ዓመታት የታየው ጥላቻ፣ ጭካኔና ጥፋት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከዓላማም ከይዘትም አኳያ ሙሉ ንጽጽር አይገኝለትም፡፡ አሁን ላይ ዓላማው እንደ ፀሐይ ብርሃን ፍንትው ብሎ የሚታየው አገዛዝ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንዳልቆመ ታውቋል፡፡ የአገዛዙ የመጀመሪያውን ዓመት ‹የማርያም መንገድ› በመስጠት ብናልፈው እንኳ ከዛ ወዲህ ባለው ጊዜ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የገባንበት ማጥ ሕጋዊና መዋቅራዊ መሆኑን ገልጸን ይበጃል ካልነው መፍትሄ ጋር በቶሎ እንዲታረም ስነወተውት ቈይተናል፡፡ ይሁን እንጂ የአገዛዙ ሃሳብ ካሳባችን፣ መንገዱ ከመንገዳችን እንዳልሆነ የተረዳን ኢትዮጵያውያን ሃሳቡም፣ ትችቱም፣ ምክሩም ሆነ ተግሣፁ ይቀርብ የነበረው ለውስጥ ጠላት መሆኑን ስናውቅ ሁናቴው በእጅጉ ማስደንገጥ ብቻ ሳይሆን ቀቢፀ-ተስፋ ውስጥ የሚከት ዓይነት ሆኖብናል፡፡ 

ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሚገኙ ለአገዛዙ ያደሩም ሆነ ‹ነፃ› የሆኑ መደበኛም ሆኑ ማኅበራዊ ሜዲያዎች በዕለት ጉዳዮች ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ በዋናነት አረመኔያዊው አገዛዝ በገሃድና በኅቡዕ ከሚፈጽማቸው አገራዊ ጥፋቶች ሕዝብን ለማዘናጋት ይረዱኛል ብሎ በሚወረውራቸው አጀንዳዎች መነታረኩ ቀጥሏል፡፡ እውን የኢትዮጵያ አንገብጋቢ ችግር የውሸት ምርጫው፣ የአሜሪካ ማዕቀብ ወዘተ. ነው? እውን ጊዜው የውስጥንም ሆነ የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ወግነን እሰጣ አገባ የምንገባበት ነው? የተሸከፈ ‹ቤት› ቢኖረን፣ ‹ቤተሰባችንን› በሥርዓትና ባግባቡ ብንመራና ብናስተዳድር የውጩን ሥጋት በእጅጉ መቀነስ አይቻልም? ቢመጣስ ባንድነት በኅብረት የምንቋቋመው አይሆንም? እውን ምዕራባውያኑ መንግሥታት ቋሚ ወዳጅና ቋሚ ጠላት አላቸው? ውሳኔአቸውም ሆነ የሚወስዱት ርምጃ ጥቅማቸውን መሠረት ያደረገ አይደለም? ወያኔን በኢትዮጵያውያን ላይ ለ27 ዓመታት የጫነብን ማነው? የወያኔ ወራሽ የሆነው ኦሕዴድ/ብል(ጽ)ግና ከአውራሹ እጅግ ቢከፋ እንጂ ያንሳል? ‹ሌላ አገር ዓላሚ፣ ሌላ ሕዝብ› ፈላጊ አገዛዝ መሆኑን ለምን እንዘነጋለን? እኛ ስለ ማዕቀብ ስናወራ በሉዐላዊ ግዛታችን ዜጎቻችንን እየገደለ፣ ሀብትና ንብረት እየዘረፈና እያወደመ እንግሩን አንፈራጦ የተቀመጠ  የጎረቤት ጠላት የለም? ከዚህ የበለጠ የሉዐላዊነት መገሰስ አለ ወይ? ኢትዮጵያን ጠላት አድርጎ በታሪካዊ ጠላቶቻችን እገዛ ተገንጥሎ ራሱን ማስተዳደር ያቃተው የኤርትራ አገዛዝ/ሻእቢያ አገራችን ገብቶ የትግራይ ወገኖቻችንን ሲጨፈጭፍ የሉዐላዊነት ጉዳይ ለምን አልተነሣም? ለመሆኑ በዚህ ባሳለፍነው ሠላሳ ዓመታት የአገርም ሆነ የሕዝብ ሉዓላዊነት በተግባር ነበር? ዛሬስ በተግባር አለ? በኢትዮጵያና በሕዝቧ ስም በጉልበት የተሰየመውና በተቈጣጠረው ኃይል ምክንያት በውሸት ምርጫ አመኸኝቶ በጉልበት ለመቀጠል እየተዘጋጀ ያለው አገዛዝ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያለአንዳች ተጠያቂነት እገዛዋለሁ የሚለውን ሕዝብ በማንነቱና በሃይማኖቱ በጅምላ ሲጨፈጭፍና ሲያስጨፈጭፍ፣ በሚሊዮኖች ሲያፈናቅል፣ ተቋማትን ሲያፈርስ፣ ግዙፍ መንግሥታዊ ዝርፊያ ሲፈጽም፣ የሕዝብ ሀብት ሲያባክን፣ ባጠቃላይ አገር ሲያጠፋ በሚገባ መጠን ጮኸናል? እምቢኝ አሻፈረኝ ብለናል? ለምን ግብዞች እንሆናለን፡፡ ለምን ሁሌም የአገዛዞች ፕሮፓጋንዳና ቆሻሻ ፖለቲካ ሰለባ እንሆናለን? ለመሆኑ መቼ ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተፈራረቁበት አገዛዞች በተለይም ከቀዳማዊውና ካልዓይ ኢሕአዴግ ‹ማዕቀብ› ነፃ ሆኖ የሚያውቀው? የመብትና ነፃነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ማዕቀብ ላልተወሰነ ጊዜ ተጭኖብን እየኖርን አይደለም እንዴ? ለባርነት የውስጥና የውጭ አለው እንዴ?

የአገራችን ህልውናና የሕዝባችን ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ዋና ምንጩ ምንድነው? ቀድሞ ሕወሓት አሁን ደግሞ ወራሹ ኦሕዴድ የሠለጠነበት አገዛዝ አይደለም? የውጭ ኃይሎች ናቸው የሚል ያላዋቂ ንግግር እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡ ጎበዝ! በጐሣ ከፋፍሎና ለያይቶ ለመግዛት በፈቀደ ደካማ ‹ቤት› ውስጥ እንኳን ኃያላኑ ‹ደካማዋም› ሱዳን ገብታለች፡፡ የሚጠጣ ውኃና ትኩስ ፍራፍሬ ከኛ የምታገኘው ጅቡቲ እንኳን አፏን እያላቀቀችብን ነው፡፡ ምን ያስደንቃል? ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ ነውና፡፡ የፉክክር ቤት እኮ ዖና ነው፡፡ ዖና ቤት ደግሞ የማንም መፈንጫ ነው፡፡ የወደቀ/የከሸፈ ‹መንግሥት› ይዘን ስለ ምዕራባውያን የምናደርገው ንትርክ መሳለቂያ ከመሆን አይዘልም፡፡ ይልቁንስ ቀንአዊነቱ ካለ፣ ቊጭቱ ካለ፣ አገራችንን እና ሕዝባችንን ከልባችን የምንወድ ከሆነ በቅድሚያ ‹ቤታችንን› እንሸክፍ/እናስተካክል፡፡ እንደ መርግ የተጫኑብንን ዐበይት ችግሮች ከላያችን ላይ አሸቀንጥረን ለመጣል ባንድነት እንነሳ፡፡ በቅድሚያ አገዛዙ የጣለብንን ሁለንተናዊ ‹ማዕቀብ› ለማንሳት እንታገል፡፡ ያኔ ከውጭ የሚመጣውን አደፍ ጉድፍ አጥርተን ማየት እንችላለን፡፡

Filed in: Amharic