>
5:21 pm - Sunday July 20, 8645

የወገን ሰቆቃን ለማሳወቅ ለሳውዲ ንጉስ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ...!!! ነቢዩ ሲራክ

የወገን ሰቆቃን ለማሳወቅ ለሳውዲ ንጉስ የተጻፈ ግልጽ ደብዳቤ…!!!
ነቢዩ ሲራክ

የተቃውሞ ዘመቻ ክፍል  2 
* የነገው አቢይ መልዕክት ቅምሻ‼
* ሳውዲና ህዝቧን እንዎዳቸዋለን 
* ለአእላፎች መጠጊያ ሀገራችንም ናት
* የሳውዲን ክፉ አንዎድም …
* ዛሬ ተቃውሟችን የምናሰማበት ሀቅ …
  በሳውዲ በዜጎቻችን ላይ የሚፈጸመውን ሰብአዊ መብት ረገጣ ለአለም ለማሰማት የመጀመሪያው የሆነውን ክፍል 1 ዘመቻ በስኬት እየተከወነ ይገኛል። ለሰብአዊነት ቀናኢ ለሆናችሁ ለአጋር ወዳጆቸ በመሉ አድናቆት የከበረ ምስጋናየን አቀርባለሁ  !
  ክፍል 2 ዘመቻችን ነገ ይቀጥላል። የነገው
የአቢይ መልዕክት ለሳውዲ አረቢያ መራሔ መንግስታት የምናቀርበው  ይሆናል። የመልዕክቱ ዋና አላማ የተቃውሞ መልዕክታች ምክንያቶች ማስረዳት ሲሆን በእጃቸው ላለው መፍትሔ ይተባበሩን ዘንድ መጠየቅ ይሆናል  !
የመልዕክቱ ቅምሻ …
የሳውዲን  እንዎዳታለን ፣ ክፉ አንዎድም …
ይድረስ …
ለተከበሩት የሳውዲ አረቢያ ንጉስ …
 ከሁሉ በማስቀደም የከበረ ሰላምታዬ ይድረሳችሁ። በዚህ አጋጣሚ በአጽንኦት ታውቁት ዘንድ በፈጣሪ ስም ሀቅ እውነቱን እንናገራለን ። የአለም ሙስሊማን ሁለቱ ቅዱስ ቦታዎች የመካ ሙከረማና የመዲና ሙነዎራ መገኛ የሆነችውን የሳውዲን ምድር የረገጥን ኢትዮጵያውያን የሳውዲ አረቢያን ደግ እንግዳ ተቀባይ ህዝብ ፣ ለመንግስትና  ለሰንደቅ አላማችሁ ላቅ ያለ ክብር እንዳለን ስንገልጽልዎ በኩራት ነው ። የነቢያቱን ምድር እንዎዳታለን። …
  ሀገረ ሳውዲ አረቢያ እኔን ጨምሮ ለእልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን መጠለያ ፣ ሰርተን ቤተሰብ የደገፍንባት ባለውለታ ምድር ናት። ሳውዲ መደገፊያ እንጅ መገፊያ ምድር አልነበረችምና ክፉዋን በፍጹም አንዎድም ። ለሳውዲ ካለን ታላቅ ፍቅር አክብሮት ግልጽ ክብራችን መገለጫ ለማለታችን ማሳያው ሳውዲ ለእኛ ሁለተኛ ሀገራችንም ናት ብለን ማመናችን ነው  ! …
ተቃውሟችን የምናሰማበት ሀቅ …
 የዛሬ ተቃውሟችን መልካሟ ሳውዲ እቢያ  ተለውጣብን ተቸግረን ነው። ዛሬ የሳውዲን መንግስት አምርረን የምንቃዎምበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ተልይተን በደል እየተፈጸመብን በመሆኑ ነው። ህገ ወጥ ማጥራት በተባለ ሰሞነኛ ኢ- ፍትሐዊ ዘመቻ ሰበብ የሀገር ፣ የህዝቡንና የመንግስት ህግጋትን አክባሪ ንጹሃን ዜጎች ተለይተው እየተበደሉ ነውና ከፍቶናል። …ይድረስ …
ለተከበሩት የሳውዲ አረቢያ ንጉስ ሰልማን ቢን አብድልአዚዝ እና ፣ ለቀራችሁት ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች …
ለደጉን የሳውዲ አረቢያ ህዝብ ክብር አለን ። የሙስሊማኗን ቅዱስ ሀገር መገኛ ምድር እንዎዳታለን። ሳውዲ እኔን ጨምሮ ለእልፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን መጠለያ ፣ መደገፊያ ብቻ አልነበረችም። ለሳውዲ ካለን ፍቅር አክብሮት ፣ ምስጋና መገለጫ ለእኛ ሁለተኛ ሀገራችንም ናት ብለን እናምናለን  !
የዛሬ ተቃውሟችን መልካሟ ሳውዲ እቢያ  ተለውጣብን … የምንወደው የሳውዲ መንግስት ሰሞነኛ እርምጃ የምንቃዎምበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን ተለይተን በደል እየተፈጸመብን በመሆኑ ነው። … ከፍቶናል 🙁
… ሮጠው የማያመልጡ ፣ ተናግረው የማያስከፉ ፣ ነፍሰ ጡሮች ፣ ወላድ አራሶች እየተሰቃዩ ነው። በደካማ እግራቸው እግረ ሙቅ የብረት ሰንሰለት ገብቶበታል።  ውሎ አዳራቸው የጨለማ ሆኖባቸወ  ልባችን ሰብሮት ከፍቶናል። የተቃዎምናችሁ አቅመ ደካማ ለጋ ህጻናት ፣ ሴቶች ፣ ታማሚ ዜጎቻችን ምግብ ፣ የሚጠጣ ንጹህ ውሃ ፣ የንጽህና ቁሳቁስ ሳይቀር ተነፍገዋልና ነው። ከረሀቡና ውሃ ጥሙ ጋር በበጋው ሀሩር ሙቀት እተሰቃዩ  ነው። ይህን ሀቅ ይዘን የመንግስትን ሰሞነኛ እርምጃ ስንቃዎም በዜጎች ላይ የተጭናቸው የበደል ቀንበር በአስቸኳይ ይነሳ ዘንድ ለመጠየቅ ነው  ።
… በሙስሊማን መልዕክተኛ ተብለው የሚታመኑት  ነቢዩ መሐመድ ( ሰአወ) ሱሃባዎቻቸውን የላኩባት ኢትዮጵያውያን ዜጎች በሳውዲን መንግስት ግፍ እና በደል ደርሶበ ደርሶባቸዋል። ኢትዮጵያ ልጆቿን ትፈልጋቸዋለችና መንግስታችሁ ለዜጎቻችን ጊዜ ሰጥቶ በጉልበት በላባቸው ሰርተው ያፈሩትን ሀብት ንብረት ወደ ሀገራቸው በክብር እንዲመለሱ ፍቃዳችሁ ይሆን ዘንድ በአክብሮት እንማጸናችኋለን  ‼
… እንደ ፈጣሪ ደቃድ ሙሉ መልዕክቱ በነገው ክፍል 2 ፍትህ ጥየቃ ዘመቻ  ይቀጥላል…
  ክፍል 2 ዘመቻ ሙሉ መልዕክት በአማርኛ ፣ በእንግሊዝኛና ብሎም በአረብኛ ቋንቋ  በጽሁፍና በተለይም መልዕክቱ ለባለቤቶቹ ይደርስ ዘንድ በድምጽ ተዘጋጅቶ በአረብኛ ቋንቋ የሚቀርብ ይሆናል።
  ለሰብእና ቀናኢ የሆናችሁ ወዳጆቸ እና ሰብአዊነት የሚሰማችሁ ወገኖቸ መረጃውን አካፍሉ ። ስለ መልካም ትብብራችሁ በተገፊዎች ስም ምስጋናዬ ይድረሳችሁ ‼
 ከሰላምታ ጋር 
ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓም
Filed in: Amharic