>

የድሮ ዘፈን ላይ የቀረበ አጭር ትንታኔ...!!! ( በእውቀቱ ስዩም’)

የድሮ ዘፈን ላይ የቀረበ አጭር ትንታኔ…!!!

( በእውቀቱ ስዩም’)

የድሮ ዘፈን ነፍሴ ነው ! የድሮ ዘፈን የሆነ ቬጂተርያን ቃና ነበረው:: በጊዜው ያልተዘመረለት የዱር ፍሬ የለም! “ የሾላ ፍሬ ” “ እንኮይ እንኮይ” “ ብርቱካኔ” “ ሸንኮራ” “ ፓፓየ” ነሽ !
“ ተቀጠፈ ሎሚ ተበላ ትርንጎ/ ከሸጋ ልጅ መንደር በስሎ ተንዤርግጎ ! “ የምትለዋን የነዋይን ግጥም ማን ይረሳል? ምን ዋጋ አለው! ከለታት አንድ ቀን ታደሰ አለሙ የሚባል ዘፋኝ ተነስቶ የአማርኛን ዘፈን ስጋ በስጋ አደረገው !
የድሮ ዘፋኞች ከማዝናናት ጎንለጎን ጠቅላላ እውቀት ይለግሱ ነበር ፤ ህዝቡ ስለቤት እና የዱር አራዊት ጠባይ መረጃ እሚያገኘው ከዘፋኞች ነበር ፤ ለምሳሌ፤
“ካላጉረመረመ አይበላም ነብር( ይርጋ ዱባለ) –
“የቁልቁለት መንገድ ለበቅሎ አይመችም”
( ሙሉቀን መለሰ)
“የእባብ ዘለግላጋ የለውም እግር እጅ “
 (አለማየሁ እሸቴ )
“ዶሮ ውሃ ጠምቶት ተንጋሎ ይጠጣል”
(ንዋይ ደበበ)
“ፍየል ቅጠል እንጂ አትበላም እንጉዳይ”
( ንዋይ ደበበ)
ባጠቃላይ ፤ የድሮ ዘፈን ራሱን የቻለ ናሽናል ጆግራፊ ቻናል ነበር ማለት ይችላል !
በደምሳሳው ሲታይ የድሮ ዘፈን ግጥም ብዙ አይመስጥም! በኔ ግምት ሁለመናው የተዋጣለት የዘፈን ግጥም የተጀመረው በይልማ ገብረአብ ነው ! አሁን ደግሞ የሀብታሙ ቦጋለን፤ የአብርሃም ወልዴንና የኑረዲን ኢሳን ግጥሞች አጣጥማለሁ፤
ከቆዩ ዘፋኞች ውስጥ ግጥም እማይሰምርለት ኢያዩ የሚባል ዘፋኝ ነበር ! የኢትዮጵያ ሬድዮ እግር ኩዋስ ባስተላለፈ ቁጥር ለምን የሱን ዘፈኖች ጆሩዋችን ላይ እንደሚጥዳቸው እስታሁን አይገባኝም !
“ እንስራዋን አዝላ በወገቡዋ ላይ
ውሃ ልትቀዳ መሄዱዋ ነው ወይ ? “
ይላል ኢያዩ::
እረ የለም ! እንስራዋን ውሃ ዋና ልታስተምር እየሄደች ነው በነጭና ጥቁር ቲቪ ይተላለፉ የነበሩትን የድሮ ሙዚቃ ቪድዮዎች ባየሁ ቁጥር አንድ ነገር ይገርመኛል ! ዘፋኞች በጣም የተጋነነ የእጅ እና የፊት እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፤ ለምሳሌ ፀሀየ ዮሀንስ ከነዋይ ደበበ ጋር አንዲት ማይክ ተካፍሎ በሚዘፍንበት ቪድዮ ውስጥ፤
“ ባቄላ ምርቱ እንጂ አያምርም ክምሩ
ተጫወች ልጫወት ምንድነው ማፈሩ “
ሲል በእጆቹ እንቅስቃሴ የባቄላ ክምርን ለተመልካቹ ለማሳየት መከራውን ያያል ! ይሄ ለምን አስፈለገ ልትል ትችላለህ! በዛን ዘመን የነበረው ትቪ ድምፁ ጥራት አልነበረውም ፤ ጠረጴዛ ላይ ተጎልቶ ደቅ ደቅ ደቅ ሲል መስታውት የተገጠመለት ጄኔተር ይመስላል ! እና ዘፋኞች ዘፈናቸውን በምልክት ቋንቋ እንዲያጅቡ ይገደዱ ነበር!
(የሰርፀ ፍሬ ስባሃትን አስተያየት አይቼ እቀጥላለሁ)
Filed in: Amharic