>

የ2013ን ምርጫ ያሸነፈው አዲስ አበቤ! (ብሩክ ደሳለኝ)

የ2013ን ምርጫ ያሸነፈው አዲስ አበቤ!

ብሩክ ደሳለኝ


አዲስ አበቤ መች ዋዛ! መለስም አዲስ አበባ እየፎከረና እያቅራራ ምርጫ ሲመጣ ጭራውን ቆልፎ ወደ አድዋ ይሮጥ እንደ ነበረው ሁሉ የሱ ምልምል አቢይም እንጦጦ ፓርክን ሰራሁ፣ ቤተመንግስቱን አደስኩ እያለ በሚመጻደቅበት ከተማ ለመወዳደር የአዲስ አበቤን ፊት ለማይት ስለፈራ እርሱም እንደ ጡት አባቱ መለስ ጭራውን ቆልፎ ወደ በሸሻ ሸሽቷል፡፡ በሸሻ ሄዶ የሚወዳደረው ለበሸሻ ፓርክ ሰርቷል ወይስ ቤተመንግስት? እንዲያው ለመሆኑ አንድ የውሃ ጉድጓድስ አስቆፍሮ ይሆን? ይሄን ሁሉ ፎቶ፣ ካናቴራ ከመበተን ለሚኖርበት ቀበሌ የፈረደባቸው ሴቶችና በምናምን የተደራጁ ወጣቶች ሞቅ አርጎ ወጪ ቢመደብ እኮ፣ በዚያ ላይ የኮሮጆ ዕቃ ዕቃ ጨዋታውን በማሳመር መመረጥ ይቻላል፡፡ ምንድነው ይሄ ሁሉ ወጪና ትርምስ? ብልጽግና እኮ ያራዳ ልጆች ቢኖሩበት በአነስተኛ ወጪ ጠቅ ጠቅ ይደረግና መመረጥ ይችል ነበር፡፡ 

ታዲያ እንዴት ኢትዮጵያን የምታክል አገር በዚህ በ21ኛው ክፍለዘመን እንዲህ ያለ አዲስ አበባን የሚፈራ ይመራታል? እርሱ የአዲስ አበባን ህዝብ ፈርቶ በማይወዳደርበትና በማያገባው አዲስ አበባ ውሰጥ በየአደባባዩና መንደሩ ፎቶውን እየለጠፈ ራሱን የማፍቀር ጥማቱን ያረካል፡፡ የሚገርም የደነዝ ዘመን ላይ እኮ ነው ያለነው! ለመሆኑ አለን እንዴ? ለተወካዮች ምክር ቤት በሸሻ ላይ የሚወዳደረው ሰውየ ፎቶ አዲስ አበባ ምን ሊያደርግ ይለጠፋል? በዚያ ላይ የፓርቲ መሪ መሆኑ እንኳ ያልታወቀ ሰው ፎቶ አዲስ አበባ ላይ መለጠፍ ምን ይባላል? ይሄ ብልጽግና የሚባል ፓርቲ ለምንድነው መሪውን ያልመረጠው? በፎቶ ፎግረው በኋላ ሊፈነግሉት ይሆን እንዴ? ባልተወዳደረበት፣ የየትኛውም ድርጅት መሪ መሆኑ ባልታወቀበት አዲስ አበባ ላይ የሱ ፎቶ የሚለጠፈው በምን ምክንያት ነው? ምርጫ ቦረዱም ያው የእንኩቶ ዘመን ውጤት ስለሆነ ይሄን እያየ ዝም ይላል፡፡ ምን ዓይነት ዘመን ነው? ዘመነ መንሱት ያሉት ማን ነበሩ?

ለማንኛውም የ2013 ምርጫ በአግባቡ ተካሄደም አልተካሄደም አዲስ አበቤ ብልጽግናንም ሆነ አቢይን በሸሻ ድረስ በማሸሽ ገና ውድድሩ ሳይጀመር ማሸነፉን አረጋግጧል! አቢይን አዲስ አበባ ላይ ማወዳደር ያልቻለው ብልጽግና በግልጽ ውድድሩ ሳይጀመር ፎጣውን ጥሎ ከመቧቆሻው ሪንግ መውረዱን  ስላረጋገጠ የ2013 ምርጫ አሸናፊ አዲስ አበቤ ነው!   በመንግስት  መዋቅራዊ ሙሉ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰውን ብልጽግናን ፎጣ ያስጣለው ደግሞ ያለጥርጥር በእስክንድር የሚመራው ባልደራስ ነው፡፡ አስክንድር ሆይ ምርጫ ቢጭበረበር፣ ኮሮጆ ቢሰረቅ ሳይጀመር ያለቀውን ምርጫ አሸናፊ አንተ፣ ባልደራስና አዲስ አበቤ ናችሁ፡፡ 

የአዲስ አበቤን ልብ ለማማለል የሚያስፈልገው በፋራ ሙድ  ፋሽንሾው የመሰለ የፎቶ፣ የምርቃት ጋጋታና አበል መክፈል ሳይሆን ሰው- ሰው መሽተት ነው፡፡ እንኳን  ከበሸሻ፣ እንኳን ከዓድዋ ከየትም መጥተህ ሰው-ሰው ከሸተትህ የአዲስ አበቤን ልብ መግዛት ትችላለህ፡፡ በፋራ ፕሮፌሰርነት፣ ዱክትራናና የፎቶ ድርደራ፣ የአዲስ አበባን ህዝብ መሸወድ አይቻልም፡፡ ይቺ ይቺ በሸሻ ላይ ትሰራ ይሆናል ለአራዶቹ አዲስ አበቤዎች ግን አትሰራም፡፡ በመሰረቱ ፋራና አራዳ ያላቸው ልዩነት የዳይሜንሽን ስለሆነ ታችኛው ዳይሜንሽን ላይ ሆነህ ፕሮፌሰርም ዶክተርም ብትሆን ዕድገትህ አግድም እንጂ ሽቅብ ስላልሆነ እዚያው ዝቅተኛው ዳይሜንሽን ላይ ነው ክብጤዎችህ ጋር የምትተረማመሰው፡፡ ይልቅ አሁንም ብልጽግና ሆይ ከገባህ ዝም ብለህ ከመገገም ትንሽም ለመቆየትና አቢይ እጅግ፣ እጅግ የናፈቃትን ሌጅትሜሲ ለማግኘት ከአዲስ አበቤዎች ቀልቀል አድርገህ የመውጫ ስትራተጂ አዘጋጅ፡፡ መቼም ያራዳ ልጅ ሲፈጥረው ጭካኔ የለውምና የምትሾልክበትን ጠቅ ጠቅ  አድርጎ ሁሉንም ያመቻቸዋልና ከአዲስ አቤቤዎች ጋር ብትደራደር ይሻልሃል፡፡ 

መለስ እንኳን አዲስ አበባን ለአዲስ አበቤዎች እነተውለቸው ሲል ደነዙ በረከት እምቢ ብሎ ከባህርዳር አዕምሮው የቀነጨረ የቀነጨረውን ሰብስቦ ግማሹን  አዲስ አበባ በማስፈር የመንግሰትን መስሪያ ቤቶች ሁሉ በነሱ ጠቅጥቆ ሰውየውንም ለበሽታ ዳርጎ እስከወዲያኛው እነዲያሸልብ ከማድረጉም በላይ፤ ለእራሱ ለሱም፣ ለአማራውም፣ ለኢትዮጵያም ፣ ለኢህአዴግም ሆነ ለብልጽግና የማይጠቅሙ የቀነጨሩ  አማሮች ሰብስቦ ይሄው በራሱ ሰዎች ወህኒ ገብቶ በቁሙ ሞቷል፡፡ 

ስለዚህ ብልጽግና ሆይ ከአዲስ አበቤ ተጣልተህ የትም አትደርስም፡፡ ይልቅ በጊዜ ዘይድና ሰጥተህ በመቀበል ተግባባ አለበለዚያ የዛሬ ሳምንት ብልጽግና አሸነፈ ብለህ ብትለፍፍ አዲስ አበቤ ይናደድ ወይም ይገረም እነዳይመስለህ፡፡ ይልቁኑም ብልጽግና አሸነፈ ቢሉት አሿፊው አዲስ አበቤ  ምን የሚል ይመስልሃል? ታዲያ ምን ይጠበስ? ዓሳ በቤንዚን? ነው የሚልህ!

Filed in: Amharic