ጌታቸው ሽፈራው
1) ፌስቡከኛው እርስ በእርስ የተለማመደውን መፈራረጅ፣ እርስ በእርስ የለመደውም መሰዳደብ አደባበይ ይዞት መጥቶ ሚሊዮኖችን በጅምላ እየሰደበበት ነው። ሕዝብን! ነውር! አሳዛኝ! ይህን እያደረገ ያለው ደግሞ ገና ምርጫ ቦርድ በይፋ ውጤት ሳያሳውቅ ነውኮ። ይህን ፍረጃውን ስድቡን የሚያወርደው ደግሞ ምርጫ አይጠቅምም ሲል የከረመውም፣ ያልመረጠውም ሌላ ሀገር ያለውም ነውኮ። ይሄ ኮሽኮሾ የሆነ ፌስቡከኛ ሕዝብ ሲሳደብ ማየት እጅግ ያሳዝናል። ገና ድል ተገኘ ሲባል ሳያጣራ እልል፣ ችግር መጣ ሲባል በትንሹም በትልቁም ሕዝብን ጭንቀት የሚያስይዝ፣ የሚያስበረግግ ብረት ምጣድ የሆነ፣ ቶሎ ሞቆ ቶሎ ትሽሽሽሽ ብሎ የሚበርድ ፌስቡከኛ ነውኮ ሕዝብን የሚፈርጀው፣ ሕዝብን የሚሰድበው። ውጤቱ ጠቅለል ብሎ እስኪመጣ እንኳን አይጠብቅም። ሌሎቹ ሲደነፋ ከርሞ፣ በሶስት ሳምንት ብትንትናው የወጣን ኃይል እንኳን አይወቅሱትም። እምቅ አድርገው የሚችሉት አላቸው። በእኛው ሰፈር ሀዘንም ደስታም የማይችለው ብዙ ነው። ይህኛው በምርጫ ውጤት ጅማሮ ሕዝብን ይሰድባል። ነውር። አሳፋሪ። እንጭጭነት!
2) ገና የምርጫ ውጤት በተናጠል ሲለጠፍ ሕዝብን “ወደሽ ከተደፋሽ……” ቅብጥርጥስ ይለ ሕዝብ ግለሰብ አይደለምኮ። ሚሊዮኑ የተለያየ ፍላጎት፣ የተለያየ መረዳት አለው። አንዳንዱ ፈልጎት፣ አንዳንዱ ተሸውዶ፣ ሌላው ተጭበርብሮ፣ ሌላው እታገላለሁ በሚለው ድካም፣ …ቀሪው…… ሊመርጥ፣ ላይመርጥ ይችላል። ይህን ሁሉ በአንድ ያሰበ አስመስለህ ካልፈጨሁህ ትለዋለህ?
ገና ምርጫ ሳይጠቃለል “ከአሁን በኋላ የፈለገ ቢያደርገው አያገባኝም” ይላል። ኧረ! ኧረ! ለአምስት አመት ብቻ ነበር እንዴ የሕዝብ ጉዳይ ያገባኛል ብለህ ኮንትራት የወሰድከው? “ሕዝቤ” ቅብጥርጥስ ስትለው የኖርከው በአንድ ቀን ምርጫ፣ በተወሰኑ ድርጅቶች ውድድር፣ ከራሱ በወጡ ልጆች መዝነህ ልትወረውረው ኖሯል?
3) “ሕዝብ ይሳሳታል አይሳሳትም” እያልክ ደግሞ ትመፃደቅልኛለህ? ኧረ ደግሞ ይሄ ኮሽኮሾ፣ ግንፍልተኛ፣ ሞቆ በረድ ፌስቡከኛ ሕዝብ ይሳሳታል አይሳሳትም እያለ ለመከራከር ሞራል የት አግኝቶ ነው? ራሱ ፌስቡከኛው ስራው ማሳሳት አይደለም? ከማንም ገፅ ያገኘውን ፎቶ ሲያረባ፣ ከየትም ያገኘውን ሰበር ዜና ሲያሰራጭ፣ ችግር ሲፈጠር ሕዝብን ከማረጋጋት ይልቅ ማሸበርን ስራው ያደረገው ፌስቡከኛ “ሕዝብ ተሳሳተ፣ አይ ሕዝብ አይሳሳትም” የሚል ክርክር ጭብጥ ሊይዝ ሞራል አለው? ትንሽ ድል መጣች ሲባል የያዘውን ጥሎ የሚዘል፣ ችግር ሲመጣ ከፊት ያለውን በሙሉ ዘንግቶ የሚቆዝም፣ የሚጓተት፣ ወገኑን ገፍትሮ የሚሄድ፣ የኋሊት ሽምጥ የሚጀምር ፌስቡከኛ ስለሕዝብ መደናገር፣ ስለ ሕዝብ መሳሳት፣………የማውራት ሞራል የት አመጣ? ሕዝብን ራሱን በአውራጃ፣ በዞን፣ በወረዳ፣ በቀበሌ የሚከፍል ሙትቻ ፌስቡከኛ ቆራጥ ታጋዮቹን ወክሎ ሊወቅሰው ከየት ሞራል አመጣ? አቤት ድንቁርና!
4) በምርጫ የቻሉትን አድርገው፣ የደረሰባቸውን ጫና አውቀው፣ የመጣውን የተቀበሉት ታጋዮች ያሉትን አይተሃል? አንብበሃል? ላይ ላዩን አይተኸው ይሆናል። ለሕዝብ ታግለው፣ የቻሉትን ያደረጉት በትግል፣ በሕዝብ ተስፋ አልቆረጡም። ሕዝብን አልሰደቡም። “ከአሁን በኋላ እንደፈለክ” አላሉም። የወጡበት ነው። ባሕራቸው ነው። ይህን ሁሉ ጫና የተቀበሉት ለሕዝባቸው ብለው እንጅ ለራሳቸው ብለው አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶቹ በግልም ደውለህ ጠይቃቸው ሕዝባቸውን ያደንቁልሃል። ካደን አይሉህም። ፌስቡከኛው ግን “ቀሩብህ” ብሎ ሕዝብና ልጆቹን ሊነጣጥል፣ ከሕዝብ በላይ ልጆቹን ሊሰቅል ሲፍጨረጨር ታየዋለህ። ጉድ ነውኮ። ተአምር ነው። እነሱኮ ወደ ትግል የገቡት ሲቀናቸው “መጣሁልህ” ሲሸነፉ “ቀረሁብህ” ሊሉት አይደለም። አይሉትም። ከአንተ የሚለዩት በዚህ ነው። ሕይወታቸውን ሊሰጡለት ነው የገቡት። ከራሳቸው በላይ ሕዝብን አክብረው፣ የሕዝብን ጥቅም አልመው ነው የገቡት። ልጆቹን ለወላጆቹ “ቀሩብህ” ትላለህ? ወደ ትግሉ ሲገቡ ከሌላው ቀድመው፣ ያላቸውን ትተው፣ የሚመጣባቸውን ይምጣ ብለው የገቡትኮ ችግር ሲገጥማቸው ሕዝብ እንዲሰደብባቸው አይደለም። ለሕዝብ መከታ፣ አለኝታ፣ ክብሩን አስጠባቂ ለመሆን ነው የገቡትኮ። ትንሽ የተሳሳቱ ቢመስሉህ ደግሞ እነሱውን ትኮንናለህ። የመሰላሰያ ጊዜ የምትሆን ደቂቃ ሳትወስድ ሕዝብን ከዱት ብለህ ባንዳ ታደርገቸዋለህ።
5) በየአካባቢው ውድድር ሲካሄድ የመረጡ አሉ። ለምሳሌ ገዥዎች 402 ለ390 “አሸንፈዋል” ተባለ እንበል። የፌስቡከኛው ድፍረት ለጉድ አይደል መቸስ? ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን 402 የተባሉትን ስደብ። ምክንያትም አትጠይቃቸው። ግድ የለም። እየተዋከቡም፣ ብዙ ጫናም ችለው አንተ የምትወደውን መርጠው ድምፃቸው “ተሸናፊ” ለሆኑትስ ክብር የሚባል የለህም? ያልመረጠም አይሰደብም። መርጠው ተሸነፉ ከተባሉት መካከል ራሳቸው የሕዝብ ልጆቹኮ አሉበት። ተመራጮቹም የዛች ተሸነፈች የተባለችው ድምፅ አካል ናቸው። ታዛቢዎቻቸውን አስበሃል፣ ተጨቅጭቀው አይሆንም ብለው እነዚህን የመረጡትን አስበሃል? የዛ ሕዝብ አካል አይደሉም? መገለጫው አይደሉም?
ግን ብልግናው ተለምዷልና ቀጥልበት። መርጠው በ12 ድምፅ የተሸነፉትን፣ የታገሉትን አብረህ ጭዳ ታደርጋቸዋለህ? እንቀጥል። ተዋክበው፣ አትመርጡም ተብለው፣ ድምፃቸው ብልሽት አለበት ተብሎ ያልተቆጠሩ፣ የተጭበረበሩ 20ና 30 ድምፆች ኖረው፣ ግን በስርዓቱ ችግር የምትፈልገውን ኃይል ባለመምረጣቸው አሸናፊ አልሆንክም እንበል። እነዚህ የባከኑ የአንተ ወገን ድምፆች ቢጨመሩ ኖሮ ደግሞ ያን የሰደበውከውን በሙሉ ልታሞግስ ነበር። በ390 ታጋይ ድምፅ የሰደብከውን፣ በ13 ድምፆች ቢጨመርልህ ኖሮ ልታሞግሰው ነበር? በአንድ ድምፅ ልዩነት ሕዝብን ስትወግርና ስትሰድብ? የመረጠህን አመስግን። አድንቀው። አክብረው። ይገባዋል። በብዙ ጫና ያገኘው ድል ነው። ባልመረጠ ሰበብ ዝም ብሎ ሕዝብ አይሰደብም።
6) ኧረ እንዲያው በፈጣሪ አይደለም ሚሊዮን ሕዝብ፣ የሕዝብን ስነ ልቦና የማይወክሉ ጥቂቶች የሚሰሩትን ትክክል ያልሆነ ነገር ሽንጥህን ገትረህ ስትከላከል አይደለም ወይ የከረምከው? አንተዋወቅም? የሕዝብ ስም ይጠፋል ተብሎ ለስንቱ ዘብ አልተቆመም? ውስጥህ እያወቀው ሕዝብ ላይ አጀንዳ እንዳይያዝ እየተባለ፣ አጀንዳ እንዳይያዝ እያልን የማናውቃቸውን፣ ግን ለሕዝብ ተብሎ እንዳልሸፋፈንን አሁን በደፈናው ሕዝብ “ይበለው፣ ወደሽ ከተደፋሽ” ይባላል? ሁለት ሶስት ሰዎች የሰሩት ሕዝብን ያሰድባል እየተባለ እንዳልተሸፋፈነ በብዙ ምክንያት ችግር በገጠመው ነገር ሕዝብ በጅምላ መስደብ ምን የሚሉት ታጋይነት ነው?
7) የሚደረገው ምን መሰለህ? ስታሸንፍም ስትሸነፍም ችግር ሲገጥምህም መልካም ሲሆንልህም ቅጥ አለው። ለደስታውም ለሀዘኑም ልክ አለው። ስሜት ቤት አይሰራም ይባላል። ፖለቲካው ላይ ሲሆን ደግሞ የተሰራ ያፈርሳል። መልካም ነገር ሲገጥምህም፣ መጥፎው ሲመጣም ስሜትን ዋጥ፣ እምቅ ማድረግን ይጠይቃል። ለቀጣዩ ስለሚጠቅም ያሸነፍክበትንም የተሸነፍክበትንም ምክንያት በደንብ ትቆጥራለህ፣ ለምን፣ እንዴት ትላለህ። ቀጣዩን ታሰላለህ። የምርጫው ጉዳይ ላይ፣ መጀመርያ ነገር ብዙው ነገር ቢያልቅ መልካም ነው። ከጅምሩ ለደስታም ለሀዘንም የሚሆን ምክንያት ይጠፋል ማለት አይደለም። ግን ያዝ ማድረግ ተገቢ ነው። ከዛ ጠቅለል አድርጎ ሲገለፅም ስድብ ፍረጃ አይደለም የሚያስፈልገው። ካሸነፍክ “ለምን ድምፅ ሰጠኝ፣ ለምን ድምፅ ነሳቸው?” ብለህ ትጠይቃለህ። ለቀጣዩስ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ፣ ስላሸነፍኩ የተሸናፊዎች ቀጣይ ስራ ምን ይሆናል? ብለህም ታሰላስላለህ። ከተሸነፍክ ደግሞ “ለምን ተሸነፍኩ፣ እንዳልሸነፍ ምን አደረጉብኝ? ምን ያላደረኩት አለ? ምን ተፈጠረ? ብለህ ትተነትናለህ! ለቀጣይ ትዘጋጃለህ!
ልድገምልህ!
“ታጋይ” ነኝ ካልክ እየተሸነፍክም፣ እየወደክ እየተነሳህም ለሕዝብ ነው የምትታገለው። ሕዝብ እንዲታገልልህ አይደለም። ሕዝብ ሰፊ ነው። የምታደራጀውም፣ ሀሳብህን የምታሰርፅለትም፣ እንዲመርጥህ የምታደርገውም አንተው ነህ። ሌላ ተቀናቃኝም አለብህ። በሕጉ ላይመራ፣ በሴራ ሊያበላሽብህ እንደሚችል ካላሰብክ ከንቱ ነው።
መሳሳትም መንቃትም አንፃራዊ ሆኖ ሕዝብ ውስጥ ይፈጠራል። ግን! የተደራጀ፣ ስልጣን የያዘው ኃይል ቀርቶ የአንተ የፈጠራ ወሬኮ ሕዝብ ያሳስታል። ያስደስታል ወይ ያሳዝናል። ፌስቡክ ላይ እንኳን ስንቱ የተሳሳተ ወሬ ለሕዝብ እውነት መስሎ ቀርቷል። ስንት አሳስቷል። ኃይል፣ ስልጣን ያለው ሊያባብል፣ ሊያሳስት ይችላል። ታጋይ ከሆንክ ያንተ ዋናው ሚና እንዳይሳሳት፣ እንዳይታለል፣ ያልሆነው እውነት እንዳይመስለው መጣር ነው።
እኔምልህ?
ስንቴ ሕዝብን አደነክ? ስንቴ ይህ ቅኔ ሕዝብ አልከው? ስንቴ ከአሁን በኋላስ ብሞትም አይቆጨኝ አሰኘህ? በየጊዜው ትገለባበጣለህ? በሰልፍ አድንቀኸው በምርጫ የምትረግመው፣ በጦርነት ወድደኸው በኮሮጆ የምታወግዘው ችግሩ ከሕዝብ ቢሆን ነው? አይደለም!
ስንቴ ደብረማርቆስን አወገዝክ? ስንቴ አሞገስክ? ስንቴ ሸዋን ወቀስከው? ስንተ አደነከው? ስንቴ ጎንደርን አሞገስከው? ስንቴ ኮነንከው? ስንቴ ደሴን ረገምካት? ስንቴ ወቀስካት? ስንቴ ካድሬ ሲሰለፍ፣ ስንቴ ካድሬን ስትቃወም ተፈራረክባት? አሁንም? ነገም ትቀጥለለህ አንተስ!
ዋናዎቹ ታጋዮች፣ ተወዳዳሪዎቹ፣ ድምፅ ሆነውት ድምፅ ያላገኙት “ትግሉ ይቀጥላል!” እያሉ፣ ሕዝብ በደለን ሳይሉ አንተ “ቀረብህ፣ እንደፈለገ ያድርግህ ካልክ አንተ ሰሞነኛ ነህ። እንደነሱ አልቆረጥክም። ዘሪሁን ገሰሰ ከምርጫው በኋላ ከክልል ውጭ ችግር ለሚደርስባቸው ወገኖቹ ድምፅ መሆን ቀጥሏል። አንተ “ኧረ ከዚህ በኋላ ለዚህ ሕዝብ” ብለህ ተስፋህን ቆርጠሃል። አየህ ከታጋዮቹም ከሕዝቡም ጋር አትተዋወቅም።
ኧረ! ኧረ! አንተኛው ደግሞ ምኑ ጉዱ ነህ? ማዶ ተንቤን የገቡትን ፅናት እያደነክ ሰማሁህ ባለፈው? አይደል። ሌላ 17 አመትም ቢሆን እንታገላለን ብለው ገቡ ብለህ መስሎኝ ያደነካቸው? ተሸንፈው ብቻ ሳይሆን ርሃብም፣ ጦርነትም ጠርተውበት፣ ርዛት አምጥተውበት፣ ጥለውት ባዶ አድርገውት ሄደው እንኳን ስታደንቅ ነበር መሰለኝ። ሕዝብን ጥለው፣ ሕዝብም ትቷቸው ነውኮ ዋሻ የተደበቁት። አሁን ለአንድ ቀኑ ምርጫ እየተማረርክ ስለ ትግል ታወራለህ፣ በዛኛው በኩል ደግሞ በሕዝብ ላይ መአት አምጥቶ የሸሸ፣ ሕዝብም ያልተከተለውን ታደንቃለህ! ኧረ ያደናግርህ የሚያደናግር!
ለማንኛውም ሕዝብ አይሰደብም። አንተ የምታደንቃቸውም የወጡት ከሕዝብ አብራክ ነው። የምትመገበው እንኳን ከስንት አረም ተነቅሎበት ነው እህልም፣ ምግብም የሚሆነው። ዝም ብለህ ከተውከው አረሙ የአንተውን ንብረት ሊውጠው ይቀርባል። አንተ ራሱ አረም ከዘራህ፣ ማረም ካቃተህ፣ እህልና አረም ካለየህ ደግሞ የራስህ ችግር ነው!
ሕዝብ ግን አይሰደብም። ደግሞ ጥቂት ጊዜ ቆይተህ ስታሞካሸው ትገኛለህ።
እነ እስክንድር እስር ቤት ሆነው ዋጋ የሚከፍሉለት፣ የሱፍ፣ ጣሂር፣ ጋሻው፣ የሚደክሙለት፣ ከክብራቸው በላይ ክብሩን ያስቀደሙለት አንተ እንድትሰድበው አይደለም። ሌላ ክብሩን እንዳይከናው የቆሙለትን ሕዝብ አንተ ለእነሱ ያሰብክ መስለህ እንድትሰድበው ሊፈልጉ አይችሉም። አጓጉል ነገር ነህ። ክቡር ገና ክብሩን ጣል አድርጎ ከካድሬ ጋር ሊወዳደር የገባው ሕዝብን “ወደህ ከተደፋህ” እንድትልበት አይደለም። አንተ በእነዚህ ጎበዞችና በሕዝባቸው መካከል ድልድይ አይደለህም። ደላለ አይደለህም። ራሳቸው ወስነው የገቡለት ሕዝብ ነው። አንተ በሕዝብና በእነሱ መካከል የምትለው እነሱን እንደማይወክል ከራሳቸው ትሰማለህ። ሕዝብን “በቀጣይም እንታገልለታለን ይላሉ እንጅ ከዳን አላሉትም። የገጠማቸውን ችግር፣ ሕዝብን የገጠመውን ችግር ያውቁታል።
አንተስ ተስፋ በቆረጥክ። ችግሩ ነገ ደግሞ ትንሽ ነገር ብልጭ ስትል ልታደንቀው ሮጠህ ትመጣለህ። እንዲያውም! ሽንፈት ማለት ሽንፈት ራሱ አንተ ነህ! በዛው ተስፋ እንደቆረጥክ በቀረህ ወዲያ!