>

…. ከምርጫ በኋላ (መንግሥቱ ደሳለኝ)

…. ከምርጫ በኋላ

መንግሥቱ ደሳለኝ


ምርጫው መንግሥት መስርቶ፣ቅራኔ አረጋግቶ፣ሠላም አስፍኖ፣የተረጋጋ አገርና ህዝብ ካሰፈነልን እሰየው ነው፡፡ያ ካልሆነ ደግሞ ምርጫ በራሱ ግብ አይደለምና ኪሳራ ሆኖ ይመዘገባል ማለት ነው፡፡፡፡የምርጫ ኪሳራ የድሃ አገር ምሱ ነው እንደሚሉት አይነት፡፡ምርጫ የህዝብ ቅቡልነት ካጣ፣የፓርቲዎች ጉምጉምታ ከበዛ ለበለጠ ግጭትና አመፅ ካነሳሳ እርባና ቢስ ነው፡፡የምርጫ ውጤት ከምርጫ በፊት የነበረን ሁኔታ ከመለሰ ምርጫው የሞኝ ገበያ ነው፡፡ ሁሉም ሊመስለው ይችል ይሆናል እንጂ ያተረፈ የለም – ሁሉም ሙልጭ ወጥቷል፡፡

ኢትየጵያ ችግሯ ብዙ ነው፡፡

 • ቅጥ አምባሩ የጠፋ  መቶ ትንንሽ ኤሊት ፖለቲከኞች፣አክቲቪስቶች፣አስመሳይ ምሁሮች፣/ለችግሮች በጋራ ለመቆም አለመቻል/
 • የፖለቲካ አለመረጋጋት፣የሰብአዊ መብት ጥሰት፣የፍትህ ዕጦት፣የዴሞክራሲ መቀጨጭ፣
 • ድህነት፣ሙስና፣የኑሮ ውድነት፣
 • በሽታ፣የስራ አጥ ብዛት፣
 • የውጭ ምንዛሪ ዕጦት፣
 • የውጭ ንግድ ደቃቃነት፣
 • አናሳ ሃገራዊ ቁጠባ፣
 • ኤኮኖሚን ያልመጠነ የህዝብ ብዛት፣
 • የኢንዱስትሪ አብዮት ለማካሄድ አለመቻል፣
 • የምዕራቡ አለም ቀመስ ቴክኖሎጂያዊ ሽግግር መራቅ፣
 • የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት፣
 • ጦርነት …… ናቸው፡፡የችግራችን ብዛቱ!!!

በተለይ ጦርነቱና የውስጥ አለመረጋጋቱ አንዳንዴ ኮንቬንሽናል እንዳንዴም የሽምቅ እየመሰለ እራሱን ይገልፃል፡፡የሽምቅ ተዋጊ ሚስጥራዊ እና ለጠላትም በማይገባ ሁኔታ ጥቃትን ለመፈፀም የሚያልም ነው፡፡የሽምቅ ተዋጊ ሁኔታዎች ለእርሱ ያደሉና ውጤት የሚያስመዘግብ ከሆነ ብቻ ጥቃትን እንደሚፈፅም ይታመናል፡፡ጥቃቱም ድንገት ፣ፈጣን፣አላማውን የሚያሳካ እና በአጭር ጊዜ የሚፈፀም ይሆናል፡፡የሽምቅ ተዋጊ ከውጊያውም በላይ የፈጣን ሰአት ሩጫ ክሕሎት ታዋቂ ነው፡፡ከጀርባ ማጥቃት መሰረታዊ ባህሪው ነው፡፡በምስራቅ አጠቃቅሶ በምእራብ ይወጋል፡፡በሰሜን አጓርቶ በደቡብ መሬት ነክሶ ያጠቃል፡፡እንቅስቃሴው ምንጊዜም predictable/ተገማች እንዲሆን አይሻም፡፡የጠላት ጀርባ ለሽምቅ ተዋጊ ምንጊዜም ግንባሩ ነው፡፡በታሪካዊ ግምገማ የሽምቅ ተዋጊ የመጀመሪያውን ደረጃ /phase በርትቶ ከተሻገረ ምናልባትም ከ 15 በመቶ እስከ 25 በመቶ የሆነውን ህብረተሰብ ክፍል በእጁ ካስገባ እርሱን የመቆጣጠሩ ተስፋ ይመክናል ይባላል፡፡ሞተ ሲሉት ይኖራል፣አለ ሲሉት ይጠፋል፡፡ ይህ ደግሞ ከቬትናምም ከቻይናም ሳይሆን እዚሁ አገር ቤት ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈፅሞ አይተነዋል፡፡ታሪክ ራሱን ሊደግም እየተንደረደረ እንዳይሆን ! 

አዋቂዎች ብሄራዊ ዲያሎግን እንደ ቅራኔ መፍቻ እና የፖለቲካ ለውጥ ማሳለጫነት አይነተኛ ፍቱን መድሃኒት አድርገው ያቀርቡታል፡፡በጣም በበርካታ አገሮች ግጭቶችን ለመፍታት ተጠቅመው ተሳክቶላቸዋል፡፡ብሄራዊ ዲያሎግ 

በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑ ቢታወቅም በትንሹ ግን የሚከተሉትን ካካተተ ለስኬት ያቀርባል ይላሉ፡፡እነርሱም፡-

 1. አካታችነት፣/የባለ ድርሻ አካላትን/፣
 2. ግልፅነት እና ህዝባዊ ተሳትፎን ማስፈን፣
 3. ወሳኝ አጀንዳዎችን   የመምረጥ ሁኔታ፣ 
 4. ግልፅ ሃላፊነት፣በልኩ የተሰራ መዋቅር ደንብና ፕሮሲጀር፣
 5. እኔ ነኝ ያለ በሁሉም ቅቡልነት ያለው አወያይ፣
 6. ውጤቶችን ወደ ተግባር የመለወጥ መንገዶች/ዘዴዎች ናቸው፡፡እነዚህን ይዘን ብንጀምረውስ፡፡ምን ይከብዳል???
Filed in: Amharic