>

ትኩረት በሳውዲ ዓረቢያ ግፍ እየተፈጸመባቸው ላሉ ወገኖቻችን!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ትኩረት በሳውዲ ዓረቢያ ግፍ እየተፈጸመባቸው ላሉ ወገኖቻችን!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሰሞኑን ሳውዲዓረቢያ በሀገሪቱ ካሉ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ብቻ ነጥና ዓለም አቀፍ የስደተኛ ሕጎችንና ድንጋጌዎችን በመጣስ በወገኖቻችን ላይ ግድያን ጨምሮ የዝርፊያ፣ የድብደባንና የጅምላ እስርን እየፈጸመች ትገኛለች!!!
በተለያዩ የዓረብ ሀገራት በየበረሃውና በየሰው ቤቱ በበረሃው ሃሩር እየተጠበሱና በጥጋበኛ የዓረብ አሠሪዎች ፍዳና መከራ እየተቀበሉ ስለሚሠሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በያለንበት እንጮህላቸው ዘንድ የምንገደደው እኅቶቻችን ወንድሞቻችን ወይም ወገኖቻችን ስለሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሠርተው በሚልኩት ገንዘብ በዚህ ኑሮ እሳት በሆነበት ዘመን ቤተሰቦቻቸውን ቀጥ አድርገው የያዙ በመሆናቸውና በዚህ ተግባራቸውም በአውሮፓና በአሜሪካ ካለው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በተሻለ መልኩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየደገፉ ያሉ በመሆናቸውም እንጅ!!!
በአውሮፓና በአሜሪካ ያለው ዳያስፖራ ኑሮውን እዚያው አደላድሎ የመሠረተ ስለሆነ የሚያገኘውን ገቢ የሚያጠፋው እዚያው ነው፡፡ እነኝህ በዓረብ ሀገራት ያሉ ወገኖቻችን ግን ሠርተው ወደሀገርራቸው የሚመጡ በመሆናቸው የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር የሚያስገቡ ናቸው፡፡ እውነቱን ለመናገር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ቀጥ አድርገው የያዙት እነኝህ ትኩረት የተነፈጋቸው መከረኛ ወገኖቻችን ናቸው!!!
አገዛዙ ግን እንደምታዩት በዘመኑ ሁሉ ይሄንን ያህል ጥቅም ለሀገርና ለወገን እየሰጡ ያሉ ወገኖቻችንን በያሉበት የዓረብ ሀገራት መብትና ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያደርገው ጠንከር ያለ ጥረት ኖሮ አያውቅም፡፡ ወገኖቻችን እንዲህ እንደሰሞኑ ከሌሎች ሀገራት ስደተኞች ተለይተው ሲጠቁና ግፍ ሲፈጸምባቸው ሁሉ የሚያደርገው ነገር የለም!!!
ሌሎቹ ሀገራት ለዜጎቻቸው ክብር ስላላቸውና ጥቃት ሲፈጸምባቸው ፈጥነው ስለሚንቀሳቀሱ ዜጎቻቸው ተከብረው ነው በዓረብ ሀገራት የሚሠሩት፡፡ የእኛ ወገኖች ግን አገዛዙ እንደ ዜጋ ሳይሆን እንደ የማይፈለጉ ዜጎች ወይም እንደ ቆሻሻ ስለሚመለከታቸው ይሄንን የአገዛዙን አመለካከት የሚያውቁ የዓረብ ሀገራት ደግሞ ወገኖቻችንን እንደ ሰው ሳይሆን እንደቆሻሻ እንዲያዩና እንደፈለጉ ግፍ እንዲፈጽሙባቸው አድርጓቸዋል!!!
ሲመስለኝ ሳውዲዓረቢያ ሰሞኑን በወገኖቻችን ላይ ይሄንን ግፍ እየፈጸመች ያለችው ሕዝቡ ይሄንን አገዛዝ “በሳውዲዓረቢያ ያሉ ወገኖቻችንን ታደግ!” እያለ እንዳያስጨንቀውና ሳውዲዎችም ያሻቸውን ማድረግ እንዲችሉ ይሄንን አሳቻ ሰዓት ለሳውዲዎች በመንገር ሕዝቡ ትኩረቱ በምርጫ ጉዳይ ተወጥሮ በተያዘበት ወቅት ይሄንን ግፍ እየፈጸሙ ያሉ ነው የሚመስለኝ!!!
የዓረብ ሀገራት ስደተኛ ወገኖቻችንን አክብረው መያዝ የሚገደዱት ወይም የሚኖርባቸው  የዓለም አቀፉ የስደተኞች ሕግ ስለሚያስገድዳቸው ወይም ውለታ ስላለባቸው ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከጥንት ጀምረው ሀገራችን አቅም አግኝታ ዓባይን እንዳትገድብ ለማድረግ ከግብጽና ከሱዳን ጎን ተሰልፈው ሀገሪቱን ምስቅልቅል ውስጥ በመክተት ላለንበት ስር የሰደደ ድህነት የዳረጉንና ከድህነታችንም እንዳንወጣ እያደረጉን ያሉት እነሱ በመሆናቸው ከየትኞችም ሀገራት በላይ ከዚህ አሳዛኝ ድህነት ላይ የጣሏት ሀገር ስደተኞችን የመቀበልና የማስተናገድ የሞራል ግዴታ ስላለባቸውም እንጅ!!!
እናም እባካቹህ ለወገኖቻችን በየፊናችን እንጣርላቸው??? በተለይም በአውሮፓና በአሜሪካ ያላቹህ ወገኖቻችን ላላቹህባቸው ሀገራት መንግሥታትና ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም ይሄንን ሕገወጥና አረመኔያዊ ግፍ የማጋለጥና የማሳሰብ ግዴታና ኃላፊነት አለባቹህና እባካቹህ ጩሁ ዝም አትበሉ!!!
መጅሊስ የሚባለው በሀገራችን ያለው የእስልምና የበላይ አካልም ለዚች የእስልምና እራስ ለሆነች ሀገር ማለትም ለሳውዲዓረቢያ መንግሥት እየፈጸመ ያለው ተግባር “በፈጣሪ አምናለሁ!” ከሚል አካል ፈጽሞ የማይጠበቅ ኢሰብአዊ፣ ኢሞራላዊ፣ አረመኔያዊ ተግባር መሆኑንና የነቢያቸውን የመሐመድን ቤተሰቦች ተቀብላ ከሚያሳድዷቸው ጠላቶቻቸው በመታደግ ለእስልምና ታላቅ ውለታ በዋለች ሀገር ዜጎች ላይ እንዲህ ዓይነት ግፍ መፈጸም ከአረመኔነትም በተጨማሪ እጅግ አሳዛኝ ውለታቢስነት መሆኑን በማሳሰብ የሀገሪቱ መንግሥት ከዚህ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነጥሎ እየፈጸመው ካለው የግፍ ሥራው እንዲታቀብ ቢያሳስቡና ቢማጸኑ መልካም ነው፡፡ ይሄንንም የማድረግ የዜግነትና የእምነት ግዴታም አለባቸው!!!
Filed in: Amharic