>

በምርጫ ካርድ በአግባቡ ስለመጠቀም (ሲናጋ አበበ)

በምርጫ ካርድ በአግባቡ ስለመጠቀም

ሲናጋ አበበ


የዘንድሮ ምርጫ ከሞላ በጎደል ከምንጊዜም በበለጠ መልኩ አሳታፊ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ አሳታፊነቱ ምንም እንኩዋን ለገዢው ፓርቲ አልጋ ባልጋ ቢሆንለትም ሌሎችም ድምጻቸውን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በችግር ላይ ችግር ቢፈጠርባቸውም በአዲስ አበባ በመጠኑም ቢሆን መሰማት ችለዋል፡፡

         እንደምንመለከተውም ሆነ እንደምንሰማው ከየምርጫ ጣቢያዎችም ለውድድር የሚቀርቡትን ብልጽግና ፓርቲ ለውድድር የመረጣቸው የታወቁ ሀኪሞች፤ መሀንዲሶች፤በየሠፈሩ አንቱ የተባሉትን እንደሆነ በየመንገዱ ከተለጠፉት ፎቶግራፎች ማየት ይቻላል፡፡  እነዚህም እጩዎች አብዛኞቹ በፓርቲው ፕሮግራም የተጠመቁ ሳይሆኑ በፓርላማ ገብቶ ክብርና ሞገስ ለማግኘትና ደመወዝ ለመብላት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የየአካባቢው ነዋሪ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ቢመረጡ ጠቃሚዎች የሚሆኑበት ሲያሰላ የታወቁ በመሆናቸው፤ በሙያቸው ምሥጉን ስለሆኑ ብቻ በመሆኑ ሊመርጡዋቸው እንደሚያስቡ ከአንዳንድ ሰዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ጥያቄው እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ተመርጠው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ወንበራቸውን ይዘው በመራጮቻቻው እንደሚገመቱት ከብልጽግና ፖሊሲ ውጭ ቀርጸው የሚያራምዱ ሳይሆን ያስመረጣቸውን ፓርቲ ማለትም የብልጽግናን ፖሊሲ ከማራመድ አንድ ስንዝር የተለየ ሥራ እንደማይሰሩ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምንም  ዓይነት የተለየ ፖሊሲ ሊያራምዱ ቀርቶ የተለየ ነገር እንኩዋን መናገር አይችሉም፡፡ የፓርቲ ደንቡ ያስገድዳቸዋል፡፡

        ለምሳሌ ያህል ብልጽግና ይህ በብሄረሰብ የተዋቀረው ፌዴሬሽን እንዳለ እንዲቀጥል መፈለጉን አስታውቁዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዳይነካበት በፓርቲው አመራሮች ሲገለጥ በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከሞላ በጎደል የጎሳን ፖለቲካ ይጠየፋል፡፡ የአዲስ አበባ የብልጽግና እጩዎቹም አስተሳሰብ ከዚህ አይለይም ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

         ስለዚህ ማንኛውም መራጭ የየፓርቲዎችን ፖሊሲ በመመርመር፤ በማጤን ለኔ፤ ለቤተሰቤ ለወገኖቼ የቆመ ፓርቲ ነው አገሬኔ ከችግር ያወጣታል፤ ሰላም ማስፈን የሚችል ፓርቲ ነወ ወይሰ ወደ የባሰ ማጥ ከቶ እርስበርስ ሊያጫርሰን የሚችል ይሆን ይሆን ብሎ ማሰብና የሱን ፍላጎት የሚያራምደውን ፓርቲ እጩ መምረጥ እንጂ ግለሰቡን ማምረጡ አያዋጣም፡፡

          ለውድድር የቀረበው እጩ ጠባዩ ሸጋ፤ ሰላምተኛ፤ ሰው አክባሪ፤ ታዋቂ ግለሰብ፤ ባለሥልጣን ሞሆኑ መለኪያ ሊሆን አይገባም ምንም እንኩዋን ለተመራጩ ሁሉ አስፈላጊ መሆናቸው ቢታወቅም፡፡ ከዚህ መለኪያ የሚገኝ ምንም ትሩፋት አይገኝም፡፡ ይህን ሰው ለመምረጥ እሱን የመረጠው ፓርቲ የሚያራምደው ፖሊስ ወንዝ የሚያሻግር መሆኑን መረዳት ነው፡፡ የፓርቲው ፕሮግራም ለዚህም ሆነ ለመጭው ትውልድ የሚተርፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አቅፎ የሚያዝ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡

         ይህን መራጩ ህብረተሰብ እንዲገነዘብ ያስፈልጋል፡፡

ማንኛውም መራጭ የሚመጠው ፓርቲውን እንጂ ግለሰቡን እንዳልሆነ ማጤን ያስፈልጋል፡፡

                                         

Filed in: Amharic