>

ማንዴላ በብዕሩ ከእስርቤት የሚናፍቃት፣ ነፃዋ፣ የፋሺስቶች ድልአድራጊ፣ ውዷ፣ አዲስ አበባችን ... !! (አሰፋ ሀይሉ)

ማንዴላ በብዕሩ ከእስርቤት የሚናፍቃት፣ ነፃዋ፣ የፋሺስቶች ድልአድራጊ፣ ውዷ፣ አዲስ አበባችን … !!

አሰፋ ሀይሉ

የደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ ጥቁር አፍሪካውያንን ከተጠመዱበት የባርነት ቀንበር በጀግንነት ተፋልሞ ነፃ ለማውጣት ያለመውን ኤምኬ (ኡምክዌንቶ ዌ ሲዝዌ) የተባለ ህቡዕ የአርበኞች ዕዝ ለማቋቋም ሲያስብ፣ በቀጥታ የተጓዘው ወደ አዲስ አበባችን ነበር።
ማንዴላ በየካቲት ወር 1955 ዓ.ም. ላይ – ታላቅ የነፃነትን ብርሃን በባርነት ለተጠመደው ያገሩ ህዝብ ሊያዋልድ በመወሰን፣ ወደ ብርሃናማዋ ጥቁር አብረቅራቂ የነፃነት መዲና ወደ አዲስ አበባችን ሊያቀና በተነሳበት ወቅት፣ ከአዲስ አበባ ሊያገኝ ያሰበውን ወታደራዊ ሥልጠናና፣ የገንዘብና የጦር ቁሳቁሶች ድጋፍ ማንዴላ በራሱ የእጅ ፅሁፍ በእስርቤት የምስጢር ማስታወሻው ላይ ከትቦት እናገኘዋለን!! አዲስ አበባ ላይ ማንዴላን ያሰለጠነውን ሻለቃ በፍቃዱን ደግሞ ደጋግሞ ያነሳዋል።
አዲስ አበባችን የአፍሪካውያንን ነፃነት የፀነሰች የነፃነት አብራክ ነች! አዲስ አበባችን ልዩ ጥቅም ያማራቸውን ባንዳዎችና ፋሺስቶች ያልተገራ አምሮት በቁርጥቀን ልጆቿ የከበረ ደምና አጥንት ድል አድርጋ ያመከነች የኢትዮጵያችን የነፃነት አምባ ነች። አዲስ አበባችን የአፍሪካን አንድነትና ነፃነት የፀነሰች፣ ታላላቅ አፍሪካዊ ምኞት ያደረባቸውን ታላላቅ አፍሪካውያን አባቶች በክብር ለክብር ያበቃች የአፍሪካ የነፃነት መናገሻ፣ የአይበገሬነት መነሻና መዳረሻ ነች!
ዛሬም አዲስ አበባችን የጠባብ ኋላቀር ጎሰኛ ጅቦችን የልዩ ጥቅም አምሮትና፣ በዜግነት ፖለቲካ ስም ለዚያ ያልተገራ ፊንፊኒያም ኋላቀር የጎሰኞች ምኞት የሚያጫፍሩ ተለጣፊ ባንዳዎችን ድል አድርጋ፣ ከቅርብም ከሩቅም የሚመሠከርለትን የነፃነት ታሪኳንና የአይበገሬነት ሠገነትነቷን በተግባር ታረጋግጣለች!
አዲስ አበባችን የአድዋው ጀግና የእምዬ ምኒልክ እና የጀግናዋ የእቴጌ ጣይቱ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያረበበባት ዘላለማዊ የኢትዮጵያውያን የነፃነት ገፀበረከታችን ነች!
ፋሺስት አዲስ አበባ ላይ በአንድ ጀምበር 30 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ጠፍጭፎም የአዲስ አበባን፣ የኢትዮጵያን አይበገሬ ጀግኖች ክንድ መቋቋም አልቻለም! እያንዳንዷ የምንረግጣት የአዲስ አበባ መሬት ከጠባብ ዘረኛ ፋሺስቶች ጋር ተናንቀው ባለፉ አባቶቻችንና እናቶቻችን ደም የታጠበ፣ ታላቅ የደም ዋጋ የተአፈለበት የነፃነት አውድማ ነው! ዛሬም ሆነ ነገ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አዲስ አበባችንን ሊገዙ ያሰፈሰፉ ጠባብ ዘረኛ ፋሺስቶችንና ባንዳዎቻቸውን ይፋለማቸዋል!
የእምዬ ምኒልክ ሀገር አዲስ አበባ፣ ማንደላ በውቅያኖስ ውሃ በተከበበች የዘረኞች እስርቤት ውስጥ ሆኖ በብዕሩ የሚቃትትላት አዲስ አበባ – ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም – ጠባብ ዘረኞችንና ፋሺስቶችን ድል ታደርጋለች! የነፃነት አርማዋን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራዋን ከፍ አድርጋ በክብር ትቆማለች!
የፋሺስቶች ሁሉ መቀበሪያ፣ የጀግኖች ሁሉ መናገሻ፣ የታላቋ የነፃነት ምድር መዲና፣ የኢትዮጵያዊነት ውብ ሙዳይ፣ የፋራዎች አሠልጣኝ፣ የአራዶች መናኸሪያ – አዲስ አበባችን – ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic