>

ከመቧጨር መስራት ይቅደም! (ኤርምያስ ለገሰ)

ከመቧጨር መስራት ይቅደም!

  ኤርምያስ ለገሰ

ኦሮሙማ መራሹ ብልፅግና በተለያየ መንገድ ያሰማሯቸው ውታፍ ነቃዮች እና ተደጋፊ ተደማሪዎች ከሚፅፉትና ከሚናገሩት በመነሳት አንዳንድ መሰረታዊ ነገሮችን ከእውቀት ማነስ ሲያዛቡ እመለከታለሁ። ከእነዚህ ቁምነገሮች መካከል “ፕሮፐጋንዳ” እና “ካድሬ” የሚሉት ጥልቅ ሃሳብ ያላቸው ቃላቶች ናቸው።
እነዚህ ቃላቶች በአብዛኛው ከመንግስትና የገዥው ፓርቲ አሰራሮች ጋር የተሳሰሩ ቢሆንም በስራው የተሰማሩ ሃይላት ስለ ባህርያቶቹ ፣ልዩነቱና አፈፃፀሙን በትክክል የተረዱት አይደለም።
ለዚህ አጭር መጣጥፍ ‘ፕሮፐጋንዳ’ እና ኢትዮ360 ዛሬ ምን አለ? ፕሮግራም ላይ ላተኩር።
1. ፕሮፓጋንዳ ምንድነው?
አንጋፋው ብዕረኛ ሙሉጌታ ሉሌ በተለያዩ ጊዜያቶች በከተባቸው መጣጥፎች የፕሮፐጋንዳን ትርጉም እንደሚከተለው ይገልፀዋል፣
“ፕሮፐጋንዳ የሰዎችን አእምሮ መማረኪያ ፣ የአስተሳሰባቸውን አቅጣጫ የመለወጫ ብርቱ ትግል የሚጠይቅ ስልት ነው” ይለናል።
ከዚህ አባባል መረዳት እንደሚቻለው ‘ፕሮፐጋንዳ’ በራሱ መጥፎ አይደለም። በራሱ ጥሩ አይደለም። ይልቁንስ ፕሮፐጋንዳ ስልት፣ ጥበብና በፕሮፐጋንዳው ሥርጭት ረገድ በሙሉ ልቡ አብሮ የተሰለፈ ኃይል አስፈላጊ መሆን ከአላማና ግቡ ጋር የተያያዘ ነው።
2. የፕሮፐጋንዳ ዐበይት ነጥቦች
የሰዎችን አእምሮ ቅኝ ለመያዝ ፕሮፐጋንዳ ሕዝቦች ሊቀበሉት የሚችሉት ጠንካራና የነጠረ ሃሳብ ባለቤት መሆንን ይጠይቃል። ከዚህ አንፃር ሶስት አበይት ነጥቦች ከግምት መግባት እንዳለባቸው ብዕረኛው ያስገነዝባል። እነዚህም፣
1ኛ) የፕሮፐጋንዳው ይዘትና ሊኖረው የሚችለው ተቀባይነት
2ኛ) ፕሮፐጋንዳውን ተቀባይ የሆነው ሕዝብ ወይም የሕዝብ ክፍል ልምድ፣
3ኛ) ፕሮፐጋንዳው ፕሮፐጋንዳ አድራጊውን ወገን ( በእኛ ሁኔታ መንግስት) በጥራት ለማሳየት መቻል አለመቻሉ ናቸው።
3. የፕሮፐጋንዳ ስራ በዚህ ዘመን
“የፕሮፐጋንዳ ስራ ዛሬ ረቀቅ ያለ ጥበብ መሆኑ የሚስተባበል አይደለም” በማለት የሚገልፀው ሙሉጌታ ሉሌ ፤ ስራው የዓላማ ጥራትን፣ ሕዝብ ለሚቀበለው መርሕ ሳይዋዥቁ መቆምን፣ የበሰሉ ፕሮፐጋንዳስቶች መያዝን እንደሚጠይቅ ያስረዳል። ከቶውንም በአሁኑ ጊዜ አንድ መንግስት የፕሮፐጋንዳ ሥራውን ከፍተኛ ዓላማ ካለው በራሱ ተቀጣሪዎችና መደበኛ ካድሬዎች የኢንፎርሜሽንና የዲፕሎማሲ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን በውጭ መንግስታትና ድርጅቶችም አማካይነት ለመስራት ይቻላል።
የጦረኝነት፣ ፍለጠው ቁረጠው የፕሮፐጋንዳ ፓሊሲ የሚከተሉ መንግስታት ትርፉ ውግዘትና በየፓለቲካውና በየኢንፎርሜሽን ሚዲያ የሚገጥመው የውግዘት ዘመቻ ነው። በመጨረሻም ከፍተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ይገጥመዋል።
4. ኢትዮ-360 ‘ዛሬ ምን አለ?” ፕሮግራም
በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ የፓለቲካል-ኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰባት ቀን ሙሉ ሳያቋርጥ እየተላለፈ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ፕሮግራም ኢትዮ-360 ፕሮግራም ብቻ ነው። ይህ በመሆኑ ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል። ለአድማጮቻችንም የላቀ ምስጋና አቀርባለው። በየቀኑ የሃሳብ ድግስ ደግሰህ ተቋዳሾችህ እልፍ ሲሆኑ ከመመልከት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም። እናም በየቀኑ በአማካይ ከ6ሺህ በላይ የቀጥታ ስርጭት ተከታታይና በ24 ሰዓት ውስጥ በአማካይ 80ሺህ ተመልካች ያለው ፕሮግራም ባለቤት የሆነበት ብቸኛው ‘የዛሬ ምን አለ?” አካል መሆን እጅግ ያኮራል።
እርግጥም ይህ ብዙዎች ሊተገብሩት ቀርቶ ሊያስቡት የማይችሉት ከባድ ተግባር ነው። ሞክረውት ወደ ኃላ የወደቁ ብዙዎች ናቸው። በእርግጥም እንደ መስቀል ወፍ እየመጡ እንዲህ አይነት ድካም እና ፅናት የሚጠይቅ ስራ መስራት እንኳን በእውን በሕልምም ያዳግታል። በተለይ በተለያዩ ፓለቲካዊ ምክንያቶችና ግላዊ የቅናት ዛሮች ተነሳስታችሁ የዘመታችሁብን ሰዎች እስቲ ሞክሩትና እናክብራችሁ። በሰው እጅ ያለውን ከበሮ እናንተም ጨብጡትና እንዳትደናገሩ እናግዛችሁ።
እንድ ነገር እንድትገነዘቡት የምፈልገው ሰርቶ ያሳየና አቃቂር አውጪ እኩል የሕሊናና የሞራል ሚዛን የላቸውም። በተለይ በተለይ አንዲት ገፅ ዜና መፃፍ አቅቷችሁ ሙሉ ቀን ስትንደፋደፉ በተግባር የምናቃችሁ የስመ ጋዜጠኞች ደግሞ ብታርፉ ይሻላል።በአደባባይ ባንተዛዘብ ጥሩ ስለሆነ ዝምታችንን ተረድታችሁ አደብ ግዙ። አንድ ክሬዲት ካርድ እየጫሩ መኖር ጊዜው አልፎበታል። ካርዱም ተመዝግቦ የታሪክ ፋይል ውስጥ ተቀምጧል።
እናም ይህ ስኬት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም። መሰረታዊው ምክንያት የኢትዮጵያና ኤርትራውያንን አእምሮ መማረኪያ ፣ የአስተሳሰባቸውን አቅጣጫ የመለወጫ ብርቱ ትግል የሚጠይቅ ስልት በመጠቀማችን ነው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ሊቀበሉት የሚችሉት ጠንካራና የነጠረ ሃሳብ ባለቤት በመሆናችን ነው። በምናቀርባቸው ፕሮግራሞች ይዘት ላይ የማያቋርጥና እጅግ ፈታኝ ዝግጅት የማድረግ ቁርጠኝነት ሰላለን ነው። ብዙውን ጊዜ የዕለት ርዕሳችንን መረጣ እንኳን አስቀድመን ሰፊ ውይይት የምናደርግበት ነው። ብዙ የውስጥ የቤት ስራዎች አሉብን።
ይሄ ማለት ግን የሚጎድለን ነገር የለም ማለት አይደለም። ብዙ እጥረቶች አሉብን። ታዳጊ እንደመሆናችን መጠን ግን ክፍተታችንን እየሞላን እንጓዛለን። መርሆ እና መስመራችንን እስካልሳትን ድረስ ሕዝባችን እንደ ትላንትና ዛሬ ሁሉ ነገም አብሮን እንደሚቆምና ስናጠፉ እንደሚያስተካክለን እናውቃለን። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። በደልና ግፍ ባለበት ሁሉ ለመገኘት የምንጥር ኢትዮጵያዊ!!
Filed in: Amharic