>

ብታምኑም ባታምኑም አቢይ አህመድ የተላከው ለቅጣት ነው! (ምሕረት ዘገዬ)

ብታምኑም ባታምኑም አቢይ አህመድ የተላከው ለቅጣት ነው!

ምሕረት ዘገዬ


አሁን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ነው – ውጤቱ ለታወቀው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ልንደርስ ሦስት ሌሊቶች የቀሩት የዓርብ ምሽት፡፡ ወደዚህ የንዴት ማስተንፈሻ ጽሑፍ የገባሁት ባልተቤቴ አንድ ፎርሜሽን ነግራኝ ነው – በጣም አናዳጅ ፈርሜሽን ወይም መረጃ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ከኢዮብ የበለጠ ትግስትና ከብረት የጠነከረ ጽናት ባለቤት ነው፤ ከባቢሎን የከፋ መለያየት ውስጥ የሚገኝ ሕዝብም ጭምር፡፡ የግብጽ ሴቶች ፓስቲ አሥር ሣንቲም ጨመረ ብለው ማንከሽከሻቸውን ይዘው አደባባይ በመውጣት መንግሥት ይጥላሉ እኛ አንድ ሊትር የምግብ ዘይት 130 ብር ስንገዛ ፊታችን በደስታ የተዋጠ መስሎ ከሱቆች እንወጣለን – በአሽሙር ሣቅ፡፡ የምንገርም ሕዝብና የሚገርም መንግሥት ነው ያለን፡፡ ቅጣትም እኮ ዓይነትና መልክ አለው፡፡ የኛ ይለያል፡፡

“ይሄውልህ ዛሬ ገበያ ወጥቼ…” ስትል ወጓን ጀመረች ክብርት ባለቤቴ፡፡ እኔም ይህ ዓይነቱን ነገር ለምጄዋለሁና ምን ልታረዳኝ ይሆን ዛሬ ደግሞ በሚል በጥሞና አዳምጣት ጀመር፤ ዘመኑ መቼስ በየትኛውም አቅጣጫ የመርዶ እንጂ የብሥራት አልሆነም፡፡ “ይሄውልህ ዛሬ ገበያ ወጥቼ ዛላ በርበሬ ብጠይቅ አንዱ ኪሎ 360 ብር አሉኝና ሳልገዛ መጣሁ፡፡ አንደኛ ደረጃ 360፣ ሁለተኛ ደረጃ 340፣ የመጨረሻውና እዚህ ግባ የማይባለው ምራጩ ደግሞ 300 ብር፡፡…” ስትለኝ ክው ነው ያልኩላችሁ – ጠላታችሁ ክው ይበልና፡፡

ኑሮን ተዋት፡፡ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ተደርባ ከነሱ ባልተናነሰ ሁኔታ እያሽቃነጠችብን ናት፡፡ ብል(ጽ)ግና ከመጣ ወዲህ የኑሮ ውድነቱ ሆን ተብሎ በሚመስል አኳኋን ሽቅብ እየተሽቀነጠረ ነው፡፡ አቢይ አህመድ ለቅጣት እንደመምጣቱ እኛ እህል እንቅመስ መርዝ እንጠጣ፣ ትቢያ ላይ እንረፍ ጉድጓድ ውስጥ እንተኛ … ጉዳዩ አይደለም፡፡ ይራበን ይጥማን ፣ እንሙት እንዳን የርሱ ጣጣ አይደለም – በጭራሽ አያሳስበውም፡፡ አንዳንዴ ሳስበው የሚያስተዳድረውን ሕዝብ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ምናልባትም ራሱን የአንደኛው የአውሮፓ ሀገር መሪ አድርጎ ሳይቆጥር አልቀረም፡፡ እኛ በርሱ ወታደሮች አንገታችን እየተቀላ እርሱ የሚገኘው አትክልት ሲተክልና መናፈሻ ሲያስጌጥ ነው፡፡ ይህ ሰው ዘረመሉ(ጂኑ) መመርመር አለበት፡፡ በደስታ የሚያለቅስ፣ በሀዘን የሚስቅ ዓይነት ግራ አጋቢ ስብዕና ያለው ነው፡፡ የሱ ዋነኛ ጭንቀት ያቺ ጦሰኛ እናቱ በሰባት ዓመቱ የነገረችው የሰባተኛ ንጉሥነት ትንቢት ናት፡፡ በህልሙም በእውኑም፣ ቆሞም ተኝቶም የሚያቃዠው የወንበሩ ጉዳይ እንጂ ሚሊዮን አማራ ታረደ፣ ሚሊዮን ዜጋ ተሰደደ፣ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ከመኖሪያው፣ ከእርሻውና ከንግዱ ተፈናቀለ ጉዳዩ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ ጩኸትና ትርምስ መሀል ግና ቤተ መንግሥት ውስጥ እንዴት እንቅልፍ ይዞት እንደሚያድር ግርም ይለኛል፡፡ በዚህ ረገድ ታድሏል እላለሁ፤ እኔ ብሆን በጭንቀት እፈነዳ ነበር – ለነገሩ ለመፈንዳትም እኮ ሰው መሆንን ይጠይቃል፡፡ መላ ትኩረቱ እንደምንም አጭበርብሮ ይቺን ምርጫ እማለፉና ሥልጣኑን እመጠቅለሉ ላይ ነው፡፡ መከራ ፍዳውን የሚበላው ለዚያቺው ሥልጣን ነው፡፡ ብቻ ከጨለማው ንጉሥ የተሰጠውን ተልእኮ በሁለንተናዊ ስኬት እየተወጣ ነው፡፡ ይሉኝታ ብሎ ነገርማ በጭራሽ አልፈጠረበትም፡፡

እንግዲህ ልብ አድርጉ፤ በአንድ ሽህና ሁለት ሽህ የወር ደመወዝ የአራትና አምስት ብር ዕቃ አራትና አምስት መቶ ብር ተገዝቶ እንዴት ሊኖር ነው? የሥጋ ነገርማ አይነሣ፡፡ እንደሚባለው ከሆነ አንድ ኪሎ ሥጋ ከ800 እስከ 1000 ብር ደርሷል አሉ፡፡ ጥቂት ነጋዴዎችና ጥቂት ባለሥልጣኖች ነፍሰ ሥጋችንን የፊጥኝ አስረው እየተጫወቱብን ነው፡፡ ይህችን ሀገር ድራሹዋን እያጠፋ የሚገኘው አንዱና ዋናው ነገር ደግሞ ሙስና መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዘረኝነቱንና ተረኝነቱን ተታኮ የሚካሄደው ሙስና አሁን አሁን እስትንፋሳችንን ፀጥ ሊያደርግ ምንም አልቀረው፡፡ የትም ሂድ፣ የትም ግባ ጉዳይህ የሚሳካልህ በእጅህ ሄደህ እንጂ በእግርህ ከሆነ ከዘቦች አታልፍም፡፡ የሞቱት ተሻሉ፡፡ የሞቱ በለጡን፡፡ መተከልና አጣዬ በማንነታቸው ምክንያት ሰማዕት የሆኑ ወገኖቼ አስቀኑኝ – ተራየ መድረሱ ላይቀር እስከዚያው የኔም ስቃይ በዛ፡፡ የተራ ጉዳይ ነው፡፡ አቢይ እስካለ ድረስ ሁላችንም ግን ተራ በተራ እናልቃለን፡፡ በኑሮ ሆዳችን ላይ የጀመሩትን ዕርድ በሜንጫ አንገታችን ላይ ይጨርሱታል፡፡ አንድዬ ይድረስልን – በውጭ ሀገር ያላችሁ ምንኛ ታድላችኋል! በስማም! ኢትዮጵያ ሀገሬ አልመስልህ እያለችኝ ተቸገርኩ፡፡ ወዴትና በየት በኩል ልሂድ? ሰው እንዴት ሰው ባልሆነ ሰው ይተዳደራል?

Filed in: Amharic