>

ይድረስ ለ'ኔ ትውልድ፦ (ጎዳና ያእቆብ)

ይድረስ ለ’ኔ ትውልድ፦

ጎዳና ያእቆብ

 

*… ከሦስት ሺ ዘመን በላይ በስነ ጽሑፍ — በኪነ ህንፃ — በስነፈለክ — በአገር-መንግስት — ፤ የዚህ ሁሉ ማዕቀፍ በሆነው ሀይማኖት የዳበረችን ኢትዮጵያ ‘ለሀምሳ ዓመት ፖለቲካ ተብዬ’ አሳልፈህ ልትሰጣት ተባባሪ አትሁን !
          የ’ኛ ትውልድ በግዜ-ወንዝ የውሃ ጠብታ ያህል ነው። ዛሬ አግዝፈን ያነወርነው – ነገ በግዜ ንስሀ ይታጠባል።
ልዑል እግዚአብሔር  <በወንድማማቾች መሀከል ጠብን የሚዘራን> አብዝቶ ይፀየፋል። በአንደበትህ ወይም ከዕእምሮህ ጓዳ በብዕርህ ጫፍ መልካም ፍሬን ዝራ::
እግሮችህ የረገጧትን ወይም ነገ ከነግ ወዲያ ልትሳለማት የምትመኛትን አክሱም ፅዮንን አስብ፣. . . በአድዋ ከፍታ ላይ ሁሌም የሚያንፀባርቀውን የአባቶቻችንን አሻራ ፈትሽ፣ ከስጋዊ ወንድማማችነትም በላይ በአንዲት ቤተክርስትያን ያገኘነውን ልጅነት አብዝትህ ዋጋ ስጠው ::
ከሦስት ሺ ዘመን በላይ በስነ ጽሑፍ — በኪነ ህንፃ — በስነፈለክ — በአገር-መንግስት — ፤ የዚህ ሁሉ ማዕቀፍ በሆነው ሀይማኖት የዳበረችን ኢትዮጵያ ‘ለሀምሳ ዓመት ፖለቲካ ተብዬ’ አሳልፈህ ልትሰጣት ተባባሪ አትሁን !
ከዚህም ከዚያም በሚወረወረው የማጠልሸት ‘ፕሮፓጋንዳ’ ሱታፌ አታድርግ፣… የትግራይ ማህበረሰብና የአማራዉም ሆነ የተቀረው  የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከሚያለያየው የሚያስተሳስረው እሴት በጅጉ እንደሚልቅ አትዘንጋ፣… እዚህም እዛም ውህድ ማንነት ያላቸው የትየለሌ ዜጎች መኖራቸውን ልብ በል፣… ኦርቶዶክሳዊነትን ማቀጨጭ ግቡ ለሆነ አካል መሣርያ አትሁን፣…በየአቅጣጫው የቀጠለው የአማራ ማህበረሰብ ሰቆቃና ሞት አንተ በመረጥከው መንገድ እንደማይገታ መርምር፣…በማህበራዊ ሚዲያ ሞቅታ አትዋኝ።
በመጨረሻም የምማፀንህ ኢትዮጵያን የምትወድና ለሕዝቧም የምትጨነቅ ከሆነ . . .ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ከተነሳ እኩይና ቆሻሻ ‘የሀምሳ ዓመት ፖለቲካ ተብዬ’ ፈፋ ውጣና  ከበጎ ህሊና የሚመነጭ  የትግራይንና የተቀረውን የሀገሬን ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ የሚያቀራርብ የራስህን ጡብ አስቀምጥ።
በዚህ አስተሳሰብ ከወዳጆችህ አንድም…ሁለትም… ብታፈራ በቂ ነው። ቸር ያክርመን።
Filed in: Amharic