ፍርድ ቤት እና ዳኞች ዋጋ ያጡበት ኦሮሚያ ክልል…!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
መንግስት ለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አልገዛ ሲል ፍትህ ይዛባል፣ የዜጎችም ሰብአዊ መብት አደጋ ላይ ይወድቃል…!
ዳኞች በነጻ እና በዋስትና የሚለቋቸውን እስረኞች ፖሊስ አለቅ ብሎ የሚሰውርበት እና ፍትህ የጠየቁ የታሳሪ ቤተሰቦች የሚንገላቱበት፣ የሚታሰሩበት ሂደት መቆም አለበት።
ፍትህ፤ ፍርድ ቤት ነጻ ላወጣቸው ለደሳለኝ ዱፌራ እና አብረውት ለታሰሩ 36 ሰዎች፤ እንዲሁም ልጃቸው ፍርድ ቤቱ ባዘዘው መሰረት እንዲፈታ በመጠየቃቸው የተነሳ ለታሰሩት የደሳለኝ አባት አቶ ዱፌራ ከበደ!
*********
ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸው እስረኞች ከታሰሩበት ፖሊስ ጣብያ ታፍነው የት እንደተወሰዱ አለመታወቁ ተገለፀ።
ማለዳ
በቡራዩ አሸዋ ሜዳ ፖሊስ ጣብያ ኦነግ ሸኔን ትደግፋላቹ በሚል ታስረው የነበሩ ደሳለኝ ዱፌራ ጨምሮ 36 እስረኞች የት እንደደረሱ አይታወቅም።
ደሳለኝ ዱፌራና ገመቹ ከበደ መጋቢት 13 ቀን በኦሮምያ ፖሊስ ከፊንፊኔ ልዩ ቦታው ኮልፌ ወረዳ 11 ከቤታቸው ታፍነው ተወስደዋል። ከዛ ከ 9 ቀናት በኋላ በቡራዩ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተከሳሾቹ ኦነግ ሸኔን ትደግፋላቹ የመሳሪያና ሌሎች እርዳታን ለተቋሙ ትለግሳላቹ በማለት ክስ ቀርቦባቸዋል።
ይሁንና ከሁለት ግዜ ቀጠሮ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተጨባጭ መረጃ አላገኘሁም ሲል በነፃ ለቋቸው ነበር ።
ይሁን እንጂ ፖሊስ ጣብያው ታሳሪዎቹን በነፃ አለቅም በማለቱ ጉዳዩን ለፍትህ ቢሮና ለፍርድ ቤት በማሳወቅ በአምስት ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ዳግም ቢያዝም ፖሊስ ፍቃደኛ አልሆነም ።
ከቀናት ቆይታ በኋላ የፍርድ ቤትን ትዛዝ ከመጣሱ ባሻገር ደሳለኝና ጓደኞቹ ግንቦት 7 ቀን ከፖሊስ ጣብያው ወደማይታወቅ ቦታ ተወስደዋል። ቤተሰብ ደሳለኝና ጓደኞቹ የት እንዳሉ በተደጋጋሚ ፖሊስ ጣብያው ቢጠየቅም ለመናገር ፍቃደኛ አይደለም።
በተያያዘ ዜና የደሳለኝ አባት አቶ ዱፌራ በላቸው ደሳለኝ በተያዘበት ሳምንት በፖሊስ ተይዘው በቡራዩ ማርያም ፖሊስ ጣብያ ይገኛሉ።
የ64 አመት ሽማግሌ የሆኑት አቶ ዱፌራ ፍርድ ቤት የምመሰርተው ክስ የለም በማለት በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ትዛዝ ሰጥቶ የነበር ቢሆንም ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዛዝን በመጣስ በጣብያው እንዲቆዩ አድርጓል።
አቶ ዱፌራ በከባድ ጫና ውስጥ መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ለ ማለዳ ሚድያ ተናግረዋል።
የፍርድ ቤት ትዕዛዞች ይከበሩ!