>

"አድዋም ይሁን አዳማ የሚኬደው በአሜሪካ መልካ ፍቃድ ብቻ መሆኑን ለዛ ሰው ንገሩት...!!!" (አዋድ መሀመድ)

No Fly Zone !!!
“አድዋም ይሁን አዳማ የሚኬደው በአሜሪካ መልካ ፍቃድ ብቻ መሆኑን ለዛ ሰው ንገሩት…!!!”
አዋድ መሀመድ

ሽመልስ አብዲሳ መቼ ለት ምንድነው ያለው? እኔ ከአድዋ ይሁን ከአዳማ አልፌ ስለማላውቅ የአሜሪካ የበረራ ማዕቀብ አይመለከተኝም ነገር ነው ያለው? አይ ሽሜ! ይሄን ሲል ማን ትዝ እንዳለኝ ታውቃላችሁ? ኢራቅ ናት። ንግግሩን እንደሰማሁት ወዲያው ወደ ጭንቅላቴ ምን እንደመጣ ታውቃላችሁ? አሜሪካ በኢራቅ የገዛ የአየር ክልሏ ጥላ የነበረው የ No fly zone (ከበረራ ነፃ ቀጠና) ክልከላ ነው።
አሜሪካ በገዛ አገራችን፣ በራሳችን ሰማይ፣ በራሳችን የአየር ክልል በአይሮፕላንም ሆነ በሄልኮፕተር እንዳንበር ልታደርገን እንደምትችል ነው ያስታወሰኝ፣ ከፈለገች። ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከአዲስ አበባ ደሴ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አዋሳ እንዳንበር ልታግደን የሚያስችል ኋይሉም ጉልበቱም እንዳላት ነው። እነ አብይ በገዛ አገራቸው እነ ሽመልስ በገዛ ክልላቸው ከቦታ ቦታ በአየር እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ መሬት ለመሬት እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ አንዳንዴ በባጃጅም ልትወስናቸው እንደምትችል ነው። ወደ አድዋም ሆነ ወደ አዳማ በየብስ በመኪና ካልሆነ በስተቀር እንዳይዘዋወሩ የማድረግ ኋይል አሜሪካ አላት። ይሄን ደግሞ No Fly Zone ብላ ከ 1991 እንደ ፈረንጆች እስከ 2003 ድረስ ለ 12 አመት፣ በኢራቅ ሰሜናዊና ደቡባዊው ግዛቶቿ ላይ የበረራ ማዕቀብ በመጣል አሳይታለች። ይሄ የሽመልስ አብዲሳ የጅል ቀልድ ያስታወሰኝ ይሄንን ነው፡ አሜሪካ በኢራቅ የገዛ ሰማይዋ ላይ ለጥፋው የነበረውን “በዚህ በኩል መብረር አይቻልም” ን ታቤላ ነው።
አሜሪካ እንግሊዝና ፈረንሳይ በጋራ በመሆን በኢራቅ መንግሥት ላይ በገዛ የአገሩ ሰማይ፣ በሰሜን ኩርዶችንና በደቡብ ሺአዎችን ከሳዳም የጦር ጀትና ሄሊኮፕተሮች ለመከላከል በሚል በ 1 March 1991 የበረራ ማዕቀብ ጥለው ነበር። የሰሜኑን አየር ከላይ የደቡቡን ከታች ቆርጠው የኢራቅ መንግሥትን ዳግመኛ በእነዚህ አካባቢዎች እንዳይበር፣ ከበረረ በገልፍ፣ በሳዑዲና በቱርክ ከሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ቤዞች በሚተኮስ ክሩዝ ሚሳዬልና አየር መቃወሚያ አይሮፕላኖቹን እንደሚመቱ በማስጠንቀቅ ያንን ተከትሎ ሊፈጠር ለሚችለውም ሙሉ ሀላፊነቱን የኢራቅ መንግሥት በዋናነት እንደሚወስድ በማስፈራራት የበረራ ማዕቀቡን በኢራቅ ጥለው ነበር። በዚህም የተነሳ የኢራቅ ባለስልጣናትም ሆኑ ሲቪሊያኖች በአይሮፕላን ከአንዱ የአገራቸው ክፍል ወደ ሌላው የአገራቸው ክፍል እንዳይሄዱ ታግደው ነበር።
ከ 12 አመት የበረራ ማዕቀብና ማሸት በኋላ ደግሞ በ 2003 እ. ኤ.አ ማለት ነው፣ አሜሪካና ተባባሪዎቿ የመጨረሻውን ጦርነት በኢራቅ ላይ በመክፈት አገሩን አፍርሰው፣ መንግሥቱን አስወግደውና ሕዝቡን እንዳልነበር አምሰው 200 አመት ወደኋላ ሊመልሷት ችለዋል።
ምን ለማለት ነው፣ አይበለውና ነገ ከነገ ወዲያ ትግራይን ከኢትዮጲያና ከኤርትራ የጦር ጀቶችና ሄሊኮፕተሮች ለመጠበቅ በሚል ሰበብ አሜሪካ የሰሜኑን የሀገራችንን አየር ከበረራ ነፃ ቀጠና በማድረግ ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሽመልስና አብይ እንዳይበሩ ብታደርግ፣ ከልካይ የላትም። ትችላለች። ሽመልስንና አብይን ሲቪሊያኑንና ወታደሩን በገዛ አገራቸው በራሳችን ሰማይ እንዳንንቀሳቀስ በማድረግ ላይ ጉልበት አላት። በቃ፣ የዛኔ የምንጎዳው እንደ አገር የምንጎዳው እንደ ህዝብ ይሆናል። ከዛ በኋላ ሊያፈርሰን የሚችል መቀመቅ የመግባት ዕድላችን ይፈጥናል ማለት ነው።
ይልቅ ይልቅ አሜሪካኖች አሁን የጀመሩትን ነገር በቀላሉ እንደማይተውና ወደ ሌላ ወደ ባሰ ሁኔታ ሊወስዱት እንደሚችሉ በመገንዘብ፣ ሽመልስም ሆነ አብይ ታዬ ደንደአም ሆነ ደመቀ መኮንን የማይሆን ቀልድ ከመቀለድና የማይመስል ድንፋታ ከመደንፋት ቢቆጠቡና እየመጣብን ካለው መአት ማምለጫ መንገድ ላይ፣ መመከቻው ላይ ጠንክረው ቢሰሩ ይሻላቸዋል። የአገራችንንና ህዝባችንን ህልውና ማስቀጠያ ዘዴ በመዘየድ ላይ እንደ መንግሥት ቢዚ ቢሆኑና ነገሮችን ከአሜሪካ በኩል ሊያባብሱ ከሚችሉ የባዶ ቃላት ትንኮሳዎች ቢጠነቀቁ የሚበጅ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic