>

አንዳንድ ሰውን ሳስብ..  (አሰፋ ሀይሉ)

አንዳንድ ሰውን ሳስብ.. 

አሰፋ ሀይሉ

አብይ አህመድን እወደዋለሁ! ለትግራይ ወያኔዎች እንዳሰኛቸው የመዘዋወሪያና ራሳቸውን የማደራጃ ነጻ ቀጣና ሰጥቷቸው፣ ሀገር ምድሩን፣ ህዝቡን ድንበሩን ሁሉ ጥሎላቸው ወጥቷል! አማራውን ደሞ ጦሩን ያርመሰምስበታል፣ እንደ ብአዴን ያሉ ወዶገቦችን ጉሮሮው ላይ ጠምዶበታል፣ አማራው ራሱን የሚያደራጅበት አንዲት ሰባራ መላወሻ ሜዳ አሳጥቶታል!
ኦሮሚያ የሚባለውን ምድር እታጠቃለሁ ላለ ነጻዋን ኦሮሚያ ለሚናፍቅ ሠራዊት ሁሉ አስረክቦታል! ሀገር ምድሩን ለሥርዓት-አልበኞች መፈንጫ አድርጎ በዛሬው ቀን 200 አማራ ተገደለ፣ 38 ስምንት እንደርታ ተገደለ፣ በዚህ ወጣ በዚህ ገባ እያለ ከቤተመንግሥት ቁጭ ብሎ የሚዘግበውን አብይ አህመድን እንዴት አልወደው? እወደዋለሁ እንጂ! እንዲህ አድርጎም መሪ የለ!
አንዳንድ ሰውን ሳስብ.. ምናለ በጀመረው ሙያ ቢቀጥል? የሚያሰኘኝ ብዙ ሰው አለ፡፡ ሂትለር ለምሳሌ እንደጀመረው ሰዓሊ ቢሆን ኖሮ፣ ጎብልስ እንደጀመረው የአርት ሰው ሆኖ ቢቀር ኖሮ፣ ኢዲአሚን ቦክሰኛ ሆኖ ቢቀር ኖሮ፣ … አብዮት አህመድ እንደጀመረው ማራገቢያ (መሽረፈት) ሻጭ ሆኖ ቢቀር ኖሮ፣… ምን ነበረበት?
አንዳንድ ሰዎች በጀመሩት ሙያ ቢቀጥሉ… በህዝባቸው አናት ላይ ተፈናጥጠው ሀገርምድሩን የደም ሸማ ሳያደርጉት እዚያው በተነሱበት ተቀልጥመው ቢቀሩ ኖሮ… ምን ነበረበት? ዓለም ምን ያህል ሠላም ታገኝ ነበር? ምን ዋጋ አለው? እንዳሳመረ አይገድል!? ወይ ነዶ!
ድንገት የዚያን ሰሞን መሽረፈቴ ትዝ አለኝ!
መሽረፈት ያለ የሌለ ቱሪናፋውን ነፍቶ ስንቱን ውድ የሰው ልጅ ነፍስ፣ በሺኅዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠርን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነፍስ አጠፋ? ስንቱን የዜጎችና የሀገር ንብረት አወደመ? የስንቱን ሠላማዊ ኑሮ አደፈረሰ? የስንቱን ቤት አጎደለ? ሀገር ምድሩን በቀይ የወጣቶች የደም ምንጣፍ አለበሰ? ለመሽረፈት የቀን ቅዠት ሲባል ስንት እጅ-ለእጅ ተያይዞ ሀገርን በተባበረ ክንድ የሚገነባ ዜጋ ተጋደለ?
ስንት ተመስግነውም ተወቅሰውም በክብር የእርጅና እድሜ መኖር የሚችሉ ለዚህች ሀገር ለአንዲትም ቀን የሰሩ ሰዎች ለውሻ ብቻ እንጂ ለሰው ልጅ ፍጡር በማይገባ አሟሟት ተረሸኑ? ለመሆኑ መሽረፈትና ስማቸውንና ስልጣናቸውን እየቀያየሩ በምቾት የሚንደላቀቁ የኢህአዴግ ቡችሎች ሁሉ ተነጥለው ከተገደሉትና ከተሳደዱት የኢህአዴግ ፈጣሪዎች በምንድነው የሚለዩት? በጎሰኛ አይዲዎሎጂያቸው? በፖለቲካቸው? በየትኛው ጽድቃቸው ነው የሚለዩት?
በበስንት ቢሊየን የሀገር ሀብት ወደመ? ለመሆኑ መሽረፈት የፈጸመውን የሀገር ክህደት ወንጀል የፈጸመ ተስተካካይ ከሃዲ ሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ይገኛል? በኤርትራ ጦር የገዛ ሀገሩን ያስወረረ፣ የትግራይን ህዝብ በኤርትራና በሶማሊያ ያስወረረ፣ የአማራን ህዝብ በሱዳኖች ያስወረረ.. ወራዳና ሀገር የከዳ ባንዳ.. እንዴት እንዲህ በሰው ነፍስ ሲቀልድ፣ በዜጋ ነፍስ ሲያላግጥ.. እንዴት ተው የሚለው፣ የሚያስታግሰው፣ የሚገባውን ፍትህ የሚሰጠው አካል ይጠፋል?
መሽረፈት ቡፋውን ሲነፋ፣ ጉራውን ሲቸበችብ ከርሞ.. የለጋ ታዳጊ ዜጎችን ደም አፍስሶ፣ በትግራይ ምድር ኢትዮጵያዊ ወገንን ከገዛ ወገኑ ጋር በጥይትና በሳንጃ አቆሳስሎ… የገዛ ሀገሩን ዜጎች በአውሮፕላን ቦንብና በሄሊኮፕተሮች፣ በሚሳይልና በድሮን እየጨፈጨፈ… ስንቱን በመቶሺኅዎች የሚቆጠር.. ኢትዮጵያዊት ደሃ እናት ‹‹አህ›› ብላ አምጣ የወለደችውን የየቤቱን ተስፋ ከአፈር ቀላቀለው?
አሁንም ወሬውን እያወራ! አሁንም ቱሪናፋውን እየነፋ! አሁንም መሽረፈቱን እያራገበ.. እንዴት ሀገር በቁም ቅዠተኛ ትመራለች? ለዜጋው የሚቆረቆር ዜጋ የለም ወይ? ለሀገሩ ለባንዲራው ለህዝቡ ለዳርድንበሩ ለክብሩ የቆመ፣ የወገኑ መሐላ የባንዲራው ቃልኪዳን ያለበት ሀገርጠባቂ፣ ህግ አስከባሪ ወታደር የለም ወይ ባገሩ?
የመሽረፈትን በደም የጨቀየ ህልም ቀድሜ ያለምንም ማወላወል በማውገዜና ሁሉም እንዲያውቀው በመወትወቴ የሚሳቀቁ ሰዎችን ሳይ ሁሌም ይገርመኝ ነበር! ይህን ውጤት አልባ ሀገራዊ ደም መፋሰስና እርድ እንዳይከሰት ነበር እኮ ስጮህ የነበረው? ዛሬ ላይ ቆሜ በህዝባችን በሀገራችን በታሪካችን በስማችን ላይ መሽረፈት ያደረሰውን ጠባሳና ቁስል፣ ስብራትና ውድመት፣ ሞትና ሰቆቃ ሳስብ.. ይህ ሁሉ እንዳይሆን ማራገቢያውን ከፍ አድርጌ ለእውነትና ለሠላም የቆምኩበት ህሊና፣ ያነገብኩት ፊት-ለፊትነት ያኮራኛል!
አንድ የሚፀፅተኝ ነገር ቢኖር… በመሽረፈት የጥፋት ህልምና ቅዠት የተነሳ የጠፋው የማይተካ የንጹህ ኢትዮጵያውያን ነፍስ ብቻ ነው! ፈጣሪ በማራገቢያው ቅዠት እርስበርሳቸው ተጨፋጭፈው፣ በውጪ ሀይል ተጨፍጭፈው ላለቁ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች – ለነፍሳቸው የበዛ ሠላሙን ይስጣት!
መሽረፈት የገዛ ሀገሩን አወደመ፣ የገዛ ህዝቡን አጨፋጨፈ፣ ሀገር ምድሩን በደም አቀለመ..! ራሳችንን አጥብቀን እንጠይቅ፣ ከዚህ ሁሉ የደም አበላ የተገኘው አንዳች ትርፍ ምንድነው? ለመሆኑ ኢትዮጵያ ይገባኛል የምትላቸውን ድንበሮች ለኤርትራ ያለአንዳች የህዝብ እውቅናና ዓለማቀፍ ስምምነት እንካችሁ ብሎ አንስቶ ማስረከብ ጀብድ ነው ወይ? የሀገር ክህደት የሚባለው አንድ ሰው ከዚህ የበለጠ ምን ዓይነት ሸፍጥ በሀገር ላይ ሲፈጽም ነው? ምን የከፋ ነገር ሲያደርግ ነው?
ለመሆኑ ምንድነው በትክክል ከኤርትራ ጋር እንደ ሀገገር የገባንበት ውል? የትግራይ ምድር የኢትዮጵያ ግዛት አይደለም ወይ? የሰሜን ድንበራችንን መጠበቅ፣ ሀገርን ማስተዳደር ከአንድ መንግሥትን እመራለሁ ከሚል አካል የሚጠበቅ የመጀመሪያውና መሠረታዊው ተግባር አይደለም ወይ? እሺ የወያኔ ናዚ ሽማግሌዎችን ለመዋጋት፣ እና ሥርዓትና ህግ ለማስከበር ኤርትራ መሽረፈትን አገዘች ይባል… አሁንስ ምን እየተከናወነ ነው?
ለመሆኑ አብይ አህመድ በአሁኑ ጊዜ ውግንናው ከማን ጋር ነው? በትግራይ ግዛት ላሉት ህዝቦችና ይመራናል ብለው ለመረጡት ኃይል? ወይስ ለኤርትራ ህዝብና ሠራዊት? ለትግራይ ግዛቱና እንዳሻህ አስተዳድር፣ ከፈለግክ ግደል፣ ከፈለግክ አኑር ብሎ ሀገሩን ለለቀቀለት ለህወኀት ያለው ኦፊሴላዊ አቋም ምንድነው? አሁንም መሽረፈት ሽብርተኛ ድርጅት ነው ብሎ ነው የሚናገረው ህወኀትን? ለሽብርተኛ ድርጅት ነው 6,000,000 (ስድስት ሚሊየን) የትግራይ ነዋሪዎችን አሳልፎ የሰጠውና እግሬ አውጭኝን የመረጠው?
መሽረፈት ከቅዠቱና ከህልሙ የሚነቃው መቼ ነው? ለመሆኑ ህወኀትን ‹‹ሽብርተኛ›› ብሎ የፈረጀው ፓርላማ ተብዬው የተለመደ የሎሌዎች ስብስብ፣ አሁን አብይ አህመድ የሀገሪቱን ሰሜናዊ ግዛት ከነሚሊየን ህዝቦቹ ለዚያ ሽብርተኛ ብሎ ለፈረጀው ድርጅት አስረክቦ ሲወጣ ምንድነው የሚለው? ዝም-ጭጭ ነው የሚለው?
የሀገሪቱ ከፍተኛና የበታች ወታደራዊ መኮንኖች በመሽረፈት የተፈጸመውን ሀገር ጥሎ የመሸሽ ትዕዛዝ፣ ከቀደመው ውረረው- ህግ አስከብር- ግደል-ደብድብ-አውድም ትዕዛዝ ጋር አነጻጽረው ነገሩን እንዴት ነው የሚመለከቱት? መሽረፈት በዚህ መልክ ነገስ ለኦነግ ሸኔ የትኛውን የኢትዮጵያ ግዛት ነው ከነህዝቡ መርቆ የሚሰጠው? ለመሆኑ ክልሎች ተብዬዎቹ ሁሉ.. የቱንም ያህል በወያኔ-ወለድ ጎሳና ነገድ ፖለቲካ ተደራጅተው ቢግተለተሉ.. እንዴት ሰብሰብ ብለው ይህ ልክ አይደለም፣ ይህ በዚህ መልኩ መመራት አልነበረበትም፣ ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? የሚል ቃል የሚወጣው ዜጋ በሥራቸው አልፈጠረባቸውም?
በበኩሌ ገና ከጅምሩ ከፍ ወዳለ ጥፋትና የእርስ በርስ መጠፋፋት የሚያደርሰው የመሽረፈት ወደየትም የማያደርስ ጉዞ ወለል ብሎ ታይቶኛል፡፡ ያንንም በቻልኩት ሁሉ ተቃውሜያለሁ፡፡ ሆኖም በህይወቴ እንደ መሽረፈት ያለ ወደየትምና ወደምንም ለማያደርስ ቅዠትና እብደት ሲባል እንዲህ የዜጋን ደም ለማፋሰስ የቆመ (የየትኛው ጠላት ሀገር ቅጥረኛ እንደሆነ ልለየው ያልቻልኩት) ደም-የጠማው ኢትዮጵያዊ አጋጥሞኝም፣ አስቤም፣ ይኖራልና እውን መሪ ሆኖ ይቆማል፣ ይቀጥላል ብዬ አልሜም አላውቅም! ፈጣሪ ምስክሬ ነው!
በፍጹም እንዲህ ያለ ፀረ-ሀገር እና ፀረ-ህዝብ ሰው ህዝቡን በምላሱ እየደለለ ይሄን ያህል በሥልጣን ላይ ይቆያል፣ ይህን ያህል ደም ያፋስሳል፣ ይህን በሚያህል ደረጃ ሀገሪቱን ይዞ ወደ እንጦረጦስ ይንደረደራል፣ ህዝቡም ዝም ብሎ ያየዋል፣ እያጨበጨበ መከተሉን ይቀጥላል የሚል እምነት አልነበረኝም! የሆነ መስመር ላይ ሀገሩን በደም ማቅለምና ሀገሩን ለውጪ መንግሥታት መሸጥ የጀመረውን መሽረፈትን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀይ ካርድ እንደሚሰጠው ነበር የማስበው!
ግን አለመታደል ሆኖ፣ ነገራችን ሂትለርን የተከተለውን ህዝብ ዓይነት ነገር ሆኖ.. የሁሉንም አዕምሮና አቅል በማይታወቅ የምላስ ማደንዘዣ ወግቶታል፡፡ ሂትለር እኮ ቢያንስ የሆነ ለሀገሩ፣ ለምድሩ፣ ይጠቅማል ያለው ታላቅ ግብ እኮ ነበረው.. የቱንም ያህል በሌሎች ህዝቦች ላይ የከፋ አውሬ ቢሆን! ይሄኛው እኮ ህዝቡን አቅሉን አስቶ ታዛዥ ተከታይ በማድረጉ ነው እንጂ ከሂትለር ጋር የሚነጻጸረው፣ የዚያኛው ቅዠትና የዚህኛው ቅዠት አይገናኝም፡፡
የዚህኛው ጠባቡ ሂትለር ቅዠት ኢትዮጵያን እያነበነቡ፣ በኢትዮጵያ ስም እየማሉ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን መፍጀት፣ ማጠፋፋት፣ ማባላት፣ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ክብርና ማዕረግ ሁሉ መግፈፍና ኢትዮጵያን መበታተን ነው፡፡ እንደ አህያ ዛሬን በልቶ፣ ጮሆ፣ አናፍቶ መሞት ነው፡፡ እና የቱንም ያህል ሚሊዮኖችን ማግዶ ጠባብ የጎሳ ግቡንና ከውጭ የተሰጠውን የማይታወቅ ሰይጣናዊ ሀገርን የማባላት ተልዕኮ ማሳካት ነው፡፡
ሳስበው ቅዱስ መጽሐፉ የሚናገሩትን ሳይሆን የሚያደርጉትን ተመልከቱ፣ በፍሬዎቻቸው ታውቋቸዋላችሁ – የሚለው እንደመሽረፈት አይነቶቹን ይመስለኛል፡፡ ዛሬ የመሽረፈት ጉዞ ምን አተረፈልን ብሎ መጠየቅ ከያንዳንዱ ጤነኛ ሰው የሚጠበቅ ትንሹና መሠረታዊው የዜግነት ግዴታ ነው፡፡
ዛሬ መሽረፈት ሀገሪቱን ከጎረቤቿ ሁሉ ጋር አያናከሳት ነው፡፡ ዛሬ መሽረፈት የዓለም ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ እንዲሰለፍና ኢትዮጵያ የዘር አጥፊ ምስል እንዲሰጣት አድርጓል፡፡ ዛሬ መሽረፈት የኢትዮጵያን ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ በዓለም የሚዘበትና የዶሮ ነፍስ እንዳለው በሺህዎች ያለምንም ዓላማ የሚታረድ የመስዋዕት በግ አድርጎታል፡፡ መሽረፈት ሀገራዊ የህዝብ ተቋሞቻችንን ለውጪ ባለሀብቶች እየቸበቸበው ነው፡፡
መሽረፈት የኢትዮጵያን ብር እንደ ጣቃ ጨርቅ በብዛት እያመረተ የገንዘባችንን ዋጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ በውጭ ምንዛሬ ዋጋ ያሳጠበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ መሽረፈት ሥርዓት የሌለበትንና በፕሮጀክት ስም ጠባብ ጎሰኞች ያሻቸውን ሀገራዊ ዝርፊያ እንዲያደርጉ፣ ባሻቸው የህዝብ በጀትና ፕሮጀክት ላይ በቢሊዮኖች እንዲቀልዱ ያደረገበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ዛሬ ለተራቡና በየጎዳናው ለወደቁ ህጻናት ከሚወጣው በጀት በላይ፣ የመሽረፈት ቅዠት ለሆኑት መናፈሻዎች ግንባታ የሚወጣው ወጪ፣ ለመሽረፈት ጠባቂ ሪፐብሊካን ጋርዶች የሚበጀተው የሀገር ሀብት ይበልጣል!
ዛሬ መሽረፈት ከወያኔም በባሰ ፍጥነትና ይሉኝታ ቢስነት የሀይማኖት ክፍፍልን ለሥልጣኑ መግዢያ ለመጠቀም በመባተት የሀገራችንን ዜጎች በሀይማኖት እያቧደነ እያጣላና እያባላ፣ ለነገ ጭፍጭፍ እያዘጋጀ ነው፡፡ ዛሬ መሽረፈት ምስጢራዊ ወታደራዊና የደህንነት ተቋሞቻችንን ሳይቀር የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ለሆኑ የውጭ ሀገራት እንዳሻቸው ሰርገው እንዲገቡና እንዲቆጣጠሩት እያደረገ ነው፡፡ ከጠንቋዩ ታምራት ገለታ ሚሊዮን ጊዜ በሚልቅ የሆነ ማደንዘዣ ህዝቡን የቅዠቱን እጣቢ እያለቃለቀ በጥፋት መንገዱ አስከትሎ እየሄደ ነው! እስካሁንም ተው የሚለው፣ የሚያስቆመው፣ አደብ የሚያስገዛው አካል ከሰፊው የኢትዮጵያ ምድር አልተፈጠረም!
ለዚህ ሁሉ ሰቆቃ፣ ሀገራዊ ውርደት፣ እና በህግ ማስከበር ስም ሀገሪቱን ህግ አልባ፣ ሰው አልባ፣ ስርዓት አልባ ምድር አድርጎ ያስቀረው መሽረፈት – ከቅዠቱ ተቀስቅሶ ተይዞ ለፍርድ እንዲቀርብ፣ እና በፍትህ እንዲዳኝ ከልቤ እመኛለሁ! የጠፋውን ሁሉ መመለስ ባይቻል፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ ከአሁን በኋላ በማንኛውም ሰዓት ወደ ሌላ ወደባሰ ደም-መፋሰስና እልቂት ውስጥ ሳይከተን.. መሽረፈት ማንቁርቱን ተይዞ ለፍርድ እንደሚቀርብ አንዳችም ጥርጥር የለኝም!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከዚህ እጆቹ በንጹሃን የዜጎች ደምና በሴራ፣ በሀገር ክህደት፣ በጭካኔና በሰው ልጆች ጭፍጨፋ ከጨቀየ ቅዠታም ሰው ጨርሶ ይማራት! ጨርሶ ይገላግላት! ጨርሶ ይፈውሳት ፈጣሪ አምላክ! ከዚህ በቀር የምለው – እና ከሚገባኝ እጅግ ብዙ ርቀት ሄጄ ልለው የምችለው – ሌላ ምንም ቃል የለኝም! የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር – ይህን ሁሉ በገሃድ ለሁሉም ተገልጦ የሚታይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ ያን ጊዜም ዓይናቸውን ጨፍነው አናይም የሚሉ እንደሚኖሩም አልጠራጠርም፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያችንን ከሚመጣብን ክፋት ሁሉ ያሻግረን፡፡ ከክፉ ሁሉ ይሰውረን፡፡ የድሆቻችንን፣ የእናቶቻችንን ተስፋ ያጡ ወጣቶቻችንን መቃተት ይመልከትና ያውጣን ፈጣሪ አምላክ ከገባንበት የሸፍጥና የመከራ ጉዞ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
_______________________________
ፎቶው፦ ከ8 ወራት በፊት የተነሳሁት የመሽረፈት መታሰቢያ ፎቶ ነው፡፡ ይህ ምስል ዕድሜዬን ሙሉ በሀገራችን የወደቀብንን የሰው ልጅ ሞትና መከራ የማስታውስበት፣ የጊዜዬ የዘመኔ ማስታወሻ ሆኖ አብሮኝ ይኖራል፡፡
Filed in: Amharic