>

" በዚህ ምርጫ ተሸናፊና አሸናፊ አይኖርም!!!"  (በድሉ ዋቅጅራ)

” በዚህ ምርጫ ተሸናፊና አሸናፊ አይኖርም!!!”

 በድሉ ዋቅጅራ

ህዝቡ ድምጹን ለኢትዮጵያ ሰጥቷል ፤ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ኢትዮጵያን እየመረጡ ነው፤ በዚህ እንደሚቀጥሉና ይህን ምርጫ በስኬት እንደምንወጣው የብዙዎቻችን ተስፋ ነው
.
ከድምጽ አሰጣጡ ቀደም ባለው ጊዜ በነበረው ሂደት የታዩ ችግሮች እንዳሉ ሆነው፤ የስድስተኛው ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሰላማዊ ሆኖ እየተካሄደ ነው፡፡
.
የምርጫ ስኬት በሶስት አካላት ላይ ይወድቃል፤ በምርጫ ቦርድ፣ በመራጩ ህዝብ እና በተወዳዳሪ ፓርቲዎች፡፡
.
የዚህ ምርጫ የመጀመሪያው ስኬት ብርቱካን የምትመራው የምርጫ ቦርድ ነው፤ እንደተጠበቀው የገጠመውን ችግር በተቻለ ፍጥነት እያረመ፣ እርምጃም እየወሰደ የተሻለ ምርጫ እያካሄደ ነው፡፡ የመጨረሻውን ውጤት ለባለቤቱ ለህዝብ እሲኪያሳውቅ ድረስ በዚሁ እንደሚቀጥል የእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የብዙሀን እምነት ነው፡፡ ምክንያቱም እስካሁን እንደታየው የሚሰራው ለመንግስት (የብልጽግና ፓርቲ) ወይም ለተፎካካሪ ፓርቲዎች አይደለም፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡
.
ሁለተኛው የዚህ ምርጫ ስኬት መራጩ ህዝብ ነው፡፡ በብሄር ተኮር ግጭት ሲሞት፣ ሲሰደድ፣ ንብረቱ ሲወድም፣. . .  የከረመው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ትላንትናና ዛሬ በድምጽ አሰጣጡ ጨዋነቱን አሳይቷል፡፡ ይህ የሚያተራምሰውን ግጭት ምን ያህል እንደተጠየፈውና እንደማይፈልገው የሚያሳይ ነው፡፡ እድሜ ያጎበጣቸው ሽማግሌዎች የሚመርጡት መጪው ትውልድ ለሚኖርባት ኢትዮጵያ ነው፡፡ ነፍሰጡሮች የሚመርጡት ልጆቻቸውን በሰላም ተገላግለው ስለሚያሳድጉባት ሀገር፤ ኢትዮጵያ ነው፡፡ የተራቡ የሚመርጡት ዳቦ በልተው የሚያድሩባትን ኢትዮጵያ ነው፡፡ . . . . በአጠቃላይ ህዝቡ ቀኑን ሙሉ ተሰልፎ፣ በዝናብ በስብሶና ተርቦና ተጠምቶ ድምጹን የሰጠው ለኢትዮጵያ ነው፡፡
.
ሶስተኛውና ይህን ምርጫ በስኬት እንዲቋጭ የሚያደርገው የተወዳዳሪዎች የምርጫውን ውጤት አቀባበል ነው፡፡ መንግስትን ጨምሮ የሁሉም ተወዳዳሪዎች ምርጫም ኢትዮጵያ መሆን አለባት፡፡ ኢትዮጵያን መምረጥ ማለት ደግሞ፣ የምርጫውን ውጤት በጸጋ መቀበል፤ ችግር ካለ ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ፣ በህጋዊ መንገድ ችግሩ እንዲስተካከል ማድረግ ነው፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች የሚወዳደሩት የኢትዮጵያ ህዝብ በመረጠው መንግስት እንዲተዳደር ነው፡፡ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን መምረጥ ማለት፣ ይህን ተገንዝቦ የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ ማክበር ማለት ነው፡፡ ‹‹ፓርቲዬ ካላሸነፈ›› ብሎ ለነውጥና ግጭት መንደርደር ኢትዮጵያን አለመምረጥ ነው፡፡
.
እስካሁን በምንመለከተው ተወዳዳሪ ፓርቲዎችም ኢትዮጵያን እየመረጡ ነው፤ በዚህ እንደሚቀጥሉና ይህን ምርጫ በስኬት እንደምንወጣው የብዙዎቻችን ተስፋ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሁላችንም ኢትዮጵያን ስንመርጥ፣ ከአምስት አመት በኋላ ከአሁኑ የተሻለ ምርጫ የምናኪሂድባት፣ የተሻለች ኢትዮጵያ ትጠብቀናለች፡፡
Filed in: Amharic