ለአማራው የቤት ሥራ መስጠት የማይሰለቸው አቢይና ሰሞነኛ ጉዳዮች
አምባቸው ዓለሙ (ከወልዲያ)
ለሕወሓት ማንሰራራትና መቀሌን መያዝ ትክክለኛ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ወደፊት የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ጉዳዮችን ግን በግምት መናገር የሚከብድ አይሆንም፡፡ ከነዚህ ግምቶች ውስጥ ሁለቱ የነቀዘው ስንዴ መዘዝና አማራን ከትግሬ ለማጣላት በውጤቱም የኦሮሙማን ፍልስፍና የሚያራምዱ ወገኖች ካለተቀናቃኝ ታላቁን አባት ሀገር ኦሮምያን ለመመሥረት ከሚጠቀሙበት ሥልት አንደኛው ሊሆን እንደሚችል ብንገምት ስህተታችን ያን ያህል የሚጋነን አይሆንም፡፡ ለማንኛውም እየሆነ ያለው ሁሉ ያስገርማል፡፡
ዱቄት የተባለው ሕወሓት፣ ከማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውጪ እንደሆነ በኩራት ሲነገርለት የነበረው ወያኔ፣ “መሪዎቹም ሆኑ ሠራዊቱ እንደጉም ተበትነዋል” ሲባልለት የነበረው ትህነግ … አፈር ልሶ ነፍስ በመዝራት ድንገት መቀሌን ተቆጣጠረ ሲባል የማይታመንና የዚህን ሤራ አንድምታ ለምንረዳ ወገኖች እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ ይህ እውነት የማያስደነግጠው ቢኖር አንድ ሰው ብቻ ነው – እሱም አቢይ አህመድ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚሠራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ዋና ቁማርተኛና የተዋጣለት ፖለቲካዊ ቼዝ ተጫዋች ነው፡፡ ይህ የጭቃ እሾህ ሰውዬ ይጠቅመኛል ብሎ ካመነ ገና አዲስ አበባንም በአልቃኢዳ ሊያሲዝ ይችላል፡፡ ለዓላማው ስኬት ይረዳኛል ካለ ናዝሬትንና ነቀምትንም ለአልሻባብ ሊያስረክብ ይችላል፡፡
ወያኔ መቀሌን ቀርቶ ሣምሪንን ይቆጣጠራል ተብሎ የሚገመት ኃይል አልበረም እንደውነቱ፡፡ እውነቱን ለመናገር ትላልቅ ባለሥልጣኖቹና መሪዎቹ ወይ ሞተዋል ወይ ታስረዋል ወይ ጠፍተዋል፡፡ ይህ ድንገቴ ሊከሰት የቻለው አቢይ አንዳች ነገር ለማድረግ በማቀዱ ሊሆን እንደሚችል በበኩሌ አምናለሁ፡፡
የነቀዘው ስንዴም አንዳች አስተዋፅዖ ሊኖረው እንደሚችል መጠርጠር አይከፋም፡፡ አሜሪካን ጋር የተናጀሰ መጨረሻው አያምርም፡፡ ሁጎ ሻቬዝን ማስታወስ ነው፤ ዩ ኤስ ኤስ አርን (ሶቭየት ኅብረትን) ማሰብ ነው፤ ኪዩባንና ሦርያን፣ አፍጋኒስታንንና ሶማሊያን፣ ኢራቅንና ሌሎች ሀገራትንና ግለሰቦችን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ አሜሪካ መርዝ ናት፤ ከመረዘች ደግሞ ሳትገድል አትለቅም፡፡ ሲአይኤና ሲአይዲ እጅግ ሲበዛ ተንኮለኞች ናቸው – እየሣቁ ገደል የሚከቱ፡፡ እነሱ ጥርስ የነከሱበት መቅኖ የለውም፡፡ እንጂ እውነትም ወያኔ በኃይል ብልጫ መቀሌን ተቆጣጥራ ከሆነ (እኔ ግን አይመስለኝም) ምክንያቱ ሊሆን የሚችለው የአሜሪካ ሁለንተናዊ ድጋፍ ነው፡፡ መጣላት ያለብህን ኃይል ማወቅ ጥበበኛነት ነው፡፡ መጣላት ከሌለብህ ኃይል ጋር በዘዴ ነው ግንኙነትህን መምራት ያለብህ፡፡ ጀብደኝነት የሚሠራው ከምትበልጠው እንጂ ከሚበልጥህ ጋር አይደለም፡፡ አንደኛው ምክንያት ይህ ነቀዘ ስንዴ ከሆነ ከሚል ነው እንዲህ የምለው፡፡
እኔ እንደሚመስለኝ ግን ወያኔን ከሞት ያስነሳት የአቢይ ሤራ ነው፡፡ ሲያስበው አማራ እስካለ ድረስ ኦሮሙማው ሊሳካለት አይችልም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁለት ነገዶች በቅድሚያ አጫርሶ ትግራይና አማራ ባዶ ሲቀሩለት የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ተረድቷል፤ መካሪዎችም አሉት፡፡ በመሆኑም ወያኔ ትግራይን ሲይዝ ከአማራ ዘርፏቸው የነበሩትንና አሁን ወደአማራ የተመለሱትን መሬቶች ዳግም ለመንጠቅ በቅድሚያ በእልህ መንቀሳቀሱ ሳይታለም የተፈታ ነውና በዚህ አቢይ የመጀመሪያ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይገነዘባል፡፡ ያኔ በዚያን እንቅስቃሴ ፌዴራል ተብዬው የኦነግ/ኦህዲድ መንግሥት ለወያኔ ከወታደር ጀምሮ ሁሉን ስንቅና ትጥቅ እንደየሁኔታው በግልጽ ወይ በድብቅ ያቀርባል፡፡ በውጤቱም አማራን እንዳያንሰራራ አድርጎ ይመታዋል – ያልተወሳሰበ ቀላል ሒሣባዊ ቀመር ነው፡፡ አማራ ከተመታ በኋላ በጦርነት የተዳከመውን ትግሬን ሽመልስ አሰልጥኖ ባስቀመጠው የኦሮሙማ ልዩ ኃይል በቀላሉ በማንበርከክ ኦሮምያን ይመሠርታል፤ ሌሎች ነገዶችንም በገዳ ሥርዓት የሞጋሳ ባህላቸው በቀላሉ ባርያቸው ያደርጓቸዋል፡፡ የአቢይ ዓላማና ዕቅድ ከዚህ እምብዝም የሚያልፍ ሊሆን አይችልም፡፡ ግን የፈጣሪ ዕቅድና ፍላጎት ደግሞ አለ፡፡ የመከራው ዶፍ ከየት አቅጣጫ እንደሚሰነዘር አናውቅም እንጂ መከራው መምጣቱን ዱሮውንም እናውቃለንና ይህ ዓይነቱ ሸብረብ ብዙም እንግዳ አይሆንብንም፡፡ አቅጣጫው ግን በርግጥም ያስደነግጣል፡፡
አሁን አማራና ትግሬ ይጠንቀቁ፡፡ የተሸረበባቸው ተንኮልና ሤራ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ግብጽና አሜሪካ ኢትዮጵያ ካልጠፋች እንቅልፍ የሚወስዳቸው አይደሉም፡፡ መጪው ዘመን አደጋ የበዛበት መሆኑን ስንናገር ባጅተናል፡፡ ሰሚ ኖረም አልኖረም የወደፊቱ ጊዜ ከእስካሁኑ እጅግ የከፋ ዕልቂትና ውድመት የሚከሰትበት እንደሆነ ብዙ ጮኸናል፡፡ እንዴትና በምን ሁኔታ የሚለውን ልክ እንደዚህ በተግባር እያየን ካላወቅነው በስተቀር በእስካሁኑ ሁኔታ ከግምትም ውጪ ነው፡፡ ወያኔ በዚህ መልክ ይመጣል ብሎ ማን ሊያስብ ይችላል? ግን አቢይ እስካለ ድረስ የማናየውና የማንሰማው ጉድ የለምና በየቀኑ ጆሯችንን ቀስረን የሰውዬውን ትንግርተኛ ታሪክ ለመስማትና እንደየሁኔታውም ዕልቂታችንን ለማስተናገድ መዘጋጀት ነው፡፡
ትናንት ዱቄት የተባለና ምንም ነገር ያልነበረው ተራ ሽፍታ ዋና ከተማ እንዲቆጣጠር መፍቀድ ነገ ምን ሊከሰት እንደሚችል በግልጽ ይጠቁማልና በተለይ አማራው በተጠንቀቅ ይቁም፡፡ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን አቢይ የሚያዛቸው – ጃዝ የሚላቸው – የሕወሓት ተዋጊዎች በቅርቡ ጎንደርንና ደሴን እንዲሁም ባሕር ዳርን ይቆጣጠራሉ፡፡ የታሰሩ ቱባ የወያኔ ባለሥልጣናትም በቅርቡ ይፈታሉ፡፡ አማራን ለማጥፋት ሲባል ወያኔና ኦህዲድ ዕርቅ ይፈጽማሉ፤ ይቅር ተባብለውም በአዲስ ፍቅር ተጣምረው አማራን ማሳደዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በምርጫው “አንጸባራቂ ድል” ያገኘው ብል(ጽ)ግና ፓርቲም በአቦይ ስብሃት የክብር እንግድነት ሥርዓተ ሲመቱን በቤተ መንግሥት ያከናውናል፡፡ ያኔም አቢይ አህመድ ሰባተኛ ንጉሥነቱን በይፋ ያውጅና በኢትዮጵያ ከርሰ መቃብር ላይ ማንም የማያውቃት የሥውሯ ኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ይሆናል፡፡ የሻዕቢያ የመቶ ዓመት የቤት ሥራም በስኬታማነት ግማሽ መንገድ መጓዙ ይገለጽና የቀጣዩ ግማሽ ምዕተ ዓመት ጉዞ መጀመር በብርሃኑ ነጋ የመድረክ መሪነት ይበሠራል፡፡ … ማታ በሰማሁት ሊታመን የማይችል የመቀሌ በወያኔ ቁጥጥር ሥር መግባት ዜና ጥሩ ሌሊት ስላላሳለፍኩ እያቃዠኝ መሰለኝ – ስለዚህ “ማሟረቴን”ም እዚሁ ላቁም… በተረፈ ተስፋችን “እንኳን ከፎከረ ከወረወረ የሚያድነው” አንድዬ ነውና ምንጊዜም እንደምለው እሱን ጠበቅ እናድርግ፡፡ የምንጠብቀው ጨለማ ውስጥ ነንና ሌሊቱ እንዲነጋ አጥብቀን እንጸልይ፡፡ የእስካሁኑን የዘመናት ስቃያችንን ቆጥሮልን አመክሮ ያድርግልን፡፡ መንጋቱ ግን አይቀርም፡፡ ይህን አንጠራጠር፡፡ ቀኑም ቀርቧል፡፡ እኛ ብቻ ወደፈጣሪ እንመለስ እንጂ ሊረዳን ከበራችን ቆሟል፡፡