>

ባለሥልጣኑ የሳንሱር ሥራቸውን ጨርሰው  መጽሔቷ እንድትወጣ ፈቅደዋል፤ መጥፎ የአፈና ምልክት...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ባለሥልጣኑ የሳንሱር ሥራቸውን ጨርሰው  መጽሔቷ እንድትወጣ ፈቅደዋል፤ መጥፎ የአፈና ምልክት…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም

ትላንት ታትማ መውጣት የነበረባት ፍትህ መጽሔት ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ህትመቱ ተዘጋጅቶ ካለቀ በኋላ ማተሚያ ቤቶቱ ላሳታሚው እንዳይሰጥ በመንግስት መታዘዙን ገልጸዋል። በውስጡ የያዘው ጉዳይ በሕግ የሚያስጠይቁ ነገሮች ቢኖሩት እንኳ አሳታሚውን ድርጅት በአግባቡ በሕግ መጠየቅ ሲቻል ህትመቱን ማገድ ለምን አስፈለገ? በውስጡ ቅስቀሳ ነክ የሆነ የአንድ ፖርቲን አቋም የሚያንጸባርቅ ነገርም እንዳልያዘ ከራሱ ከተመስጌን ለማወቅ ችያለሁ። ተመስጌን እንደነገረኝም መጽሔቱ ወደ መንግስት ባለስልጣን ተልኮ ሙሉው ከተነበበ በኋላ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የታገደው ሕትመት እንዲወጣ ባለስልጣኑ መፍቀዳቸውን ለማወቅ ችያለሁ።ይሄ እጅግ መጥፎ ምልክት ነው። ባለስልጣኑ ባይፈቅዱ ኖሮ ህትመቱ አይወጣም ማለት ነው። እንዲህ ሳንሱር ነጻው ፕሬሱን ከማቀጨጭ አልፎ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትንም ይገድባል። አንዳንድ ሰዎች ካለማወቅም ሊሆን ይችላል የመጽሔቱን መታገድ ከታገደው የጠቅላዩ የቅስቀሳ ቃለ-ምልልስ ጋር ሲያነጻጽሩት አይቻለሁ። ገደቡ የተጣለው ለምርጫ ውድድር  ቅስቀሳ ለሚያደርጉ እጩዎች እና ፖርቲዎች እንጂ ዜጎች ሃሳባቸውን እንዳይገልጹ አይደለም።
Filed in: Amharic