“የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሁሉንም ጋዜጠኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እንጠይቃለን !!!
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በአፋጣኝ እንዲፈቱ የብዙኃን መገናኛ ባለሙያዎች የሚደርስባቸው ማዋከብ መቆሙን እንዲያረጋግጡ ሲፒጄ ተብሎ የሚጠራው የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ድርጅት ጠየቀ። ድርጅቱ ትናንት አርብ ባወጣው መግለጫ የሁለት ገለልተኛ ብዙኃን መገናኛዎች 15 ተቀጣሪዎች መታሰራቸውን አስታውቋል።ፖሊስ ባለፈው ረቡዕ አውሎ ሚዲያ የተባለ ተቋም የአዲስ አበባ ቢሮ ላይ ካደረገው ፍተሻ በኋላ ቢያንስ አስራ ሁለት ተቀጣሪዎች ማሰሩን የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ድርጅቱ ከተቋሙ ጠበቃ እና የታሳሪ ቤተሰቦች እንዳረጋገጠ ገልጿል። ከታሳሪዎቹ መካከል ጋዜጠኞች፣ የካሜራ ባለሙያዎች፣ የቪዲዮ ኤዲተሮች፣ የሒሳብ እና የጽዳት ሰራተኞች ይገኙበታል። ድርጅቱ ከጎበኟቸው ቤተሰቦቻቸው ባገኘው መረጃ መሠረት አስራ ሁለቱ የአውሎ ሚዲያ ተቀጣሪዎች በፌድራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል የታሰሩ ሲሆን ሪፖርቱ እስከ ወጣበት እስከ ትናንት አርብ ድረስ ፍርድ ቤት አልቀረቡም። በቁጥጥር ሥር የዋሉበት ምክንያትም አልተገለጸም። ከአውሎ ሚዲያ በተጨማሪ ኢትዮ-ፎረም የተባለው በዩቲዩብ አማካኝነት ዘገባዎችን የሚያቀርብ ተቋም ባልደረቦች የሆኑት አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ የተባሉ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ኢትዮ-ፎረም በፌስቡክ ገጹ በተናጠል ባሰራጫቸው አጫጭር መረጃዎች ሁለቱ ጋዜጠኞች “የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ እና ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ሃይሎች” መወሰዳቸውን ገልጿል። ታደለ ገብረመድሕን የተባሉ ጠበቃ ሁለቱ ጋዜጠኞች በፌድራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል ታስረው እንደሚገኙ ለሲፒጄ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ “ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በሙያቸው ሳይሆን በምክር ቤት ከታገደ ሽብርተኛ ቡድን ጋር በነበራቸው ግንኙነት ነው” በማለት አዲስ ስታንዳርድ ለተባለው የድረ-ገጽ መፅሔት ተናግረዋል።
የሲፒጄ የአፍሪካ ቢሮ አስተባባሪ አንጄላ ኩይንታል ግን “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የኢትዮ-ፎረም እና አውሎ ሚዲያ ሁሉንም ተቀጣሪዎች በአፋጣኝ” እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።