>

ስሙን ወደ «ብልጽግና» የቀየረው ኢህአዴግ፣ እና የአድርባይነታችን ልክ! (አሰፋ ሀይሉ)

ስሙን ወደ «ብልጽግና» የቀየረው ኢህአዴግ፣ እና የአድርባይነታችን ልክ!

አሰፋ ሀይሉ

ኢህአዴግ ስሙን ወደ ‹‹ብልጽግና›› ስለቀየረ እንደ ሌላ አዲስ ዓይነት ፓርቲ ለመቁጠር የሚዳዳቸው ሰዎች አሉ፡፡ እውነቱን ያለማወቅ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ የድርቅና ጉዳይ ነው፡፡ እና ጮሌነት መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ብልጽግና›› ያው ራሱ ኢህአዴግ አይደለም ብሎ ራስን በማታለል፣ ከበሰበሰው ከነባሩ ሰው-አራጅና ጎሰኛ ግንባር ከኢህአዴግ እና ሀገሪቱን ለውድቀት ከዳረገበት ኋላቀር ጎሰኛ ሥርዓቱ ጋር ከሚደረግ ከማናቸውም ዓይነት ትግል ራስን የማራቂያ ስልት ተደርጎ የተወሰደ የሽምጠጣ ስብዕና ነው፡፡ ጮሌነት ወይም ስልጠት፡፡ በምንም ስም ብንጠራው ዋናው ምክንያቱ ግን አድርባይነት ነው፡፡
በአድርባይነት ደዌ ክፉኛ የተጠቃ ሰው ጥቁርን ጥቁር፣ ነጭን ነጭ የሚል ጭንቅላት የለውም፡፡ ጉልበተኛው ነኝ ያለውን ነው የሚቀበለው፡፡ አድርባይ ጠያቂ ህሊናም የለውም፡፡ ነጭ ሆኖ ሳለ ለምን ጥቁር እንለዋለን? የሚል ጠያቂ ህሊና አልፈጠረበትም፡፡ የሰጡትን ያለጥያቄ መቀበል፣ የወረወሩለትን ትርፍራፊ ማጋበስ፣ እና ባለጊዜው ባለፈበት ሁሉ እየተከተሉ ማወደስና ማጫፈር ብቻ ነው የሚያውቀው የአድርባይ አንጎል፡፡
አድርባይ ምርጫ የለውም፡፡ ጊዜና ጥቅሙን እያሰላ ጉልበቱ ላመዘነው በሎሌነት ያድራል፡፡ አድርባይ በቋሚነት የሚወደውም፣ በቋሚነት የሚጠላውም አቋምና ፍላጎት የለውም፡፡ ጥቅምና ትርፉን እያሰላ፣ አደጋውን እየገመተ ነው የሚያጫፍረውን የሚመርጠው፡፡ የአድርባይ ህሊና ሰይጣን የበለጠ ከከፈለው፣ ለሰይጣን ለማደር ዓይኑን አያሽም፡፡ የአድርባይ ህሊና የራሴ የሚለው ነገር የለውምና፣ የሚፀየፈው ምንም ነገር የለም፡፡ ባለጊዜው የያዘውን ነገር ሁሉ ይይዛል፡፡ ባለጊዜው ያዘዘውን ሁሉ ይከውናል፡፡ ባለጊዜው የወደደውን ሁሉ ይወዳል፡፡ የአድርባይ ጭንቅላት ባዶ የገንዘብ ሳጥን ነው፡፡
የጊዜያችን የኢትዮጵያ አድርባዮች፣ በረዥም የህዝብ እምቢታና ትግል ሊወድቅ አንድ ሀሙስ የቀረው ኢህአዴግ አሁን እንደ አዲስ አንሠራርቶ ወደቀድሞ ገዳይነትና አሳሪነት ብቃቱ ተመልሷል ብለው አምነዋል፡፡ ስለዚህ ከጉልበተኛ ጋር ከመገፋፋት – ገዳዩና አፋኙ ኢህአዴግ ‹‹ነኝ›› ያለውን ሁሉ በመቀበል፣ ‹‹አይደለሁም›› ያለውን ሁሉ በመተው፣ የሚወደውን በማነብነብ፣ የሚጠላውን በመኮነን – በሠላም አርፎ መኖር ይቻላል ብለው – ይህን እንደ ብቸኛውና አዋጪው የህይወት መንገድ አድርገው ተቀብለዋል አድርባዮቻችን፡፡ ይህ የአድርባዮቻችን የዘወትር መመሪያ ሆኗል፡፡
አድርባይ ራሱን የሚሸንግልበት መንገድ ደግሞ እጅግ ገራሚ ነው፡፡ አድርባይ ለራሱ ህሊና እንዲህ ብሎ ይነግረዋል፡- ኢህአዴግ ከወያኔ ጋር አብሮ ተቀብሯል፡፡ አሁን ኢህአዴግ የሚባል ነገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ የለውጥ ፀሐይ ሲወጣ ኢህአዴግ አብሮ ቀልጧል፡፡ አሁን ያለው ‹‹ብልጽግና›› የተሰኘ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው፡፡ መሪውም ዘመናዊውና ተወዳጁ አብይ አህመድ ነው፡፡ እሱም ይመቸናል፡፡ ለዘለዓለሙም ይመራናል፡፡ ጎጇችን በላያችን ካልተደረመሰች በስተቀር እኛ ስለሌላው ጉዳይ ምን ያገባናል?! – ይህ ነው የዘመኑ የኢትዮጵያ አድርባዮች የህይወት ቀመር፡፡
ሁሉንም ሽምጥጥ አድርጎ መካድ፣ እያወቁ እንዳላወቁ መሆን፣ እያዩ መታወር፣ እየሰሙ መደንቆር፣ እና አንጠርጥረው ማንነቱን የሚያውቁትን ኢህአዴግን የዳቦ ስሙን እየጠሩ እሱ አይደለም፣ ሌላ ሰው ነው ብሎ መካድ፡፡ አዲሱ ኢትዮጵያዊኛ ጮሌነት፣ ችግር ውስጥ የማይከተው መስሎ አዳሪነት፣ አዲሱ የሠላም ኑሮ ዋስትና፣ አዲሱ የአድርባይነት ዘይቤ ይህ ነው፡፡ የገባንበት የአድርባይነት አረንቋ፣ ሰዋዊ የምንለውን ማንነታችንን ሁሉ እየዋጠብን ነው፡፡
የህሊና ሞት ሁለት ትውልድ ብቻ ይበቃዋል፡፡ አንድ ህሊናውን የቀበረ፡፡ ሁለት ደግሞ ህሊና የማይፈጠርበት፡፡ በሁለት ትውልድ ህሊና የሌለው አድርባይ ይፈጠራል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ዛሬ ሀቅና ሸፍጥን የሚለይ ህሊና በአድርባይነት ተቀብሯል፡፡ ይህ ህሊናውን በከርሱ ውስጥ የቀበረ ትውልድ ደግሞ፣ ነገ ሀቅንና ሸፍጥን የሚለይ ህሊናውን ጨርሶ የተነጠቀ ፕሮግራም የሚጫንበትን ሮቦት የሚያስንቅ፣ ቢልኩት ወዴት፣ ቢረግጡት አሜን የሚል፣ ከአድርባይነት በቀር እንጥፍጣፊ ህሊና ጨርሶ ያልፈጠረበት ትውልድ ያፈራል፡፡
በዚህ አያያዛችን ሳስበው፣ በአሁኑ ጊዜ ዲያቢሎስ ስሙን ቀይሮ ጦር ሰብቆ ቢመጣ፣ ፋሺስት ጣልያን ጦር ሰብቃ ስሟን ለውጣ ብትመጣ ራሱ – አሜን ብሎ በአዲሱ ስማቸው እያቆላመጠ አጨብጭቦ የሚቀበል ልበ-ደንዳና ህሊና-ድፍን ሰው ሞልቶ የተረፈበት አድርባይነት የመጨረሻ ከፍታው ላይ የደረሰበት ጊዜ ላይ የምንገኝ ይመስለኛል፡፡
ይህ ብልጠት አይደለም፡፡ ጮሌነት ብቻ ተብሎ የሚታለፍም ማህበራዊ ህፀፅም አይደለም፡፡ የጋራ የህሊና ህመም ነው፡፡ ከሰውነት በታች ራስን ማውረድ ግን ነው፡፡ ፈጣሪ ጨርሶ ይማረን፡፡ እና እውነትንና ሐሰትን ወደሚለይ፣ ህሊናና ይሉኝታ፣ ክብርና ሀቅ የሚባሉትን የሰው ልጅ ወርቃማ ስጦታዎች ወዳልተነጠቀ ሙሉ ሰብዓዊ ፍጡርነት ይመልሰን ማለት ነው፡፡ ፈጣሪ እንዲረዳን ከመጸለይ ሌላ በፈቃድ የመጣ የህሊና መበደን ምን ሊደረግ፣ ምንስ ዓይነት ሰው-ሰራሽ ፈውስ ሊመጣለት ይችላል?!
አንዳንዴ ሳስበው – ኢህአዴግን እንዲህ በአድርባይነት ሰጥ-ለጥ ብለን ተመችቶን እየተገዛንለት ያለው – በትክክል ኢህአዴጋዊ ኋላቀር የጎሳ ሥርዓቱ፣ እና ሀገሪቱን በጭካኔና አረመኔነት የሚያስተዳድርበት መንገድ በትክክል ለእኛ ኢትዮጵያውያን በሚመጥነንና በሚገባን የአገዛዝ መንገድ ይሆን እንዴ?! አውሮፓውያኑ – የእያንዳንዱ ህዝብ መንግሥት የራሱን የህዝቡን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ነው – የሚሉት እውነት ይሆን እንዴ? አለበለዚያማ እንዲት ለዚህ ጥንታዊ የጋርዮሽ በነገድ አለቆች ለሚመራ አውዳሚ ሥርዓት አሜን ብለን በፈቃደኝነት አንገዛም ነበር! እያልኩ አስባለሁ፡፡ ህዝቡ የሚጸየፈው አገዛዝ በላዩ ላይ ቢቋቋምበትማ እንዲህ ተመችቶት እያጨበጨበ አያቆየውም ነበር!
ይህን ስል አንድ የተለጠፈልን ስም ትዝ አለኝ፡፡ ለአድዋ ጦርነት አንድ ዓመት ብቻ ሲቀር – ከዛሬ 125 ዓመታት በፊት (በ1895 እ.ኤ.አ. ላይ) ነው፡፡ እምዬ ምኒልክ ኢትዮጵያን የዓለማቀፉ የፖስታ ኅብረት አባል ሀገር ለማስደረግ ማመልከቻቸውን ሲያስገቡ፡፡ የእኛን የአቢሲኒያኖች ጥያቄ የፖስታ ህብረቱ እያጤነ ባለበት ሠዓት – በከፍተኛ ግልፍት የተቃወመች አንድ ሀገር ነበረች፡፡ በወቅቱ ልትወረን አሰፍስፋ ለዓመታት ስታደባ የቆየችው ኢጣልያ፡፡ ኢጣልያ ኢትዮጵያ የፖስታ ድርጅቱ አባል መሆን የሌለባትን ምክንያት የገለጸችበት የተቃውሞ ደብዳቤ ብዙ ክብረ-ነክ ቃላትን የያዘ ነው፡፡ እንዲህ እያለች ትወርድብናለች ጣሊያን፡-
«[Abyssinia is a] nation of primitive tribes led by a barbarian» (ኢትዮጵያ በጫካዘመን አውሬያዊ አምባገነን የምትመራ የነገዶች ጥርቅም ነች!) — Cited by Harold Marcus)፡፡ «The Abyssinian above all things excels in cruelty both to mankind and animals» (ኢትዮጵያዊ ሲባል ከምንም ነገር በላይ በእንስሳትም ሆነ በሰው ላይ በሚፈጽመው ጭካኔ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ፍጡር ነው!) — Cited by Lord Hindlip፡፡
ያ የኢጣልያ አባባል እጅግ ክብረ-ነክ መሆኑ አጥንታቸው ውስጥ ዘልቆ የተሰማቸውና፣ የተሰጣቸውን የወረደ ማንነት ያልተቀበሉ ኢትዮጵያውያን – ኢጣልያ ያንን ተናግራ ዓመትም ሳትደፍን በአድዋ ተራሮች ላይ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ማንነታቸውን አስመስክረው አልፈዋል፡፡ አሁን ከመቶ ሃያ አምስት ዓመታት በኋላ እነዚያን የኢጣልያን ክብረ-ነክ ቃላት አስባቸዋለሁ፡፡
በትክክል ቃል በቃል ኢህአዴግ የሚባለው የዘመነ-ጋርዮሽ ግንባር – ኢትዮጵያን ያወረዳት ያኔ ጣሊያኖቹ እኛን ለመዝለፍ ወደተጠቀሙበት ጥንታዊ የጎሰኞችና የነገድ አለቆች ስብስብነት ነው፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያ የወረደች የነገዶች ስብስብ መሆኗን ብቻ አይደለም ለዓለም ያስመሰከረችው፣ ለሰው ልጅ ህሊና የሚቀፉ የሰው ልጅ እርዶች፣ ጭፍጨፋዎች፣ እልቂቶች፣ መፈናቀሎች፣ ውርደቶችና ጉስቁልናዎች የተስተናገዱትም በዚሁ በኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት ነው፡፡ እነዚያ ጣልያኖች አሁን ላይ መጥተው በእነዚያ ቃላት ቢዘልፉን – የምንመልስበት አፍ ያለን አይመስለኝም፡፡
አድርባይነት ህዝባዊ የኑሮ ዘይቤ ተደርጎ በተቆጠረባት «በዘመናይቷ» የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኢትዮጵያ፤ የጎሳና ነገድ፣ የጎጥና ዘርማንዘር ልክፍት በተጸናወተው የኢህአዴግ የጋርዮሽ ሥርዓት በምትመራው ኢትዮጵያ፤ ስሙን «ብልጽግና» ብሎ ለቀየረው ኢህአዴግ ስናጨበጭብ – በእነዚያው የነገድ አለቆች እየተመራን – ከመቶ ዓመት በፊት የተዘለፍንበትን ከሥልጣኔ የፀዳ ጎሰኛ ተናካሽ ሥርዓት ለማስቀጠል ፅኑ ፍላጎታችንን እየገለጽን ነው፡፡ ከተዘለፍነው በላይ ከፍ ብለን የመታየት ዕድሉን መቼም የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ እንግዲህ ከጮሌነታችን፣ ከአድርባይነታችን፣ እና ከጋርዮሻን ጋር ወደፊት! ከማለት ውጭ አውቆ የተኛን ምን ይሉታል? ፈጣሪ ይፍታን!
Filed in: Amharic