>
5:31 pm - Tuesday November 13, 7274

ኢዜማና የምርጫ ውጤቱ...!!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ኢዜማና የምርጫ ውጤቱ…!!!

ሞሀመድ አሊ መሀመድ
 
1 .ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ
2 .ፕ/ር በፈቃዱ ደግፌ
3 .ፕ/ር በላይ እጅጉ
4 .ዶ/ር አንማው አንተነህ
5. አቶ ክቡር ገና
6. አቶ አንዷለም አራጌ
7. አቶ ተክሌ በቀለ … ወዘተ አለመመረጣቸው አስደንግጦኛል። ይኸ ሽንፈት የኢዜማ ብቻ አይደለም። የነዚህ ምሁራንና አንጋፋ ሰዎች ሽንፈት አንደምታው ሰፊና እንደሀገርም አነጋጋሪ ነው። ይህን ከአጉል እልህ መጋባትና ከቂም-በቀል ስሜት ባሻገር አርቆ ማዬት ያስፈልጋል።
ህዝቡ ግን ለነዚህ አንጋፋ ዜጎች ለምን ድምፅ ነፈጋቸው? የኢዜማ የፖለቲካ አስተሳሰብ ችግር ነበረበት? አደረጃጀቱ፣ አመራሩና አሰላለፉ ምን ይመስል ነበር? ኢዜማ ራሱን በቅጡ መፈተሽ እንዳለበት ይሰማኛል። ከዚህም ብዙ መማር ያስፈልጋል፤ ይቻላልም።
ይህም ሆኖ፣ ኢዜማ በሰለጠነ መንገድ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል አስተምሯል። የኢዜማ አባላት የሰላማዊ ትግልን ምንነት በተግባር አሳይተዋል። በዚህ ሊኮሩ ይገባቸዋል። እኛም አድናቆትና ምስጋናችንን ልንቸራቸው ይገባል።
በግሌ ኢዜማ ላይ፣ ገና ከአደረጃጀቱ ጀምሮ ድምፀ-ተኣቅቦ (reservation) ነበረኝ። በሂደትም የአንዳንድ አባላቱ (ልጆቹ) “የማንአህሎኝነት” አባዜና ከሌሎች ጋር የገቡበት አጉል “እንካሰላንቲያ” ያልተገባ ዋጋ ያስከፈላቸው ይመስለኛል። ከዚህም፣ ከሀገራዊ አጀንዳ በመለስ አጉል ብሽሽቅና ለከፋ ለፖለቲካ ፓርቲ እንደማይመጥን መማር ይቻላል።
እነዚህ ክፍተቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አሁንም ኢዜማዎች በዚህ ምርጫ “አሸናፊዎች” መሆናቸውን መጠራጠር የለባቸውም። ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ውድድርን ከማለማመድ አንስተው፣ ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ ያደረጉት አስተዋፅኦ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በህዝብ ተመርጠው ፓርላማ አለመግባታቸው ይህን እውነት አይቀይረውም። ትግል የሚደረገውም በፓርላማ መድረክ ብቻ አይደለም። ከዚያ በመለስ፣ በፓርቲ ደረጃ ለዴሞክራሲያ ሥርዓት መጎልበት ብዙ መሥራት ይቻላል።
“ነገም ሌላ ቀን ነው!”
Filed in: Amharic