>

ከዋኖቻችን አንዱ ዐረፉ (ከይኄይስ እውነቱ)

ከዋኖቻችን አንዱ ዐረፉ

ከይኄይስ እውነቱ


ለኢትዮጵያ ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት በተለይ ታላቅ ባለውለታ የነበሩት የሊቀ ማእምራን (ፕሮፌሰር) ጌታቸው ኃይሌን ዜና ዕረፍት አንድ የቅርብ ወዳጄ ከፌስ ቡክ ገጽ አነበብኹ ብሎ (የፌስቡክን ተአማኒነት እየተጠራጠረ) ሲያረዳኝ ለተወሰኑ ሰከንዶች ክው ብዬ ቀረሁ፡፡ ከአራት ዐሥርታት በላይ ለሆነ ጊዜ በረጅም ሰቈቃና ምጥ ውስጥ የምትገኝ አገራችን ከፈተና የምትወጣበትን መንገድ ጠቋሚ ከሆኑ ዋኖቻችን መካከል በፊት ለፊት ረድፍ የማያቸው የፕ/ጌታቸው ሞት ልብ ሰባሪ ነው፡፡ 

ጋሼ ጌታቸው በወቅታዊው የአገራችን ጉዳይ የሚያቀርቧቸውን ጽሑፍ እና ቃለ መጠይቃቸውን ከሰማሁ ረዘም ያለ ጊዜ በመሆኑ በውስጤ ከዕድሜ መጫን ጋር የሕማም ጉዳይ እንደሚሆን ጥርጣሬ ቢኖረኝም አንዱን ቀን በጽሑፋቸው ወይም በድምጽ አገኛቸዋለሁ የሚል ናፍቆትና ተስፋ ነበረኝ፡፡ ይሁን እንጂ የአምላክ ፈቃዱ ሳይሆን አስደንጋጩን መርዶ ሰማሁ፡፡ ኢትዮጵያና ሕዝቧ አልፎም ዓለም ጎደለባቸው እንጂ እሳቸውስ ሩጫቸውን ባግባቡ የፈጸሙ ይመስለኛል፡፡ 

ዛሬ ባገራችን ትርጕም እያጣ የመጣው ምሁር የሚለው ቃል ሲነሣ በቀዳሚነት ወደ አእምሮዬ ከሚመጡ የአገራችን መልካም ፍሬዎች ግንባር ቀደሙ ጋሼ ጌታቸው ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ጨውነትን ከትሕትና በመላበስ በሥነ ጽሑፍ በተለይም በግእዝ ቋንቋ የተጻፉ ድርሳናትን ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ፣ በታሪክ፣ በእምነት እና በፖለቲካ ዙሪያ በርካታ መጻሕፍትን፣ የምርምር ሥራዎችን እና መጣጥፎችን ትተውልን ያለፉ እውነተኛ ምሁር ናቸው፡፡ 

በሌላ በኩል አገዛዞች በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ግፍና በደል የሚያንገበግባቸው፣ ኢፍትሐዊነትን አጥብቀው ሲቃወሙ የኖሩ የሰብአዊ መብትም ተሟጋች ነበሩ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፡፡ አለመታደል ሆኖ ልበ ደንዳና አገዛዞች ባይሰሟቸውም ላገር ለወገን ጠቃሚ የሆኑ ምክሮቻቸውን ከመለገስ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም፡፡

በዕድሜም በዕውቀትም ታናናሾቻቸው ከሆኑ ለመማር ለማወቅ ወደ ኋላ የማይሉ፤ ወጣት ምሁራንን በሚቻላቸው ሁሉ ለማገዝ ደከመኝ የማይሉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነበሩ ጋሼ ጌታቸው፡፡ በሥራዎቻቸው (በመጻሕፍቱ፣ በመጣጥፉና ቃለ መጠይቆቻቸው) ተጠቃሚ ከሆኑ ወገኖች መካከል እኔም አንዱ ነኝ፡፡ 

በልቤ ከምሳሳላቸው ምርጥ ኢትዮጵያውያን ቀዳሚው ነበሩ፡፡ ለኢትዮጵያ ስለዋሉላት ታላቅ ውለታ ብድራት ከፋይ ልዑል እግዚአብሔር ቢሆንም እግዚአብሔር ይስጥልን ብዬ ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ በሕይወት ቢሆን እመርጥ ነበር፡፡ በስንፍናዬ አልተሳካልኝም፡፡

ትውልዱ ጊዜ የማይሽረው አገራዊ አበርክቷቸውን ተረድቶ ቋሚ መታሰቢያ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ እያሳሰብኹ፣ ጋሼ ጌታቸው የኢትዮጵያ ሀብት/ቅርስ በመሆናቸው በቅድሚያ ለቤተሰባቸውና ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ 

እግዚአብሔር አምላክ የአገልጋዩን ነፍስ በገነት በመንግሥተ ሰማያት እንዲያሳርፍልን ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡

Filed in: Amharic