“እንደእናቴ ሣይሆን እንደሚስቴ አውለኝ” ብለህ ጸልይ!
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ያልተቀሰረ ጣት፣ ያልተሰበቀ ጦርና ያልተቀባበለ ጠበንጃ የለም፡፡ ሰውን ምን እንደነካው ግን አላውቅም – ይህን አደገኛ የነገሮች ግጥምጥሞሽ መረዳት አልቻለም ወይንም አልፈለገም፡፡ ሁሉም ሲራወጥ የምታየው ነገ እምን ላይ ቁጭ ብሎ ሊበላው እንደሚችል ግልጽ ባልሆነልኝ ሀብትና ገንዘብ ክምችት ላይ ነው፡፡ ፍቅረ ንዋይ ገዝቶን እሱን ማምለክ ይዘናል፡፡ ግዴላችሁም የዚያ የጅል እረኛ ነገር ሳይደገም አይቀርም፡፡ እኔና መሰሎቼ ብዙ ስንጮህ ከረምን፤ “መጮህ ልማዳቸው ነው” ተብለንም በተለይ አሁን አሁን ሰሚ ጆሮም አጣን – አዳሜ የጆሮ ታምቡሩን በጥጥ ወትፎ በሥጋ ገበያ ሩጫውን እያቀለጠው ይገኛል – መልካም ሩጫ፡፡ እረኛውስ በመንደርተኛው ሊዝናና ነው ያን “በጎቼን ቀበሮ ፈጀብኝ ኑና አስጥሉልኝ” በማለት ከአንዴም ሁለት ሦስቴ የውሸቱን አላግጦባቸው ሲያበቃ በመጨረሻው ቀበሮዎች መጥተው በጎቹን ሲገሸላልጡለት የእውነቱን ቢጮህ የሚሰማው አጥቶ ባዶ እጁን ወደ ቤቱ የገባው፤ የእኔን መሰሎች ጩኸት ግን የምር ነበር፤ አሁንም የምር ነው፡፡ “ነገ ቤት ይቃጠላል ብያለሁ” ያለቺው ያቺ ዕብድም ምንም እንኳን አቃጣይዋ ራሷ ብትሆንም የሰጠችው ማስጠንቀቂያ ግን ችላ ሊባል የሚገባው አልነበረም፡፡ እንግዲህ አውቆ የተደበቀን ምንም ማድረግ አይቻልምና ነገ ምን እንደሚያመጣብን በትግስት መጠበቅ ነው፡፡
የሚወራውና የሚደረገው ሁሉ የውሸትና ህልም እልም ቢሆን ደስታችን ወደር ባልነበረው፡፡ ግን ኢትዮጵያን የተጠናወታት የአጋንንት መንጋ ልክ እንደውኃ እያሣሣቀ መርከቧን ሊያሰጥም ተቃርቧል፡፡ ዲያቢሎስ በተፈጥሮው መለኛ ነው፡፡ እጅግ ሲበዛ ብልጥ ነው፡፡ የሚልክብህ ሰው ከአንተ ልኬት በዕጥፍ ይበልጣል – በዕውቀትም በሥልትም በሸርና በተንኮልም፡፡ የማይረባ ሰው ቢልክብህ በቶሎ እንደሚሸነፍና ከዓላማው እንደሚናጠብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ስለሆነም እንደምሣሌ ነው የምልህ – ጳጳስ ከሆንክ ፓትርያርኩን፣ ቀሲስ ከሆንክ ሊቀ ጳጳሱን፣ ዲያቆን ከሆንክ መሪጌታውን፣ ባለቢኤ ከሆንክ ባለማስተርሱን፣ ባለማስተርስ ከሆንክ ባለፒኤችዲውን … አሰልጥኖና አሰይጥኖ ይልክብሃል፡፡ ያኔ በአፍዝ አደንግዙ ትተበተብና ፀጥ ረጭ ስትልለት ያሻውን እንድትሆንለት ያደርግሃል፡፡ የመጨረሻህ መጨረሻ ግን የርሱን መንግሥት ካለተቀናቃኝ መውረስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውም ይሄው ነው፡፡ አጅሬ ሁሉንም በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ኢትዮጵያን ጢባጢቤ እየተጫወተባት ነው፡፡ እኛም ተባባሪዎቹ ሆነናል፡፡ ባለቤተ ክርስቲያንም በለው ባለ “ቸርች”፣ ባለመስጂድም በለው ባለምኩራብ … ያ ፌዘኛና አስመሳይ ተንከሲስ በፍቅሩና በቡገታ በተገኘ ንዋዩ ያላማለለው የለም፡፡ የሰው ሁላ መፈክር “ከግራኝ አህመድ አቢይ አመራር ጋር ወደስተፊት! ንቅድሚት! Fuuldhuurreetti (ፉልዱረቲ)!” ሆኗል፡፡ መንጌና መለስ ዘር ተካን ይበሉ፡፡ ወያኔ አልሞትኩም ብላ ትኩራራ – ፈጣሪዎቹን ሳይቀር የማይምር እሳት ልጅ ተክታ ይሄውና ለሌሎች በቆፈረችው ጥልቅ ጉድጓድ ራሷም ሰተት ብላ እየገባችበት ነው፡፡ ጋሽ ፀግሽ ጨርሶታል – “አባቴስ ወንድ ወለድኩ ይበል! ወለድኩ ይበል ይልቅ በቃ፡ በምላሱ እሚያመረቃ! ወኔው በአረቄ እሚነቃ ልቡን በቧልት እሚደቃ” በማለት፡፡
ለማንኛውም የሚባለው ሁሉ ውሸት በሆነልን፡፡ እንጂ እንደሚባለውማ በግብጽ ፊታውራሪነት ያልተጠነሰሰና ያልተጠመቀ የእንክርዳድ ጠላና ያልተጣለ የመከራ ጠጅ የለም፡፡ የቀረን በጀመርነው በነገድና በጎሣ እንዲሁም በሃይማኖት ጎራዎች ተከፋፍለን በየዳሳችንና በየአውራጅ አውራጃችን ድግሱን መኮምኮም ብቻ ነው፡፡ ቤንሻንጉልና መተከል ወደሱዳን ሊገባ ነው፡፡ ጋምቤላና አካባቢው ወደ ደቡብ ሱዳን ሊጠቃለል ነው፡፡ ስማ ዝም ብለህ እንግዲህ፡፡ ኦሮሞው በኦሮሙማ ፍልስምናው የቻለውን ያህል ከኢትዮጵያ ግዛቶች ቦዳድሶ ያንኑ አሜባ የሚመስል ካርታውን ሠርቶ ለዓለማቀፍ ፀረ ኢትዮጵያ የኢሉሚናቱ ኃይላት በማቅረብ የ“ይመችህ፤ go ahead!” የሚል ፈቃዳቸውን ለማግኘት ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በዚህ ሂደት ግን ሶማሌንና አፋርን በተወሰነ ደረጃ ኦሮሙማው ይውጣቸዋል፡፡ ከሚተርፈው የአፋርና የሱማሌ ክልሎች የተወሰኑት ወደ ሶማሊያና ኤርትራ ይጓዛሉ፡፡ ደቡብ በኦሮሙማ ከተበላ ቆዬ፡፡ ሐረርና ድሬዳዋም እንደዚሁ፡፡ ፌዴራል ተብዬው መዋቅር በኦሮሙማ ከተሰለቀጠ ሦስት ዓመታትን ደፍኖ ወደ አራተኛው እየገሰገሰ ነው፡፡ ከፈለግህ የየመሥሪያ ቤቶቹን ግብብዳ ሹማም(ን?)ት ታዘብ – ተላላኪ ምስለኔዎችን ትተህ፤ ባለሥልጣኑ ሁሉ ከድሪባ ጉርሜሣ እስከ ጫልቱ መገርሣ ያው አክራሪ ኦሮሞና አፍቃሬ ኦሮሙማ ነው – ከሐጎስ ወልዳይ እስከ አብረኸት ደበሳይ ወያኔዎች እንደነበሩት ማለት ነው በዘመነ ትህነግ፡፡ ኢትዮጵያ በስም እንጂ በተግባር ከጠፋች ቆየች፡፡ ስም ደግሞ በቀላሉ አይሞትም፡፡ ትግራይ በጦርነትም በርሀብም ከአማራ ጋር ባለ ግርንጭትም አካማሌ ስለሆነች የኦሮሙማ ሥጋት አትሆንም – የዝኆኖች ጠብ ለሣር ቅጠሎች እንደሚተርፍ ሁሉ የሆዳም “ልሂቃን” በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ግጭትና ቅራኔ ለተራው የትግሬና አማራ ዜጋ የኅልውና ችግር ደቀነበት፡፡ እንደሚሰማውማ እንዲያውም ከፊል ትግራይ ወደኤርትራ ተሸጦ ታላቋ የምሥራቅ አፍሪካ ሲንጋፖር ማናት ኤርትራ በአዲስ መልክ ትመሠረታለች፡፡ አማራ ከኢሱና ከአህመድ ግራኝ የምትሰጠውን ቅንጥብጣቢ ግዛት ይዞ እንደልማዱ በኦሮሙማ አሽከሮች በነአገኘሁ ተሻገር የማይቀርለት ሞቱን ያስተናግዳል፡፡ ዐረቦች በአራቱም አቅጣጫ ይገባሉ፡፡ በፈራረሰችዋ ኢትዮጵያ ላይም ይሰለጥናሉ፤ ይምነሸነሻሉ፡፡ በአትክልት ተከላ፣ በመንገዶችና በቤተ መንግሥት ውበት እንዲሁም በመናፈሻ ሥፍራ ግንባታ ሥራዎች የተለከፈው ሰውዬም የማስመሰያ ካባውን አውልቆ የሎሌነት ተልእኮውን በድል በማጠናቀቅ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡ የተሤረው እንደዚህ እንደሆነ ይወራል፡፡ እንደሚስቴ አውለኝ ብሎ መጸለይ ታዲያ አሁን ነው፡፡ “ስሉስ ባዛውር” ብለህም ጸሎትህን አዳብረው፡፡
አንድ ባል ከቤቱ ውጪ አመሸ እንበል – በጣም አመሸ፡፡ ያኔ ሚስት ምን ታስባለች – እናት የሆኑ ጥሩ ሚስቶች መኖራቸው ወይም ሊኖሩ መቻላቸው በታሳቢነት ተይዞልኝ – “አሄሄ! ይሄኔ ከዚያች ከእንትና ጋር ዓለሙን እየቀጨ ነው እንጂ …. ከነዚያ አጋሰስ ጓደኞቹ ጋር እየበላ እየጠጣ የቤቱን አስቤዛ በአሼሼ ገዳሜ ሊጨርስ … ነው እንጂ” በማለት ትብሰከሰካለች፡፡ እናትስ? እናትማ “ወይኔ ልጄ! ካንዱ ጋር ተጣልቶ ገድለውብኝ ቢሆን ነው እንጂ …. አውሬ በልቶት ቢሆን ነው እንጂ … አደናቅፎት አንዱ ጉድባ ውስጥ ወድቆ ቢሆን ነው እንጂ እንዲህ አያመሽም ነበር”፡፡ ኢትዮጵያም እንደእናትየዋም እንደሚስትዮዋም ሳይሆን እንደፈጣሪ የሚያስብላት አዲስ እረኛ ይስጣት፡፡ ደግሞም አትጠራጠሩ – ይሰጣታል፡፡ ግን ግን ካለመጸለይ ይቀራልና እንጸልይ፡፡ ስንጸልይ ደግሞ ጠፍተው የሚያጠፉ የሃይማኖት አባቶችን አንይ፡፡ ሀገርን መቀመቅ የከተተው የነሱ ውስልትናና ንቅዘት መሆኑን ተረድተን የኛን ኔትወርክ እናጥብቅ፡፡
አዎ፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጭንቅ ላይ ናት፡፡ የጭንቀቷ ዋና መንስኤ ደግሞ በአብዛኛው እኛው ዜጎቿ ነን፡፡ በሚዘረጋልን ወጥመድ ሁሉ ዘው ብለን እንገባለን፡፡ የሰጡንን ሁሉ ሳናላምጥ የምንውጥ እጅግ ብዙ ነን፡፡ በዚያም ላይ ሀገራችንና ሕዝባችን ያለንበት ሁኔታ፣ የገባንበት አዘቅት፣ የተሰነቀርንበት የኅልውና አደጋ ፈጽሞ ሊታየን ያልቻልን ዜጎች እጅግ በርካቶች ነን፡፡ ተራውን ዜጋ ትተን የሦርያና የየመን ሀብታሞችና ዶክተር ፕሮፌሰሮች የደረሰባቸውንና እየደረሰባቸው የሚገኘውን መከራና ስቃይ ብዙዎቻችን ማሰብ አንፈልግም – ምናልባት እኛ ያ ዓይነቱ አደጋ አይደርስብንም ብለን አስበን ሊሆን ይችላል – ግን ስህተት ነው፤ ይደርስብናል፤ እኛ ምን ወይም ማን ስለሆንን? የዕልቂት ጥሩንባ በየደጃፋችን እየተነፋ እኛ ግን ምንም ሳይመስለን በነበረው ማርሽ እንጓዛለን፡፡ ነጋዴው ቆም ብሎ አያስብም፤ ሙሰኛው የመንግሥት ተቀጣሪ ቆም ብሎ አያስብም፤ ቀጣሪው ተቀጣሪውን አያስታውስም፡፡ ሁሉም እንደ አቃቂ የጋሪ ፈረስ ዐይኑን ሸፍኖ በልቶ የማይጠረቃ ከርሱን ለመሙላት ሲሮጥ ይውላል፤ ያድራልም፡፡ በተናጠል ሩጫ የትም እንደማይደረስ የገባን በጣም ጥቂቶች ነን፡፡ ሀገር በጦርነት ንዳድ ብትቆላ፣ወገን በኑሮ ውድነት ቢጠበስ ማንም ግድ አይሰጠውም፡፡ ዳኝነት ተዛብቷል፤ ፍትኅ ዐይኗ ጠፍቷል፡፡ የሀገርና የወገን ፍቅር ተሟጦ ገደል ገብቷል፡፡ በቃኝን ረስተናታል፡፡ በእውነተኛው ገቢያችን መኖር ካቆምን ብዙ አሠርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባጭሩ ዐውሬ ሆነናል፡፡
ሞልቶ የተረፈው ዜጋ በየሣምነቱ አውሮፓና አሜሪካ፣ ሻንጋይና ዱባይ የሚያደርገው ሽርሽር እንዳይጓደልበት ሲል በዚህ መከረኛ ሕዝብ ላይ የሰማይ ስባሪ የሚያህል የኑሮ ሸክም ይጭንበታል፡፡ በዚህም ሳቢያ የ200 ብሩን የ5 ሊትር ዘይት 700፣ የ2000 ብሩን የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ብር 5000 በላይ፣ የ200 እና 300 ብሩን የአንድ ኪሎ ሥጋ ዋጋ 700 እና 800 ብር፣ የ10000 ብር ኮርማ በሬ እስከ ብር 150000 እና ከዚያም በላይ፣ የ40 እና የ50 ብር ምሥር ክኩን 110 ብር… ሲያደርግ ቅንጣት አይዘገንነውም፡፡ ነጋዴው ዕቃውን የሚሸጠው ለምስኪን ድሃ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ከኅዋ ለመጡ ልዩ ፍጡራን ወይም ለሮክፌለርና ለቢልጌትስ ቤተሰቦች ሳይመስለው አልቀረም፡፡ ይሄ የኑሮ ውድነት ብቻውን የአርማጌዴዖን ጦርነት ሊያስነሣ ይችላል – ባለንበት ዳይሜንሽን ምግብ ካልበሉ፣ ልብስ ካልለበሱና መጠለያ (ቤት) ካላገኙ አይኖርማ፡፡ ሀገራዊነት የሚጀምረው እንግዲህ ከዚህ ነው፡፡ አንዱ ተንቀባርሮ እየኖረ ሌላው ወንድሙ በርሀብ እየተንጠራወዘ የጋራ ሀገር የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ሥራ መያዙ ይቅርና በማንነቱ ምክንያት አንዱ እየተሳደደ ባለበት ሲገደል ሌላው ግን በሻማና በጧፍ እየተፈለገ ለሹመትና ለጥቅም ሲታጭ እያየን የወል ሀገር፣ በችግሯ ጊዜ እኩል ልንደርስላት የሚገባን የጋራ ግዛትና ድንበር አለን ማለት አንችልም፡፡ አንዱ እውነተኛ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ ሆኖ በሀገር ላይ አንዳች ነገር ቢፈጠር ደግሞ ማንም ለጦርነት አይሰለፍም – ይህንን ገሃድ እውነት በቅርብ እናያለን፡፡ “ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” አይሠራም – ሞኝነት ዱሮ ቀረ፡፡ ለሁሉም እኩል የሚያስብና የሚጨነቅ መንግሥት ያለመኖሩ ችግር ለዚህ ዓይነቱ ማኅበረሰብኣዊ ምስቅልቅል እንደዳረገን ግልጽ ቢሆንም ሕዝብ ከመንግሥት ተሸሎ የሚገኝበትን ሁኔታ ካልፈጠርን የያዝነው መንገድ ወደ ገደል የሚከት ነው፡፡ ለማንኛውም የፊታችን ወጀብ ብዙ ሳይጎዳን እንዲያልፍ ጠንክረን እንጸልይ፡፡ ልብ ይስጠን፤ ከሆዱ ቀነስ ያድርግልን፡፡ ደግሞም በቃችሁ ይበለን፡፡
በሥነ ቃል እንደጀመርን በሥነ ቃል እንሰነባበት፡-
“ወይ አንቺ ክምሬ ‹አለሁኝ› ብለሻል፤ አላወቅሽም እንጂ በቁምሽ አልቀሻል፡፡” ምሥጢሩን እናንተው ድረሱበት፡፡