>

ሰው የለንም፣ አስታራቂም የለንም… ለእኛው ያለነው እኛው ነን!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ሰው የለንም፣ አስታራቂም የለንም… ለእኛው ያለነው እኛው ነን!!!

አሰፋ ሀይሉ

 

We Are the World!
የትግራይና የአማራ ህዝብ ከቋንቋው በቀር በሁሉ-ነገሩ የሚመሳሰልና አብሮ የኖረ ወንድማማች ህዝብ ነው! ቋንቋውም ትግርኛ ማለት አማርኛን እያስቆጡ መናገር ነው ከመባሉ በስተቀር ሁለቱም ከአንድ አባታቸው ከግዕዝ የፈለቁ ናቸው፡፡ ትግሬንና አማራን አይተህ ራሱ በመልክ አትለየውም!
እንደ ስልጤና ጉራጌ የኛ ጀበና አፍንጫ አለው፣ የናንተ የለውም፣ የኛ ሹሩባ ከፍ ያለ ነው፣ የናንተ ትንሽ ነው እየተባባልን ማንነትን ወደ መሰነጣጠቅ እንሂድ ካላልን በስተቀር የትግሬ የሆነ ሁሉ የአማራ ነው፣ የአማራ የሆነ ሁሉ የትግሬ ያልሆነ የለም! ገዢ ንጉሦቻችን፣ ተራው ህዝባችን፣ አብሮ ሲኖር፣ ሲጋባና ሲዋለድ የኖረ ህዝብ ነው፡፡
ቄሶቻችን ቅኔና ዜማ አንዳቸው ከሌላኛቸው እየተለዋወጡ፣ በሰሜን አፍሪካ ብቸኛውን የክርስትያን ደሴት የፈጠሩ ናቸው፡፡ ጎንደር ካቶሊክን ስታስገባ፣ ኢሮብም ካቶሊክን ቀድማ ያስገባች ነች፡፡ ሁለቱም ሕዝቦች እስልምናንም፣ ሌላውንም እምነት አክብረውና ተቀብለው የኖሩ ናቸው፡፡
ክራራችንና ከበሯችን፣ ዋሽንትና መሰንቋችን ሳይቀር የጋራችን ነው፡፡ የትግሬ ሴት የአማራን ባል፣ የአማራ ወንድ የትግሬን ሚስት ይመርጣል፡፡ አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ ጥቂት እንከኖች ባይጠፉም፣ ሁለቱም ህዝብ በአልገዛም ባይነትና፣ በጀግንነት አብሮ ተረዳድቶ የኖረ የአንድ እግዜርን የሚፈራ ጨዋ ቤተሰብ ልጅ ነው፡፡ የሀገር ልብሳችንን ሳይቀር አብረን የምንጋራው ነው፡፡ የሚቀርብን ምኑ ነው?
የአማራ ሴት ሽሮ ወጥ ሽንኩርት ይገባበታል፣ የትግሬ ምጥን ነጭ ሽንኩርት የለውም – በሚል እንጨቃጨቅ? የትኛው ልዩነታችን ነው? ገበሬውስ አንዱ ከሌላው በምን ይለያልና በምን ይሻላል? ያው አብረን የፈረደበትን አፈር ስንገፋ የኖርን ባላገሮች አይደለንም ወይ ሁለታችንም፡፡ ከተቀረውም የኢትዮጵያ ክፍል እጅግ በሚልቅ መልኩ ባህልም፣ ታሪክም፣ እምነትም፣ ጉርብትናም፣ ዝምድናም፣ እህሉንም መጠጡንም፣ ሠማዩንም ምድሩንም አብሮ ተጋርቶ – ከአማራና ከትግሬ በላይ ለዘመናት የኖረ ሕዝብ የለም! እውነቱ ይህ ነው!
ወያኔን አለመውደድ መብት ነው! ወያኔን አልወደውም! ለኢትዮጵያ ታሪክ እና ለዘመናት አብሮነታችን ባለው ጠባብ አመለካከቱ አልወደውም፡፡ እንዲያም ሆኖ ወያኔ ከሆኑ (ከወየኑ) እጅግ ብዙ ወዳጆች ጋር በልዩነታችን ፍቅራችንን አስፍተን አብረን ኖረናል፡፡ አብረን በልተን፣ ጠጥተን፣ ክፉ-ደጉን አሳልፈን ብዙ ዓለም አይተናል፡፡ ብዙ ወንድማማችነት አሳልፈናል፡፡
ትግሬው ሁሉ አንድ ነው ያለው ማነው? በጣት አሻራው ልክ፣ በስሙ ልክ፣ በቤተሰቡ ልክ፣ በቁመቱ ልክ፣ እልፍ ዓይነት ትግሬ አይደለም ወይ ያለው? ከትግሬውም መሐል እኮ ሌላን ትግሬ የሚገድል፣ የሚሰርቅ፣ የሚዘርፍ፣ የሚነጥቅ፣ መዓት የዞረበትና ክፉ ትግሬ አለ፡፡ በትግሬ ላይ ወንጀል የሚፈጽም ትግሬ ስላለም ነው በትግራይ ፖሊስና ፍርድቤቶች ሥራቸውን የሚሰሩት፡፡
ልክ እንደዛው አማራውስ አንድ ነው ያለው ማነው? ለአማራው ሁልጊዜም አማራው ነው መድሃኒቱ ያለው ማነው? ከአማራውም መሐል አማራውን የሚገድል፣ የሚሰርቅ፣ የሚያጎድል፣ የሚነጥቅ፣ የሚሞስስ፣ መዓት የዞረበት አማራም አለ፡፡ ስላለም ነው በአማራም ምድር ፍርድቤቶችና ፖሊሶች ሳይታክቱ የሚሰሩት፡፡ ይሄን የምለው ለምንድነው?
ይሄን የምለው ለትግሬው ከዞረበት ትግሬ ይልቅ፣ ሠላማዊና ሰው-ወዳድ ጨዋ አማራ ይሻለዋል ለማለት ነው፡፡ ለአማራውም ከዞረበት አማራ ይልቅ ጨዋውና ሰው-ወዳዱ ትግሬ ይቀርበዋል ለማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ እንደ ነብር ወይ እንደ ማንጎ በዘር አንድ ተደርጎ በደመነፍስ ብቻ ሳያስብና የራሱን ባህርይ ሳይላበስ አይወጣም፣ አይኖርም፣ አይሞትም፡፡ ሁሉም የየራሱ የተለየ ባህርይ አለው፡፡ ክፉ ሰው አለ፡፡ ደግ ሰው አለ፡፡ ከማንጎም መሐል የተለየ ጣዕም ያለው አለ፡፡ የእናት ሆድም ዥንጉርጉር ነውና ከአንድ ማህጸን ወጥቶ አንዱ ቅን አንዱ ቅንቅን ይኮናል፡፡
ስለዚህ በአማራውና በትግሬው ሕዝብ መሐል የጠብ ግድግዳ የገነቡና የሚገነቡት ጥቂቶች ናቸው፡፡ አብሮ ተዋዶና ተከባብሮ ተፈላልጎ፣ አብሮ ነግዶ፣ አብሮ አትርፎ፣ በፍቅርና በዝምድና ለዘመናት በኖረው በአማራውና በትግሬው ሕዝብ መሐል ጠብን የዘሩትና የሚዘሩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነዚያ ነገር-ዓለሙ የዞረባቸው ጥቂቶች ናቸው ብዙዎቻችንን በሠላም የኖርነውንና የምንኖረውን ወንድማማቾች ወደ ጠብ የሚነዱን፡፡ እነዚያን ጥቂቶች ተዉ የሚል፣ የሚያስታግስ፣ የሚመክርና የሚኮንን ጠፍቶ ነው – ይኸው ጠንቃቸው ለሁላችንም የተረፈን፡፡
ይኸው በጥቂት መሠሪዎች ሥራ የተነሳ – ሩቅ ስላለው ስለማያውቀው ሰው ጎጆ አንዳችም የክፋት ሀሳብ የሌለውን – 95 በመቶ የሚሆነው ለፍቶ ኗሪ የትግራይና የአማራ ሕዝባችን – እርስ በርሱ በተቃራኒ ምሽግ እየቆፈረ እንዲጋደልና እንዲባላ ሆነ፡፡
አብዛኛው ህዝባችን እኮ የዕለት ኑሮውን ከመኖር፣ የጎረቤቱን ችግር ከመሸፋፈን፣ የዘመዱን ለቅሶ ከመድረስ፣ ቤተክርስትያን ተሳልሞ ተመስገን ብሎ ያለችውን ቀምሶ ከማደር ውጭ፣ ወይም ልጁን ለወግ ለማዕረግ አብቅቶ፣ ወይም የዘመድ ወዳጅ ሰርግና ድግስ በልቶ በሠላም ዘፍኖና ጨፍሮ ፈጣሪውን አመስግኖ ወደጎጆው ከመመለስ በቀር እኮ – አንዳች እላፊ ክፋት በዞረበት የማይዞር የዋህና ኩሩ ጨዋ ህዝብ እኮ ነው፡፡
እነዚህ ጥቂቶቹ – ሩቅ ተሻግረው ጥላቻና ነገር የሚቆሰቁሱት፣ ጠላትና ነገር የሚገዙለት፣ ፀብና ጦርነት የሚነዙለት – ጥቂቶቹ – ያንን በሚሊዮን የሚቆጠረውን ለፍቶ ነዋሪ ጨዋውን ሠላማዊውን ህዝባችንን ከየቤቱ ጎትጉተው የደም ግብር ያስከፍሉታል፡፡ ለሞትና ለውድመት ይዳርጉታል፡፡ በመንገድ እንኳ ተላልፎት ከማያውቀው ወገኑ ጋር ጠላት-ጠላት እያሉ ያጋድሉታል፡፡ ደም ያቃቡታል፡፡ የእምነት ክሩን ይበጣጥሳሉ፡፡ አንድነቱን ይሸረሽራሉ፡፡ ታሪኩን ይቦረቡራሉ፡፡
ሁሌም ችግሮቻችን ሁሉ የሚመነጩት ከእነዚህ ከክፉዎችና ጽንፈኞች ነገረኞች ጥቂቶች ነው፡፡ እንጂ 95 ፐርሰንቱ ህዝባችን – የራሱን ኑሮ በጨዋነት የሚመራ፣ ታታሪና ለቃሉ ያደረ፣ ጨዋ እና ውብ ባለ ድንቅ ባህል ህዝብ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ለዚህ እውነት የአፍታ ጊዜ መስጠት መቻል አለብን፡፡
ዛሬ ላይ በወገኖቻችን የደም ባህር ላይ እየዋኘን እያለ – እነዚህን የትግሬንና የአማራን ህዝብ የጋራ አኩሪ ማንነቶችና በፍቅርና ጉርብትና ዝምድና ለዘመናት አስተሳስረው በአንድ ጣሪያ ሥር ያኖሩንን እልፍ ድንቅና ውብ የጋራ እሴቶቻችንን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ትግሬና አማራ ጠላቶች አይደለንም፡፡ ልንሆንም አንችልም፡፡ ወንድማማቾች ግን ነን፡፡ እህትማማቾች ግን ነን፡፡ ቤተሰቦች ግን ነን፡፡ ወገኖች ነን፡፡ ያገር ልጆች የማር እጆች ግን ነን፡፡ ሌላው ቅር ካልተሰኘብኝ – እውነቱን ለመናገር – በዚህች በኢትዮጵያችን – ከእኛ ከትግሬና ከአማራው በላይ – አንዱ ለአንዱ የሚቀርብ ዘርም ዘመድም ወገንም የለም፡፡ እውነቱ ይኸው ነው፡፡
የጥላቻና የፀብ አጋጣሚ ተገኘ ተብሎ፣ ዝም ተብሎ ለሺህ ዓመት የማያበቃ የጥላቻ ክምር መከመር ምንድነው? ሰሚ አገኘሁ ባሩድ ጨሰልኝ፣ ነገር ተቀጣጠለልኝ ብሎ የጥላቻና የጠላትነትን ከበሮ ዝም ብሎ መደለቅ አዋቂነት አይደለም፡፡ አዋቂነት አይደለም ብቻ ሳይሆን ነውርም ነው፡፡ ነውርን የምናውቅ ህዝቦች ነን፡፡ ያጣላንም የሚያጣላንም ጥቂት ነገር ነው፡፡
ይመስለናል እንጂ ጥቂት ቀለም ጨምረህ የሰፊውን ባህር ውሃ ቀለም እንደማትቀይረው፣ ጥቂት ሰበቦች እየመዘዝክ ሰፊውንና ጥልቁን የአማራንና የትግሬን የዝምድና ባህር ቀለም በቀባኸው የጥላሸት ጥላቻ ቀለም መቀየር አይሳካልህም፡፡ በበኩሌ ወያኔም ያንን ማድረግ አልተሳካለትም ነው የምለው፡፡ ወያኔ ሃምሳ ዓመት ሙሉ የቂምና የልዩነት ሀሳብ ሲሰብክ የመኖሩን ያህል፣ በትግሬና አማራ መሐል ያለውን ፍቅር፣ ዝምድናና ቤተሰብነት የመበጠስ አቅሙ አልነበረውም!
ባሳለፍናቸው ቅርብ ዓመታት ልብ ብሎ ያየው የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ የወያኔን ሽማግሌዎች እንደ ጀግኖች ቆጥሮ የሚያከብር እንጂ፣ የጥላቻ ወሬያቸውን የሚሰማቸው የትግሬ ትውልድ አልነበረም፡፡
ትግራይ ሄደህ አንዱን የትግሬ ወጣት ስለ ኢህአዴግ የብሔር ፖሊሲ ላዋራህ ብትለው ከአጠገብህ በመቶ ሜትር ነው የሚሸሸው፡፡ ፍቅርና ጨዋታ፣ ቢዝነስና ሀገርን ያህል የሚሰፋ ወገን ቀርቦለት፣ የምን ያረጀ ያፈጀ ፖለቲካ ነው? ያንን እሴት በሂደት ማዳበር ስንችል፣ አጉል አድርገን፣ ፍቅራቸውን ነጠቅነው፣ ወያኔ ወደምትፈልገው የጥላቻ ምሽግ እንዲያፈገፍጉብን አደረግን፡፡
አሁንም አልረፈደብንም፡፡ ለፍቅርና ለእርቅ ለሠላም መቼውኑም ረፍዶ አያውቅም፡፡ ያልሞተ ሰው ለእነዚህ ድንቅ ነገሮች አይረፍድበትም፡፡ የሞተ ብቻ ነው ለፍቅር ዕድል የማይኖረው፡፡ አሁን በትግሬውና በአማራው ህዝብ መሐል የተተከሉበትን የጠብና ልዩነት አጀንዳዎች በሰከን አዕምሮ አንድ ሁለት ብለን ብናስቀምጣቸው – እርግጠኛ ነኝ – በቁጥር አምስቱን ጣታችንን እንኳ አይሞሉም፡፡ አምስት ሚሊዮን አንድ የሚያደርጉን ምክንያቶች እያሉ – በአምስት አይረቤ ልዩነቶች የተነሳ – ስንቋሰልና ስንደማማ መኖር አለብን?! ምን ሆነናል?
ተይ እንጂ ማሬ አስቢኝ፣ አንድ ቀን ወንድምሽ ነበርኩ! ተው ወገኔ አስብ፣ አንድ ቀን የልብ ጓደኛህ ነበርኩ! ተው እንጂ ወገን አንድ ቀን አንተ ዘንድ ስመጣ የባዕድነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር! አንድ ቀን እኔ ጋር ስትሆን ከወንድሜ ጋር ነኝ ብለህ ትመካብኝ ነበር፡፡
አንድ ቀን ቤተሰብ ነበርን! አንድ ቀን የአንድ እናት ልጆች ነበርን! አንድ ቀን አብረን ስቀናል፡፡ አንድ ቀን አብረን መከራን አልፈናል፡፡ አንድ ቀን ነግደናል፡፡ ወልደናል፡፡ ከብረናል፡፡ ተኳርፈናል፡፡ ታርቀናል፡፡ ዛሬ እንዴት ካልተላለቅን፣ ካልተጫረስን፣ ዘርና ዘር ካልተጨፋጨፍን አንላቀቅም እንባባላለን?
‹‹አስታራቂም የለን፣ እኛው እንታረቅ!›› እንዳለው ነው ዘፋኙ የኛ ነገር፡፡ ‹‹ሰብድየለይ›› ተብሎ እንደተንጎራጎረው ነው፡፡ ዝም ብዬ አስተውዬ ሳየው – በጠባችን መሐል – ሆይ፣ ሆይ፣ ሆይ፣ – በለው በለው በለው – እያለ እርስበርስ የሚያጣላን፣ የሚያጋድለን፣ የሚያጫርሰን እንጂ – የሚያስታርቀን ሰው የለንም፡፡ የሚሸመግለን ሰው የለንም፡፡ አስታራቂ የለንም፡፡ ለራሳችን ያለነው እኛው ራሳችን ነን፡፡
ለራሳችን ራሳችን አስታራቂ እንሁንና ከስሜት ወጥተን ጥቂቶችን ወደ ጥፋትና መጫረስ የሚነዱንን ዛሬውኑ በቃችሁ እንበላቸው፡፡ ብዙዎቻችን በሠላም ተስማምተን እንኑር፡፡ የሚያለያዩንን ኢምንት አጀንዳዎች አንድ ሁለት ሶስት ተብለው ተቆጥረው ይቅረቡልን፡፡ የጠባችንን ምክንያቶች ቆጥረን እንምከር፡፡ በስክነት እንመካከር፡፡ ለሆነው ሁሉ ይቅር እንባባል፡፡ ጉዳታችንን እንካካስ፡፡ እንተጋገዝ፡፡ ለነገ የሚበጀንን የፍቅር መንገድ አብረን ተመካክረን በሠላም እናብጅ፡፡
ክፋትን እንዳንደግመው መክረን ዘክረን ከልጆቻችን አርቀን እንቅበረው፡፡ በጥቂቶች የክፋት መንገድ ሄደን፣ ብዙዎች ደጎች ወገኖቻችንን አናስጨርስ፡፡
ፈጣሪ ከእኛ ጋር ይሁን፡፡ ፈጣሪ የሁሉንም የትግሬ ቤት፣ የሁሉንም የአማራ ቤት፣ በያሉበት የዓለም ጥግ ሁሉ – በፍቅር በጸጋ በበረከቱ ይጎብኝ፡፡ ፈጣሪ እንደሆንነው ሁሉ – አብሮ ወደኖረ ከአንድ ማህጸን እንደወጣ እንደ አንድ ቤተሰብ ያድርገን፡፡ ፍቅራችንን ይመልስልን፡፡ በክፉም በደጉም አይለየን፡፡ We Are the World! ይኸው ነው፡፡
Filed in: Amharic