>

ይሄኔ ነው አልሲሲን ማየት... (ኤልያስ ደግነት/የሺ/)

ይሄኔ ነው አልሲሲን ማየት…

ኤልያስ ደግነት/የሺ/


‹‹የምን ውኃ ብቻ የምን አፈር ብቻ፣

ወርቅም እናፍሳለን በፍየል ስልቻ፤›

ብለው ነበር

ከሁለተኛው ዙር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሙሊት በኃላ አንዳች ነገር እንደሚፈስክልኝና እንደሚበልግልኝ ይሰማኝ ከጀመረ ከዓመት በላይ ሆኗል፡፡ በተለይ ከዓባይ ጋር ተያይዞ ያሉ አንዳንድ መሰናዶዎችን ለመስራት ብዙ አርቲክሎችን ማንበብ ስጀምር በብዙ መልኩ እልህ የሚያሲዙ ነገሮች ውስጤ ይፈጠሩ ነበር፡፡

በተለይ ግብጽ ከጥንት እስከ አሁን ኢትዮጵያን ሠላምና መረጋጋት ያላትና በምጣኔ ሀብት የበለፀገች ሀገር እንዳትሆን፤ አቅም ኖሯት የዓባይን ግድብ እንዳትገነባ፤ በእርስ በእርስ ጦርነትና የጎሣ ግጭት ተወጥራና ሳትረጋጋ እንድትኖር ለማድረግ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ምን እንዴት ስታሴርና ሰትዶልት እንደኖረች በብዙ ማስተዋል ለጀመረ ሰው ንዴቱ ከአንጁቱም አይወጣም፡፡

የግብፅ መሪዎች በረዥም ጊዜ የስትራቴጂ እቅዳቸው ውስጥ ቀርፀው በማስቀመጥና በአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የተነሱትን ተቃዋሚዎችና የጎረቤት መንግሥታት ሶማሌያንና ሱዳንን ጭምር ሲረዱና ኢትዮጵያን በጦርነት ውስጥ ሲያምሱ መኖቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ሌላው እጅግ አስገራሚው እና አሰቂኙ ነገር በጃንሆይ ዘመን መንግስት ጊዜ በኤርትራ ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ትቀላቀል ወይስ አትቀላቀል ብሎ አባል ሀገራትን ሲያወያይና ሀሳብ ሲሰበስብ ግብጽም ከላይ ሆኜ ዓባይን እቆጣጠራለሁ በሚል ኤርትራን ማስተዳደር ያለብኝ እኔ ነኝ ብላ የመከራከሯ ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ለማውራት ይህን ያነነብኩ ቀን ለካ የሀገርም ጅል አለውና ብዬ ተሳልቂያለሁ፡፡

በዚህ ያላበቃችው ግብፅ ኢትዮጵያ አቅም አግኝታ በዓባይ ውኃ ላይ ግድብ እንዳትሰራ በምዕራቡ ዓለምና በዐረቦች መካከል ያላትን ተደማጭነትና የፖለቲካ ሚዛን፤ ከእሥራኤል ጋር የተደረገውን የካምፕ ዴቪድ ስምምነት በመጠቀም፤ ሌሎችንም በማስፈራራት ዓለም ባንክና አይ ኤም ኤፍ፤ ዓለም አቀፍ ገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ለኢትዮጵያ የዓባይ ግድብ ግንባታ ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳያበድሩ በቀጥታም በተዘዋዋሪም እርዳታ እንዳያደርጉ አድርጋለች፡፡ ጃንሆይም እኛ ባንሰራውም መጪው ትውልድ ይሰራዋል ብለው ህልማቸውን ለፈጣሪም ለመጪው ትውልድም ትተውት አለፉ፡፡ እንሆ መቶ ዓመታት ሳይቆጠሩ እንዳሉትም ተስፋ የተጣለበት የእኔ ትውልድ የአባቶቼንማ አደራ አልበላም ብሎ እውን ያደርገው ይዟል!!

አጅሪት ግብፅም ማድረግም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን እንዴትም አደርጋ ዓባይን አትገነባም በሚል ርግጠኝነት እንዲህ አያለችም ከበሮ ስትደልቅ ከረመች

‹‹የምን ውኃ ብቻ የምን አፈር ብቻ፣

ወርቅም እናፍሳለን በፍየል ስልቻ፤›

የግብፅ እብሪት የሞላው እርግጠኝነት ፉሩሽ ሆኖ ዛሬ ሀገሬ በክብር በኩራት እንደ ቃሏ ጅንን ብላ ባከናወነቸው ሁለተኛው ዙር ሙሌት ግብፅ እና ግብፃዊያን በንዴት ጦፈው ጭስ በአፍ እና በአፍንጫቸው ይወጣ ይዟል፡፡ ይሄኔ ነው አልሲሲን ማየት!!

ኢትዮጵያችን ይህን የዘመናት አሻጥር ሁሉ አልፋ ዛሬ በኩራት ከፍ እንድትል ላደረጋት ፈጣሪ ክብሩ ይስፋ!!!

****ሀሳቡን ከማመንጨት እንዲሁም ይህ ትውልድ እንደሚሰራው እርግጠኛ ከነበሩት ከጃንሆይ ጀምሮ አደራቸውን በየዘመናቸው ተቀባብለው እዚህ አድርሰው የዛሬን ቀን ላሳዩን ሁሉ እንሆ አኮቴት ለከበረ ተግባራችሁ ብለናል!!

****ከጉድለታችሁ ላይ ከወር ደመወዛችሁ ቀንሳችሁ ቦንድ በመግዛት የተሳተፋችሁ ለእንናተም እንዲሁ ክብር ይግባችሁ!

**** በዛ ነዲድ ሙቀት ተቃጥላችሁ ቀን ከሌሊት ለሰራችሁ ፣ ደህንነቱን በንቃት ስትጠባበቁ ለከረማችሁ የሀገር መከታ ለሆናችሁ የመከላከያ አባለት በሙሉ ወፍራም ምስጋና ይድረሳችሁ!!

****ኢትዮጵያ በቅጡ የሚናገርላት እውነቷን የሚያስረዳላት …አንደበት የሚሆናት ዲፕሎማት የላትም ወይ ተብላ እስክትብጠለጠል ድረስ በዓለም መድረክ ብቸኛ ስትሆን …ሳይከፈላችሁ …ሳትታክቱ … በየ ሚዲያው እየቀረባችሁ ስትሟገቱ ለሰነበታችሁ ….አውጫጭኙን ሳትፈሩ ለተጋፈጣችሁ እና ያንን የአልተገራ የአረብ ጭባ አንደበት ላዘጋችሁ ለእናንት ለኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በሙሉ ብድር ይግባችሁ…ትውልድ ውለታችሁን ይክፈል….የማያልቅ ክብር …ፍቅር …ሞገስ ይስጣችሁ!

በማያልቅ ኩራት እና ክብር ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ደግሞ የከርሞ ሰው ብሎን ለሶስተኛው በሰላም ያድርሰን!!1

 

 

Filed in: Amharic