>

ቀደም ሹምባሽ ኔርና ሎሚ ተዋሪድና!   (ጌቶች ነበርን ድሮ ተዋረድን ዘንድሮ!) ኦሀድ ቢንያም

ቀደም ሹምባሽ ኔርና ሎሚ ተዋሪድና!  (ጌቶች ነበርን ድሮ ተዋረድን ዘንድሮ!)
ኦሀድ ቢንያም

ጌቶች ነበርን ድሮ፣ ተዋረድን ዘንድሮ! የተለመደ የትግርኛ አባባል ነው፡፡ ዛሬ ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም. ላይ ትግራይን እና ህወሓትን አለማሰብ አይቻልም፡፡ 
 
ትግራይ ምርጫ የማይካሄድባት ክልል ነች፡፡ ትግራይ በፖለቲካው ረድፍ ውስጥ ወደ ኋላ ቆማለች፡፡ ከአስር ወራት በፊት ምርጫ ካላካሄድኩ ብሎ ህወሓት ከማዕከላዊ መንግስት ጋር የነበረውን ልዩነት የት እንዳደረሰው አንረሳውም፡፡ ምርጫውን ባጠናቀቀ ማግስትም አራት ኪሎ ያለው መንግስት ሕገወጥ እሱ ሕጋዊ መሆኑን ደጋግሞ አወጀ፡፡ አድናቂዎቹ፣ ደጋፊዎቹ እና አንዳንድ እጁ እንዳይጥላቸው የሚሳቀቁ ግለሰቦች የህወሓትን ምርጫ አደነቁ፡፡ ደገፉ፡፡ አንዳንዶች ከመስከረም በኋላ እኔና ዶ/ር አብይ እኩል ነን አሉ፡፡
ህወሓት ቦዩን ቀዶ ሊፈስበት አልቻለም፡፡ አራት ኪሎ ያለው መንግስት ሕገወጥ ነው ብሎ ክችች አለ፡፡ በብዙዎችም ተመከረ፤ ተሸመገለም፤ “አገር በሽማግሌ አትመራም፤” አለ፤ እና የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሰራዊትን እራት ጋብዞ የማወራረጃ ጽዋውን በባሩድ አደረገው፤ ከሌሎች ክልሎች ቀስሞ ያደራጀው “ሳምሪ” የወጣቶች ንቅናቄ አገልግሎቱን የማይካድራን ሰላማዊ ሰዎች በመጨፍጨፍ እንዲመረቅ አስደረገ፤ አግቶ የያዛቸው የመከላከያ አባላት ወንድሞቻችን ላይ ሲኖትራክ ነዳባቸው፤ እናም ታሪክ ተለወጠ፡፡ አሁን ላይ በመንግስት ላይ አለም አቀፍ ጫና እና እቀባ እየፈጠሩ ያሉት መንግስታት ደፍረው “ተደራደሩ” ብለው ማዘዝ የተሳናቸው እነዚህ ሶስቱ የመጀመሪያው ሳምንት የህወሓት ድርጊቶች ናቸው፡፡ የትላንቱ ጌቶች የዛሬዎቹ አሸባሪዎች የመደራደርን ክብር በብዙ ለቅሶ ቢፈልጓትም ሊያገኟት አልቻሉም፡፡
ህወሓት ሕጋዊ በሆነበት ክልል ወደ ሕገ-ወጥ ወንደበዴነት ተቀየረ፤ ሕገወጥ ነው ያለው የአራት ኪሎ መንግስት ሥራውን ቀጠለ፤ ዛሬ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቦታዎች (ከትግራይና ከተወሰኑ ክልሎች በስተቀር) ስድስተኛ የተባለው ምርጫ ይካሄዳል፤ ህወሓት በሰላማዊ መንገድ የመታገሉን አማራጭ አልፈለገምና ምሽግ ውስጥ ሆኖ “ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና አማራ ወረሩኝ፤” እያለ ጠበንጃውን ይወለውላል፤ አስር ወር ቢታገስ የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት ውጪ ማንን ይመርጥ ነበር? እውን በነዚህ አስር ወራት ራሱን አደራጅቶ ህወሓትን መገዳደር የሚችል ፓርቲ ትግራይ ውስጥ ሊፈጠር ይችል ነበር?
የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት በላይ የሚመካበት ድርጅት እንዳይኖር ተደርጎ ሁኔታዎች ከተሰሩ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ምንአልባትም ከሁሉም ክልሎች በተሻለ ሁኔታ ከፍተኛውን የበላይነት ወንበር ሊያሸንፍ የሚችለው ህወሓት ብቻ ነበር ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ ግን አልሆነም፤ የህወሓት ውድቀት ብዙ ነገር ያስተምረናል፤ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ከዚህ ቀውስ ከፍተኛውን ትምህርት መውሰድ ያለበት የትግራይ ክልል ሕዝብና የአመለካከት መሪዎቹ ተጋሩ ልሂቃኖቹ ናቸው፡፡ ከመቀሌ እስከ ጄኒቫ ያሉት ላይስተካከል የተበላሸውን ነገር መቼም መርሳት የለባቸውም፡፡
ትግራይን የመከራ ደሴት ያደረጋትን ፓርቲ አሁንም አድናለሁ ብሎ መንደፋደፍ ለከፋ ውድቀት ነው፤ ህወሓት ከሰራቸው ነገሮች የተነሳ ከዚህ በኋላ ወደ ህጋዊነት ለመምጣት የሚችልበት እድል ከዜሮ በታች ነው፡፡ እሱን መከተል ደግሞ የውድቀት ውድቀት ነው፤ ማንም ትግራይ ላይ ዘመቻ ማንሳት የፈለገ አልነበረም፤ የጦርነት ከበሮ ሲደልቅ የነበረው ህወሓት ብቻ ነው፡፡ በርግጥ ህወሓት አስቀድሞ ትግራይን እና ወያኔን ለማንበርከክ እየተሰራ ነው የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ስላጧጧፈው ይህን ለደጋፊዎቹ ማስረዳት ከባድ ነው፤ የሰሜን ዕዝን ሰራዊት ማጥቃቱን እንኳን ሴኮ እና ዶ/ር ደብረጺዮን ነግረውን ጀነራል ጻድቃንም አረጋግጠውልን አሁንም ህወሓት ጦርነት አልጀመረም የሚሉ ደጋፊዎቹን እናገኛለን፤ ራሳቸውን ከፕሮፓጋንዳ ሰለባነት ለማዳን ያላቸው አቅም በዘረኝነት፣ በአማራ ጠልነት እና በአድሎአዊነት ስለተበላ ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፤ ወገኖቻችን ናቸውና ከመታገስ ውጪ ምርጫ የለንም፡፡
የእልህ ፖለቲካ ውጤቱ ውድቀት ነው፤ ብታሸንፍም አላሸነፍክም፤ ብትሸነፍም አገር ተጎድታ ነው፤ ህወሓት ቅስቃሰዎቹ ከፌዴራል መንግስት አልፈው “ይቺ … አገር” እያለ የማጥላላት ዘመቻውን አጠናክሮታል፤ አማራ ጠልነትን የፕሮፓጋንዳው አይነተኛ ምሶሶ አድርጎ ቸክሎታል፤ የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ተስፋ እንዲቆርጥ እና በተለይም ከአማራ ሕዝብ ጋር ወደማይታረቅ የጥላቻ ምዕራፍ እንዲገባ ተደርጎ እየተነገረው ነው፤ ከጦርነቱ ወያኔን የመስበሩ ሥራ የተሳካ ቢሆንም የትግራይን ሕዝብ ከእልህ እና የጥላቻ ፖለቲካ አውጥቶ ሰላማዊ እና ተስፋ የሰነቀ ምዕራፍ ውስጥ ለማስገባት ከባድ ሥራ እና ሰፊ ጊዜ ይጠይቃል፡፡
ተጋሩን ከኢትዮጵያ እና አማራ ጠልነት ለመፈወስ ዋናው ማርከሻው ተቃራኒው የሆነው በጥላቻ ፋንታ ፍቅርን፣ በማግለል ፋንታ ማቀፍን፣ በመነታረክ ፋንታ ማዳመጥን፣ ትግራይ ላይ የተከሰተውን ቀውስ ለማስወገድ ወይም እንደምታውን ለመቀነስ የየተቻለንን ያክል አስተዋጽኦ ማበርከት፣ እና አስፈላጊውን የቁሳቁስ እና የግብአቶች ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያ አገሩ እንጂ ጠላቱ እንዳልሆነች ግልጽ ነው፤ ሆኖም ግን የታላቋ ትግራይ አቀንቃኞች ህልማቸውን ለማሳካት የተጠቀሙበት ዋነኛው እና አይነተኛው መሳሪያቸው ጥላቻ ጥላቻ እና ጥላቻ ብቻ ነው፡፡ በጥላቻ የተወጋን ሕዝብ በፍቅር ማሸነፍ ወይም በቅስቀሳ መማረክ ከባድ ነው፡፡ “ጠባችን ከወያኔ እንጂ ከትግራይ ህዝብ ጋር አይደለም፡፡” በሚል መንፈስ ከተገቢው የፍቅር ስጦታ ጋር መቅረብ አለበት፡፡
የትግራይ ልሂቃንም ትከሻ ላይ ከፍተኛው ኃላፊነት አለ፡፡ የአንድን ሉአላዊት ሃገር ህጋዊ ሰራዊት ላይ ጥቃት አድርሰህ እና በሲኖትራክ ሄደህባቸው ለድርድር መቀመጥ አትችልም፤ በከንቱ የጉሮ ወሸባዬ ጭፈራ እና ፉከራ ራስን እያታለሉ ጊዜ ማራዘሙ አገሪቷንም ክልሉን የበለጠ ከመበደል ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ ትግራይ በብዙ ችግሮች በተወጠረችበትና መከራዎች ፋታ በማይሰጡበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት ምክር አዘል አስተያየት መስጠቱ ከባድ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ግን ያስተዋልነውን የማካፈል ግዴታው አለብንና የምንችለውን ያክል መሞከር አለብን፡፡
ትግራይ ዛሬ መምረጥ አትችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሁለንተናዊው ቀውስ እድሜ እንዲያጥር የህወሓት መንገድ ከመተላለቅ ውጪ የትም እንደማያስኬድ ተገንዝቦ ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ ተለውጠው እንዲታዩ የሁሉም ዜጋ ርብርብና ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡
Filed in: Amharic