>

ምርጫን የሁሉም ነገር መፍትሔ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም....!!! (የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ)

ምርጫን የሁሉም ነገር መፍትሔ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም….!!!

የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ

የአዲሱ መንግስት ተቀዳሚ ተግባር?  ብሔራዊ መግባባት? ህገ መንግስት ማሻሻል ? ተቋማት ግንባታ?ሰብአዊ መብት….???

• ነፃ ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ ፍፁም የበቃ ምርጫን መጠበቅ አስቸጋሪ ነው
• ከመንግስት ገለልተኛ የሆነ የብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን መቋቋም አለበት

“የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ” መሥራችና ታዋቂው የሰብአዊ መብት ተሟጋች አቶ ኦባንግ ሜቶ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቆይታ፤ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በተቋማት ግንባታ፣ በህገ-መንግስት ማሻሻል፣ በብሔራዊ መግባባት፣ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ  አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

ባለፈው ሰኔ 14 የተካሄደውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
እኛ ለምርጫ ፖለቲካ ገና ነን፡፡ ይሄኛው እንኳ ገና 6ኛው አገራዊ ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ የበቃ ምርጫ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ነፃ ተቋማት ባልተገነቡበት ሁኔታ ፍፁም የበቃ ምርጫን መጠበቅ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ብዙ ሃገሮች እንዲህ ያሉ ለውጦች ሲያደርጉ የሚያስቀድሙት ምርጫን አይደለም፡፡ ተቋማዊ ለውጦችን ነው፡፡ አያሌ በቀውስ ውስጥ ያለፉ አገራት መጀመሪያ ምርጫን አይደለም የሠላምና መረጋጋት መንገድ ያደረጉት፡፡ እነዚህ አገራት ሁለት አይነት ለውጥ (ሪፎርም) ነበር ያደረጉት፡፡ አንዱ ህገ መንግስትን መለወጥ ነው፡፡ ህገ መንግስት ማለት ሃገር የምትመራበት “ማኑዋል”  ማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ህገ መንግስት፣ የዜጎች ሳይሆን የብሔር ብሔረሰቦች ነው፡፡ ለዚህ ነው ዛሬ ዜጎች እንደ ዜጋ ሳይሆን እንደ ብሔር እየተለዩ መከራ ላይ የሚወድቁት። የኛ ህገ መንግስት የቆመው ለብሔር ብሔረሰቦች ነው ቢባልም፣ ይሄን መብት እንኳ በተግባር ማስከበር የቻለ አይደለም፡፡ የትም ሃገር ብንሔድ ህገ መንግስት ለዜጎች ነው የሚቆመው፡፡ ታላላቅ ስኬት ላይ የደረሱ ሃገሮች ህገ መንግስታቸው ዜግነትንና ዜጋን ያማከለ ነው፡፡ የህገ መንግስት መቃናት ለብዙ ነገር መቃናት ምክንያት ይሆናል፡፡ የምንፈልጋቸው ጠንካራ ነፃ ተቋማትም የሚመነጩት ከህገ-መንግስቱ ነው፡፡ አሁን ያለው ህገ-መንግስት ለብሔር የቆመ እንደመሆኑ ተቋማቱም ከዚህ እሳቤ ነፃ ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን መከላከያ አደረጃጀት እንኳ ብንመለከት፣ በአንድ ብሔር የበላይነት የተያዘ ነበር፡፡ ይሄ የሆነው በህገ መንግስቱ ምክንያት ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ ከማንም በላይ የብሔሮች ህልውና ላይ ያነጣጥራል። ተቋማት በሙሉ የተሰሩት ለዜጎች እንዲሆኑ ሳይሆን ለብሔረሰቦችና ለቡድኖች እንዲመቹ ተደርጎ ነው፡፡ አሁን ይሄን ችግር ነው በግልፅ እያየን ያለነው፡፡ ምርጫውም በዚሁ ሂደት ያለፈ በመሆኑ የተለየ ነገር መጠበቅ የለብንም፡፡
በእርስዎ ምልከታ የለውጥ ሂደቱ  ይበልጥ እየተፈተነ ያለው በምንድን ነው?
በለውጡ ሹፌሩ ተለወጠ እንጂ መኪናው ያው ነው፡፡ ተመሳሳይ መኪና ነው፣ መሪ የተለወጠለት፡፡ ይሄ መኪና ተመሳሳይ ተሳፋሪዎች ነው ያሉት፤ ብሔር ብሔረሰቦች፡፡ ያውም ብሔር ብለው ስነ ምግባርና እውቀት የሌላቸው አካላት የሞሉበት መኪና ነው፡፡ ከሹፌሩ ጀርባ ያሉ ሃይሎች እንዴት ይግባቡ የሚለው ላይ ነበር ከምርጫው በፊት መሰራት የነበረበት። የብሔር ማንነትና ጥላቻ ላይ የነበረው አካሄድ ከምርጫው በፊት መፍትሔ ቢያገኝ ጥሩ ነበር፡፡ ከህገ መንግስቱ የመጣው ሳንካ ሁሉ ተነቅሎ፣ ሰው በሰውነቱ የሚከበርበት፣ በኢትዮጵያዊነቱ አንገቱን ቀና አድርጎ የሚሄድበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ነበር። ይሄ ቢሆን ኖሮ ወደ ጦርነትም ባልተገባ ነበር። ቀደም ሲል የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን ተቋቁሟል። ግን ጦርነቱን ለመከላከል ምን ሰራ? የድንበርና ማንነት ኮሚሽንም ተቋቁሟል። ግን ምን ሰራ? ብዙ መሰራት ያለበት ነገር ባለመሰራቱ ችግሮችን አወሳስቧል፡፡ ይሔ ምርጫም ቢሆን በብዙ ችግር ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ ኦሮሚያ ላይ ኦፌኮ እና ኦነግ ፓርቲዎች አልተሳተፉም። ከዚህ አንፃር ይሄ ምርጫ ብቻውን እንደ ትልቅ ስኬት ሊታይ አይችልም፡፡ ትልቁን ውጤት የሚያመጣው የብሔራዊ መግባባት መፈጠር ነው፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ መግባባት ሲባል እንደ ስልጣን መቀማት ስለሚታይ ተቀባይነት ሲያገኝ አንመለከተውም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ገና በለውጡ ጅማሮ፣ ለብሔራዊ መግባባት በር መክፈት ነበረባቸው፡፡ ከምርጫው በፊት ቢደረግ ኖሮ፣ ከምርጫው ራሱን የሚያገል ፓርቲ አይኖርም ነበር፡፡ አሁን ከምርጫው በኋላም  ቢሆን መካሄድ አለበት፡፡ የተበላሸውን ለማቃናት ብሔራዊ መግባባት ወሳኝ ነው፡፡ ምርጫን የሁሉም ነገር መፍትሄ አድርጎ ማሰብና መረጋጋት ግን የሃገሩን ችግር በውል አለመረዳት ይመስለኛል፡፡
በምርጫ አሸናፊው መንግስት በቅድሚያ ሊያከናውን ይገባል የሚሉት ተግባር  ምንድን ነው?
ከሁሉ በፊት ሃገርን ማረጋጋት ነው መቅደም ያለበት፡፡ ህዝባችን ፍጹም ሰላም ይፈልጋል፤ መረጋጋት ይሻል፡፡ ስለዚህ በመላ  አገሪቱ  የሰከነ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ መሪዎች ቀና መሆን አለባቸው፡፡ የህዝብ ጥቅም ማስቀደምና ለህዝብ ድምፅ ጆሮ መስጠት አለባቸው። መሪ ሃገሩን የሚመሩበት መንገድ ቀና ከሆነ ተመሪውም እየተስተካከለ ይሄዳል። ከዚህ ቀናነት ባለፈ አፋጣኝ የብሔራዊ መግባባት መድረክ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የብሔራዊ መግባባት መድረክን የሚያዘጋጁ ሰዎች ደግሞ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ፍፁም ገለልተኛ የሆኑ ሰዎች መሆን አለባቸው። ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ የሆነ ገለልተኛ የብሔራዊ መግባባት ኮሚሽን  መቋቋም አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች በጠ/ሚኒስትሩ የተመረጡ ሳይሆን በህዝብ የተመረጡ መሆን አለባቸው፡፡ የጠ/ሚኒስትሩን አደራ ሳይሆን የህዝቡን አደራ በእምነት የተቀበሉ መሆን ይገባቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች እስከ መንደር የሚደርስ መዋቅር ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ተቋሙም በዚህ መልኩ ነው መደራጀት ያለበት፡፡ ይሄ ተቋም በመጀመሪያ ችግሩን ማጥናት አለበት፡፡ ችግሩን ካጠና በኋላ በየደረጃው ለውይይት ያቀርባል። ከውይይቱ ለሃገር የሚጠቅምና ሃገርን ወደፊት የሚያሻግር ሃሳብ  ይመነጫል። በዚህ መንገድ እውነተኛ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ፣ ብሔራዊ መግባባት ነው ሊደረግ የሚገባው፡፡ ይሄ ሲደረግ ነው ሃገርን ወደ ተሻለ ሰላምና መረጋጋት አሻግሮ፣ ህልውናዋን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማቆም የሚቻለው፡፡
ከሰብአዊ መብት አጠባበቅ አንፃርስ ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል?
የኔ ትልቁ ምኞቴ፣ ማንም ሰው ድሃም ይሁን ሃብታም፣ መብቱ በምንም መንገድ እንዳይነካ ነው፡፡ ሁሉም ሰው መብቱና ክብሩ ተጠብቆ መኖር አለበት፡፡ ስለዚህ መንግስት ከሁሉም ነገር በፊት ሰብአዊነትን ማስቀደም አለበት፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ዋጋ የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ ከቁስ በላይ የሰው ነፍስ የሚገደው መሆን ይኖርበታል፡፡ እኔ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ስል፣ የብሔሮች መብት እያልኩ አይደለም፡፡ የዜጎች መብት እያልኩ ነው፡፡ የእያንዳንዱ ዜጋ ክቡር ሰብአዊ መብት ነው ሊከበር የሚገባው። ሌላው በዚህ የመብት ጥበቃ የሚረጋገጥ ነው የሚሆነው፡፡ ሰው በሰውነቱ ብቻ፣ ክብሩ ሙሉ ለሙሉ መጠበቅ አለበት፡፡
ሌላው በየቦታው ያሉ ግጭቶች መቆም አለባቸው፡፡ ቂም በቀሎች እንዳይኖሩ፣ ሰዎች እንዳይሞቱ መንግስት መከላከል አለበት፡፡ ላለፉት 3 ዓመታት ሰዎች ሲገደሉ የነበረው በመንግሰት አልነበረም፤ እርስ በእርስ እንዲሁም በታጣቂዎችና በሁከተኞች ነበር ሰው ሲገደል የነበረው፡፡ አሁን ግን ለዚህ አይነቱ ችግርም መንግስት ሀላፊነት አለበት። እያንዳንዱን ዜጋ ከጥቃት የመከላከል ግዴታ የመንግስት ነው፤ ዋና ስራው የዜጎችን መብት መጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በሌላ ሃይል ማሳበብ ከተጠያቂነትና ከሃላፊነት አያድንም፡፡

Filed in: Amharic