>

ለአሜሪካ መንግሥት ሰብዓዊ ጣልቃገብነት ለኤምባሲው የተጻፈ ሠላማዊ ሀሳብ! (አሰፋ ሀይሉ)

ለአሜሪካ መንግሥት ሰብዓዊ ጣልቃገብነት ለኤምባሲው የተጻፈ ሠላማዊ ሀሳብ!

አሰፋ ሀይሉ

ጉዳዩ፡- በኢህአዴግ ወንጀለኛ መሪዎች ላይ አሜሪካ ስለጣለቻቸው ዕቀባዎች ለማመስገን፣ እና የዘነጋቻቸውን አሳሳቢ ነጥቦች ለማስታወስ በአስተያየት የተላላለፈ መልዕክት፤
አሜሪካ በኢህአዴግ ባለሥልጣናት ላይ በቅርቡ የጣለቻቸውን የጉዞ ክልከላ ማዕቀቦች አጠናክራ መቀጠል አለባት፡፡ ፓርላማውን 100% ተቆጣጥሮ ራሱን መንግሥትም፣ ፓርላማም፣ ዳኛም ባደረገው በሰው-በላው የኢህአዴግ ገዢ መንግሥት ላይም የጣለቸውን የገንዘብ ማዕቀብም ይበልጥ ማጥበቅ ይኖርባታል፡፡
በተለይ ግን እጅግ አንገብጋቢ የሆነ ከአሜሪካ የሚጠበቅ ተግባር አለ፡፡ እነዚህን ሁሉ አሜሪካ የምትጥላቸውን ማዕቀቦች ሰው-በላዎቹ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በተቋማትና በመንግሥት ጥላ ሥር ስለሚከለሉ በግላቸው ብዙም የሚያስጨንቃቸው ሥጋት አያገኛቸውም፡፡ ስለሆነም የአሜሪካ መንግሥት በአስቸኳይ ዝግጅቱን አጠናቅቆ፡-
1ኛ/ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በአብይ አህመድ አሊ ላይ፣
2ኛ/ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በደመቀ መኮንን ሐሰን ላይ፣ እና
3ኛ/ በጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማጆር ሹሙ በጄነራል ብርሃኑ ጁላ ላይ
ዘ ሄግ በሚገኘው ዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት (አይሲሲ) በፍጥነት ክስ መሥርታ እያንዳንዳቸውን ለፈጸሙት ወንጀል በግላቸው እንዲጠየቁ ልታቆማቸው ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው የሰውን ዘር እየጨፈጨፉ ያሉት የኢህአዴግ ሰው-በላዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ የሚችሉት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት በማዕቀቡ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያልሰጠውን በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሁለት ክልሎች በገዢው ፓርቲ የኦሮሚያ ቱባ ባለሥልጣናት አማካይነትና፣ በእነ አብይ አህመድ አሊ ቀጥታና ተዘዋዋሪ ተሳትፎ አማካይነት፣ በተጨፈጨፉትና በተፈናቀሉት በሺህዎች በሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ስለፈጸሙት ወንጀል አስቸኳይ ማጣራቶችን በማድረግ፣ ተጨማሪ የወንጀል ክሶችን እጃቸው በዘር ጭፍጨፋው ላይ ባስገቡ እና በዓለማቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ የተጣለባቸውን  የሰውን ልጅ የመጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡት የኦሮሚያ ባለሥልጣናት ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችንና ዓለማቀፍ የወንጀል ክሶችን እንድታቀርብ እንጠይቃለን፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ብሔሮች ላይ የሚፈጸመውን የሀይል እርምጃ እያወገዘ፣ በብሔር አማራ በሆኑት ላይ የሚፈጸምባቸውን ጭፍጨፋና ማፈናቀል ግን እንዳላየ እያለፈ፣ ለሁሉም የሚታመን ገለልተኛ ሰብዓዊ አካል ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህንኑ ተገንዝቦ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩንና የወሰደውን አቋም እንዲፈትሸው እንጠይቃለን፡፡
በመጨረሻም በገዢው የኢህአዴግ መንግሥትና ተቃዋሚ መስለው ከጎኑ በተሰለፉ አጋር ድርጅቶቹ በኩል ‹‹ምዕራብ ትግራይ›› በሚል ለዓለም እየተሰራጨ ያለውና፣ የአሜሪካንንም መንግሥት ያሳሳተው መረጃ፣ እና በዚያም የተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ በአሜሪካ መንግሥት በኩል የተላለፈው የአማራ ሀይሎች ከምዕራብ ትግራይ መውጣት እንዳለባቸው የተላለፈው ቀደም ያለው ማሳሰቢያ፣ የአካባቢውን አስተዳደር በተለመከተ በመሬት ላይ ያለውን እውነተኛ ማስረጃና ጭብጥ ተገቢና ሚዛናዊ በሆነ ገለልተኛ መነጽር ያላገናዘበ በመሆኑ፣ የአሜሪካ መንግሥት በጉዳዩ ላይ የወሰደውን አቋም በድጋሚ እንዲያጤነው እንጠይቃለን፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት መሻሻል ያለባቸው መሠረታዊ የሆኑ የልዩነት ነጥቦች በስተቀር፣ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ የሚያስጨንቃቸውና በቀጥታ የሚመለከታቸው ዓለማቀፍ ሰብዓውያን ተቋማት ጭምር በኢህአዴግ ሰው-በላ መሪዎች የሚፈጸውን ግፍ በዝምታና ከዳር ሆኖ መመልከትን በመረጡበት በዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ መከራ የግፍ ጣራውን በነካበት አስከፊ ወቅት ላይ፣ የአሜሪካ መንግሥት የሰው ልጆች ሰብዓዊ አያያዝ፣ ዲሞክራሲና የሀገራችንንና የቀጣናው ሠላም አሳስቦት በቀጥታ በጉዳዩ ላይ እጁን በማስገባት የወሰደው ሰብዓዊ እርምጃ በእጅጉ ሊደነቅና ሊበረታታ የሚገባ እርምጃ ነው፡፡
እናመሠግናለን አሜሪካ፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ፈጣሪ አሜሪካንን ይባርክ፡፡
Filed in: Amharic