“የኢትዮጵያ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪነት ከማገልገል እንዲታገዱ ተጠየቀ…!!!”
በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪነት ከማገልገል እንዲታገዱ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ጥሪ አቀረቡ። የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር ጥሪውን ያቀረቡት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ነው።
ዘጠነኛ ወሩን ሊደፍን በተቃረበው የትግራይ ግጭት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከኤርትራ ወታደሮች እና ከሌሎችም የታጠቁ ሃይሎች ጋር በመሆን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የሚሳዩ ማስረጃዎች አሉ ሲሉ ሊቀመንበሩ በደብዳቤያቸው ወንጅለዋል። ሴናተሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ከከሰሱባቸው ወንጀሎች መካከል በተደራጀ ሁኔታ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር፣ ሰላማዊ ሰዎችን ማስራብ፣ የዘፈቀድ ግድያዎች እና ጭፍጨፋዎች ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ወታደሮቹ በጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ስር ሊመደቡ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲሉ ይከስሳሉ።
የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በዘግናኙ የትግራይ ግጭት ላይ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች በሺህዎች በሚቆጠሩ የትግራይ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የጭካኔ ተግባር በመፈጸም ይወነጀላሉ” ያሉት ሜንዴዝ፤ በእንደዚህ አይነት ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪነት ለማገልገል “ብቁ አይደሉም” ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ በአጽንኦት አሳስበዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ወታደሮች ከሚያዋጡት አንዱ እንደመሆኑ፤ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት በሰላም ማስከብር ተልዕኮዎች ላይ የሚመደቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ስለመሳተፋቸው ብርቱ የማጣራት ሂደት እንዲያከናውን እንጠይቃለን” ሲሉ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር በደብዳቤያቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በ1995 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ፤ የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ በሰብዓዊ እና የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ እና በደል እንዳይፈጸም ለመከላከ እርምጃዎች እንዲወስዱ ኃላፊነት እንደጣለባቸው ሜንዴዝ በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል። የመንግስታቱ ድርጅት በ2003 ዓ.ም ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የቅድመ ማጣራት ፖሊሲም፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እና የሰብዓዊ መብቶች ህጎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመጣስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በሰላም አስከባሪነት ከመመደብ እንዲታገዱ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።
የመንግስት ኃይሎች እነዚህን መሰል የጭካኔ ተግባራት ለመፈጸማቸው ተጠያቂ በሚሆኑበት ወቅት፤ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሚመደቡ የየሀገራቱ የፖሊስ እና ወታደራዊ ሰዎች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተለመደው የማጣሪያ ሂደት በመሻገር በጥብቅ የሚፈተሽበት አሰራር እንዳለው ሜንዴዝ በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም በብሩንዲ እና ሲሪላንካ የመንግስት ኃይሎች ላይ የተካሄደውን መሰል የማጣራት ስራንም በምሳሌነት አንስተዋል።
“የወታደራዊ ኃይሎች የቀደመ ድርጊት፤ በሰላም አስከባሪነት በሚሰማሩበት ጊዜ እንዴት ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ ሁነኛ ማሳያ ነው” ያሉት ሜንዴዝ፤ “ያለምንም ተጠያቂነት ተግባራቸውን ማከናወን የለመዱ ወታደሮች ሰማያዊውን [የሰላም አስከባሪዎች] ቆብ ስላጠለቁ ብቻ ይህን አካሄዳቸውን መቀየራቸው የማይሆን ነገር ነው” ሲሉ የጥብቅ ማጣራቱን ሂደት አስፈላጊነት አጠይቀዋል።
“የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎችን በሰላም አስከባሪነት ማሰማራት ያለውን አስከፊ መዘዞች ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በትግራይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በገለልተኛ አካል ተዓማኒ ማጣራት እስኪደረግባቸው ድረስ በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪነት ከማገልገል መታገድ አለባቸው” ሲሉም የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር ጠንከር ባሉ ቃላት አቋማቸው አሳውቀዋል። ይህንን የማጣራት ስራው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ሊያካሄድ እንደሚችልም ጥቆማቸውን ሰጥተዋል።
የሴናተር ሜንዴዝ ጥሪ፤ ከትግራይ ቀውስ ጋር በተያያዘ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በተከታታይ እየወሰደቻቸው ያለቻቸው ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች እና የበረቱ ጫናዎች አንድ ማሳያ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከትላንት በስቲያ ሰኞ በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ ላይ ያለው ውርጅብኝ ‘ለቅሶው ከፍየሏ በላይ ነው’ ከሚባለው በላይ ነው” ብለው ነበር። በሌሎች ሀገራት ላይ ለሚፈጸሙ ተመሳሳይ ሁነቶች የሚሰጠው ምላሽ እና በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው “አራምባ እና ቆቦ” ነው ሲሉ በኢትዮጵያ ላይ ጫና መበርታቱን አምነዋል። ()