>
5:16 pm - Monday May 24, 1075

ከነጋሪት ጉሰማ፤ወደ ጉማ ...!!!  (በእውቀቱ ስዩም)

ከነጋሪት ጉሰማ፤ወደ ጉማ …!!! 

(በእውቀቱ ስዩም)

ኢትዮጵያ ዘመም ስትልና  ስትቃና የኖረች አገር ናት፤  በነዋሪዎቿ  መካከል ያለው አንድነት ባንዱ ዘመን ይታመማል፤ በሌላው ዘመን ይታከማል ::
ዛሬ ጋብ ባለ ጦርነት  እና መልኩ ባልታወቀ መጭ  ዘመን መሀል ቆመናል፤ ተደባበረናል፤ ተጠማምደናል ፤  “ እንገንጠል” “ ይገንጠሉ “ የሚሉ  የቃላት ልውውጦች አየሩን ሞልተውታል ፤
ግን ታሪክን ብናይ ሌላም አማራጭ ያሳየናል ፤ ባንድ ዘመን እንቀሳሰፋለን ፤ በሌላው ዘመን እንተቃቀፋለን፨
ከዘመነ መንግስታቸው ባንዱ ቀን፤  አጤ ዮሀንስ ከነጉስ ተክለሃይማኖት ጋራ  ተጣሉና  ወደ ጎጃም ዘመቱ፤ ለጊዜው  አውራውን ቢያጡት ህዘቡን መቱት፤ ህዘቡም አጥብቆ ረገማቸው ፤ የሳቸው ቤተመንግሰት ጸሃፊ “  ንጉሱ ወደ ሰው በላው አገር ዘመተ  “ እያለ ጣፈ፤  ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ በጎጃም ጌታና በንጉሰነገስቱ መሀል እርቅ ተደረገ፤ አጤ ዪሀንስ ተጠጠቱ፤ ጎጃምን “የሰው በላዎች አገር “ በሚል  የሚፈርጀውን ስድብ ከብራናው ላይ አስፋቁት ፤  ብዙም ሳይቆዩ የበጌምድር ህዝብ ከጠላት ሲከላከሉ   ከብዙ ትግራዮች ጋራ  ተሰው፤
  አመታት በሁዋላ ጣልያን በጀልባ ተሻግሮ ሲወር ጎጃሜ  ለትግራይ ሊመክት ዘመተ፤  አገር ቀጠለ፤
በልጅ ኢያሱ ዘመን ደጃቸ አብርሃ ሸፈቱ፤  የደጃዝማች አባተ ጦር ተላከባቸው ፤
“የዳኘው አሽከር  የጦር ገበሬ
 አይበገርም ላብርሀ ወሬ “
እያሉ እየፎከሩ ዘመቱ  ፤ አብርሃና  ጭፍሮች ኮረም ላይ ተሸንፈው    ተማረከው ወደ ሸገር ተወሰዱ፤   በኢያሱና በመኮንኖቹ ፊት  ለፍርድ ቀረቡ ፤  ካሸናፊዎች ወገን የሆነ አንድ ሰው  እንዲህ አለ፤ “ ይህንን ጥፋት ያጠፉት  ትግሮች ሁሉ መክረው ነው እንጂ አብርሃ ብቻቸውን አልሰሩትምና ትግሬዎች ሁሉ ይቀጡልኝ  “
 ልጀ ኢያሱ  የሰውየው እብሪት አገር የሚያነድ  ክብሪት ሆኖ ታያቸው ፤  ተናጋሪውን አስጥለው ጀርባውን ባርባ ጅራፍ ማሳጅ አስደረጉት ፤  የጅራፉ ድምጥ ሲያባራ  ሸዌና ትግራይ አብሮ  መኖር ቀጠለ፤
 እኛም  እንዲሁ እምንቀጥል ቢመስለኝ ምን ይገርማል፤
በዘንድሮው ጦርነት በየፊናው የተጎዱ  ዜጎች   ይህ ቃሌ እንደማይዋጥላቸው  እገምታለሁ ፤ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ቢሉኝም አልፈርድባቸውም፤ ግን ያልተነካም ይሁን  ያልተከካ ከሆነ ቦታ  ገላጋይ  መምጣት አለበት ፤ ቀደምቶቻችን ከኛ በላይ ተደባድበዋል፤ የሽንፈትን መራራ ጥዋ  በየፈረቃው ቀምሰዋል   ተገነጣጥለው ያልጠበቁን መገንጠል የሚባለው ነገር “ነፋስን መከተል  “ ሆኖ ቢታያቸው  ነው ፤ የጂኦግራፊ ቁራኛ ሆነህ አንዴ ከተፈጠርህ በሁዋላ መገንጠል የሚባለው ነገር  ቅዠት ነው፤
 አሁን ባለንበት ሁኔታ የማእከላዊ መንግሰት ሆነ የክልል መንግስት አውራዎች መጀመርያ ማድረግ ያለባቸው    ዛቻ፤ አሽሙር፤ ጦርነት ጉሰማ መቀንሰ ነው፤ ከዚያ የህዝቡን የጋራ ካፒታል ተጠቅሞ ለርቅና ለሰላም መስራት፤
  ከጂኦግራፊ ባሻገር  የትግራይና በአማራ ህዝብ መሀል ትልቅ  ማህበራዊ  ካፒታል አለ፤  የግእዝ ፊደል፤ ከብሉይና ሀዲስ የተቀዳ ባህል፤
“የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ
 አንገቱን ሰጠላት አጤ ዮሀንስ” ፤ ” አይነትና መሰል የጋራ ሰማእትነት ታሪኮች ፤ ወዘተ፤
  የቸከ  ቢመስልም  ይህንን ለማለት እፈልጋለሁ፤
 ምላጭ የሚያስውጥ እልህህን ዋጥ አደርገህ ቁጭ ብለህ ተነጋገር    ፤ ስለ እርቅ ፤ ሰለ ጉማ ፤ የጋራ አገርን  አልምቶ በጋራ ስለመክበር ተነጋገር፤
ያለፈው አልፏል፤  በህይወት የቀረነው አብረን  እንድንኖር ተፈርዶብናል ፤  ምርጫ ካለን በሁለት ነገሮች ላይ ብቻ ነው ፤  እየተራረድን  ወይስ  እየተራረምን እንኑር?  ሁለተኛውን ተስፋ አደርጌ ልተኛ
Filed in: Amharic