>

የህዳሴው ግድብና ተመስጋኞቹ .... .!!! (ዘመድኩን በቀለ)

የህዳሴው ግድብና ተመስጋኞቹ …. .!!!

ዘመድኩን በቀለ

*… ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውግ ሙሌት መጀመሯን በይፋ አስታወቀች
 
… የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ምስጋና ለሚገባቸው በሙሉ ምስጋና መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነው። የሚያስመሰግን ሥራ ይሠራ እንጂ ደግሞ ለምስጋና አይከፈልበት። ላብ አያፈስ፣ ጉልበት አይጠይቅ። እናም በዐባይ ጉዳይ እኔ ዘመዴ ከዚህ በመቀጠል ምስጋናዬን በየተራ አቀርባለሁ።
… የሰማይ የምድር ፈጣሪ፣ የፍጥረታት ሁሉ አስገኝ፣ ገና ከመጀመሪያው የፍጥረተ ዓለም ጅማሮ ወቅት ጀምሮ ዔደን ገነትን ያጠጣ ዘንድ የፈጠረልን። “ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከዔድን ይወጣ ነበር።” ዘፍ 2፥10። ስሙ በራሱ በፈጣሪ ያወጣልን። ኢትዮጵያን እንዲከብ አድርጎ የፈጠረልን። “የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል።” ዘፍ 2፥13 ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። በ7ሺ ዘመን ታሪኩ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን አንዳች ቁምነገር ሳይሠራ በዋልፈሰስ ሆኖ እንዲሁ ሲዘፈንለት፣ ሲሞገስ የኖረው ዓባይ ወንዛችን ልጓም ተበጅቶለት በመጨረሻው ዘመን በጌታ መምጫ በዓለም ፍጻሜ ዋዜማም ላይ ቢሆን ኢትዮጵያውያንን እንዲጠቅም ያደረገ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን። አሜን።
… በእነ ቅዱስ ሐርቤ ተወጥኖ፣ በእነ አጼ ዳዊት ተሞክሮ፣ በግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ አቅም ማጣት መጀመር ቢያቅተንም ግርማዊነታቸው ” ፕሮጀክቱን ቀርጸው፣ ፕላኑን ሠርተው፣ ወደፊት የኢትዮጵያ ልጆች ቀን ሲወጣላቸው፣ ገንዘብ ሲያገኙ በራሳቸው ዐቅም ይሠሩታል።” ብለው በክብር  በማስቀመጣቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ክብር ምስጋና ለአፄዎቻችን።
… የግርማዊነታቸውን ፕሮጀክት ከመዝገብ ቤት ከሰንዱቁ አስወጥቶ አቧራውንም አራግፎ፣ ጎጃሜ አያቱ አቶ አስረስ ጠጥተው ያደጉትን የግዮን የዓባይ ወንዝ ልጓም አስገብቶ ሽምጥ መጋለቡን ለገታው ለአቶ ዜናዊ አስረስ ልጅ ለአቶ መለስ ዜናዊም ምስጋና ማቅረብ ይገባል። መለስ ሚልዮን የሚወቀስበት ሥራ ቢኖርበትም ሚልዮኖችን የሚያስደስት ህይወታቸውም እንዲቀይር የሚያደርግ ግዙፍ ፕሮጀክትም ደፍሮ የጀመረም መሪ ነው። ኢትዮጵያ ኒዩክለር እንድትታጠቅም ያደረገ መሪም ነው። የዓባይን ግድብ ወግ አንሥቶ መለስን ያለማመስገን ግመል ሠርቆ አጎንብሶ እንደ መሄድ ያለ ነው። በላዔሰብን በጥርኝ ውኃ ለቁመተ ገነት ያበቃ አምላክ በዚህ ተግባሩ ብቻ ይማረው። ምስጋናም ይገባዋል።
… አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም በዚህ ፕሮጀክት ይመሰገናሉ። ዘመንና ዕድል ተገጣጥመው የዚህች ታላቅ ሃገር መሪ የመሆን ዕድሉን ባገኙ ጊዜም መለስ ዜናዊ ያስጀመረውን ፕሮጀክት ከነብዙ ኮተቱ እንዲቀጥል አድርገዋልና ምስጋና ይገባቸዋል። በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ቸል ያሉበት ሰዓትና ደቂቃም የለም እና ምስጋና ይገባቸዋል። በህዳሴው ግድብ እንደ ድካማቸው መጠን ክቡርነታቸውንም ለማመስገን እወዳለሁ።
… በብዙ ውዝግብ ትውፊቱን አስቀጥሏል። ከላይ አባቶቹ የጀመሩትን ታላቅ ፕሮጀክት ወጣ ገባ እያለም ቢሆን አስኪዶታል። ያለ አማካሪ በራሱ ስሜት እና ፈቃድ ድርድሩን አማሪካ ወስዶ ቅርቃር ውስጥ የከተተን ቢሆንም በእነ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና በእነ ኢንጅነር ስለሺ ልበ ሙሉነት፣ ብልሃት፣ ጥበብ እና ዕውቀት በኢትዮጵያውያንም ጸሎት፣ ጥረትና ተጋድሎ ድርድሩ ከአሜሪካ እጅ ወጥቶ የአፍሪካ ኅብረት እጅ እንዲገባ ተደርጓል። ከነብዙ ችግሩም ቢሆን በእርሱ የአገዛዝ ዘመን የቀደሙ አባቶቻችን ልፋትና ጥረት ወደ ፍጻሜ እንዲደርስ ሆኗልና ለዓሰሎጠሚዶኮ ዐቢይ አሕመድም ክብርም ምስጋና ይገባዋል።
… ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ሰማዕቱ ኢንጂነር ስመኘው በቀለን አለማስታወስ ኃጢአትም፣ በደልም፣ ግፍም፣ ወንጀልም ነው። በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ በግፍ የተገደለው ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የዚህ ፕሮጀክት ዐምድም ነው ቢባል አያንስበትም። ጊዜ ደሙን ጉማ ያወጣለታል። በቀል የእግዚአብሔር ነው። የሆነው ሆኖ ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ አልቀረም። ሞት ለማንም አይቀርም። በትንታም ይሞታል። እናም ኢንጅነር ስመኘው በቀለም ምስጋና ይገባዋል።
… በፕሮጀክቱ ሥራ ላይ አሻራችሁን ያሳረፋችሁ ሁሉ ተመስገኑልኝ። በፕሮጀክቱ ግንባታ ወቅት በግንባታው ሂደት ላይ ወድቀው የሞቱ፣ ውኃው የወሰዳቸው። ብረት፣ ድንጋይ ወድቆባቸው ያረፉ። በንዳድ፣ በበሽታ፣ በሙቀቱ የሞቱ፣ በአጠቃላይ በግንባታ ሥራው ላይ ላባቸውን፣ ደማቸውን፣ ወዛቸውን ያፈሰሱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ክብርና ምስጋና ይድረሳችሁ።
… ገንዘባችሁን ሳትሰስቱ ከአንድ ብር እስከ ሚልዮን ብሮች መዥረጥ አድርጋችሁ ቦንድ በመግዛት መቀነታችሁን፣ ኪስ ቦርሳችሁን ፈትሻችሁ ግንባታውን በራስ አቅም እንዲሠራ ላደረጋችሁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ክብርና ምስጋና በያላችሁበት ይድረሳችሁ።
… በዓባይ ጉዳይ ላይ ግጥም የጻፋችሁ፣ ዜማ የደረሳችሁ፣ ሥዕል የሳላችሁ፣ ድራማ ቲአቴር የሠራችሁ፣ የሞዘቃችሁ፣ የዘመራችሁ፣ የዘፈናችሁ፣ በየዓረቡ ዓለም ሚድያም ላይ ቀርባችሁ ስለዓባይ በዓረብኛም በእንግሊዝኛም የሞገታችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ… ዘገባ የሠራችሁ ጋዜጠኞች፣ ህዝባዊ ንቅናቄ የፈጠራችሁ ሁላችሁ በያላችሁበት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።
… በዓባይ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለግብጽና ለሱዳን ያቃጠራችሁ፣ ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ ያላችሁ፣ ያስባላችሁ። ግብጽ ሆይ ግድቡን አፍርሺው ብላችሁ፣ በአማርኛ፣ በዓረብኛ፣ በትግርኛና፣ በኦሮሚኛ የለፈለፋችሁ ደግሞ የአባት የእናቴ አምላክ አናታችሁን ያፍርሰው። አሜን።
… ባጎደልኩት፣ በሳትኩት ባጎደፍኩት የረሳሁት ካለም እናንተው ሙሉበት። አሜን።
… ደስ እየተሰኛችሁ ሰላም ዋሉልኝ  !!
Filed in: Amharic