>

ብቸኛው አማራጭ ድርድርና ውይይት‼  የዛሬዋ ፍትህ መጽሔት ርዕስ አንቀፅ‼

ብቸኛው አማራጭ ድርድርና ውይይት‼ 
የዛሬዋ ፍትህ መጽሔት ርዕስ አንቀፅ‼

የዓለም የጦርነቶች ታሪክም ሆነ ወታደራዊ ሳይንስ የሚነግሩን፣ ለጦርነት ዝግጅት የሚደረገው በሰላሙ ዘመን ሲሆን፤ ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ደግሞ ዝግጅቱ የሚጀመረው በጦርነቱ ወቅት መሆኑን ነው። በዚህ ላይ፣ ሁሉም ጦርነቶች የመጨረሻ መቋጪያ የሚያገኙት ደም-አፋሳሽ ውጊያ ከተደረገ በኋላ በሚኖር ድርድር እና ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑ የተረጋገጠ ሃቅ ነው። በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሁኔታም ከዚህ የተለየ እልባት ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ነው።
የፌደራሉ መንግሥት፣ መከላከያ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል አስወጥቶ፣ የተናጥል ተኩስ አቁም ማድረጉን ካወጀ በኋላ፤ የሕወሓታ ታጣቂዎች መጠነ-ሰፊ ውጊያ የከፈቱት ይህን ጨዋታ ከግምት በመክተት እንደሆነ ይታመናል። ምዕራባውያኑ ችግሩ በድርድር እንዲፈታ ከፍ ያለ ግፊት ማድረግ መጀመራቸው ደግሞ፣ የውይይቱ ጊዜ እየተቃረበ ለመሆኑ ጠቋሚ እድርገው እንዲወስዱት የበለጠ ሳይገፋቸው አይቀርም። ከእነኚህ ኹነቶች አኳያም፣ የተወሰኑ ድሎችን ማግኘቱ በድርድሩ ላይ የተሻለ ጉልበት እንደሚሰጥ አስልተው የከፈቱት ዘመቻ መሆኑን ለመረዳት ውስብስብ አይደለም። ሕወሓት በዲፕሎማሲውም ሆነ በሴራ ፖለቲካው፣ ከፌደራል መንግሥቱ የበለጠ አፈጻጸም ማሳየቱን ያለፉት ስምንት ወራት በበቂ ማስረገጣቸውን ልብ ይሏል።
የሆነው ሆኖ፣ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ችግሮችን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሁሉንም አሸናፊ የሚያርግ መንገድ ነው። በኢትዮጵያ በዚህ ዐውድ ሊጠቀሱ የሚችሉት ዋንኛና ስር-ሰደድ ፖለቲካዊ ችግሮች ደግሞ ሁለት ናቸው። የማንነት ጥያቄ እና የወሰን አከላለል ጉዳይ። እነዚህ ችግሮች በትግራይ እና ዐማራ መሃል ብቻ ሳይሆን፤ በሁሉም ክልሎች ተንሰራፍተው የሚታዩ ለመሆኑ በደም-ግብር ጭምር የተገለጠ እውነታ ከሆነ ሰንብቷል። በተለይ፣ የድንበር እና የአከላል ጉዳዮች ከላይ ወደታች ከመጫናቸው በተጨማሪ፤ ሁሉን አካታች የነበሩ አለመሆኑ ለግጭቶቹ ዋነኛ መነሾ ሆኗል።
“ፍትሕ መጽሔት”፣ ሁሉም ክልሎች በውስጣቸው ላለ የማንነት ጥያቄም ሆነ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ለተፈጠረባቸው የወሰን አከላለል አለመግባባት፣ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመደራደር ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ትመክራለች። በርግጥም፣ ሁሉም ኃይሎች ለሰላም ውይይት ቅድሚያ ሰጥተውና በሆደ-ሰፊነት ከመደራደር በቀር፤ አማራጭ እንደሌለ የምራቸውን ሊያምኑ ይገባል ።
ይህ ዐይነቱ አካሄድ፣ በጦርነት ወይም በፍጥጫ ላይ ካሉት በተጨማሪ፤ የታሰሩትን መልቀቅ እና በውጪ አገር ያሉትንም እንዲገቡ መፍቀድን ሊያካትት እንደሚገባም ታምናለች።
መጽሔታችን የበለጠ አጽንኦት የምትሰጠው፣ የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የዐማራ ክልል አስተዳደሮች፣ ከጦርነቱ በኋላ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እንዴት በጋራና በሰላም መኖር እንደሚቻል እና ኢትዮጵያን ከእነ ግዛት አንድነቷ ስለማስቀጠል በጥሞና መወያየትና ማሰብ እንዳለባቸው ለማስታወስ ትወዳለች።
በሌላ በኩል፣ ጦርነቱ ከተነሳ ጀምሮ ምዕራባውያኑ፣ በተለይ የአሜሪካ መንግሥት የሚያራምደው አቋም፣ የተወሰኑ የሕወሓት አመራሮችን ሥልጣን እና ጥቅም ከማስከበር ያለፈ፤ ለትግራይ ሕዝብ ፍፁም ጠቀሜታ የሌለው መሆኑ ገሃድ መውጣቱ እሙን ነው። ለዚህ አንድ ማሳያ የሚሆነው፣ የተፈጠረውን ነገርም ሆነ የተሰጣቸውን ግዳጅ ቅንጣት ያህል መረዳት የማይችሉ ህጻናቶችን፣ ክላሽንኮቭ አሸክመው ለጦርነት ሲማግዱ፣ ለማስመሰል ያህል እንኳ ድርጊቱ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሰው መውቀስ አለመፈለጋቸው ነው። በርግጥ፣ ነገሩን ለማንሳት እንጂ፣ እነርሱ ከተጋነነው ካፒታሊስታዊ ስግብግብነታቸው በዘለለ፤ ስለ ሰው ልጅ ግድ ኖሯቸው አለማወቁን የረገጡት መሬት ሁሉ ህያው ምስክር ነው። የእነዚህ ጨቅላ ህጻናት ጉዳይም ከቶም ቢሆን ሊያሳስባቸው እንደማይችል ይታወቃል።
በዚህ ላይ አሁን የጀመሩት ጨዋታ፣ ትግራይን ማስገንጠል እንደ አማራጭ ይዘው እያሴሩ እንደሆነ ይጠቁማል። መቼም እንኳን ለእነሱ፣ ለሌላውም ቢሆን፣ ትግራይ ‘ኤክስተርናል ቦርደር’ እንደሌላት አይጠፋውም። ‘እገሌ ከዚህ ይወጣ፣ እግሌ እዚህ ይግባ’ ዐይነቱ መግለጫቸውም፣ ክልሉን የማስገንጠል ድብቅ ሴራቸውን ዐደባባይ ያወጣ ነው።
ይህም ሆኖ፣ ሁሉም ወገን በጦርነት ከእልቂት በቀር፤ ትርፍ ማግኘት እንደማይቻል ተገንዝቦ፣ ለሰላማዊ ውይይትና ድርድር ራሱን ማዘጋጀት ብቸኛው መፍሄ እንደሆነ ሊረዳ ይገባል። የዐውደ ውጊያ ድል ጊዜያዊ እንጂ፣ ዘላቂ መፍሄ አምጥቶ አያውቅም። ይህ ዐይነቱ መንገድ፣ በአንድ አገር ልጆች ላይ ቀርቶ፤ በተጎራባቾቹ ኢትዮጵያ እና ኤርትራም ያሰፈነው ሰላም እንደሌለ ማስታወሱ ይመከራል።
አሁንም ደግመን የምናስተላልፈው ጥሪ፣ ሁሉም ወገን ለማይቀረው ሰጥቶ መቀበል ድልድር ራሱን ማዘጋጀት እና የቤት ሥራውን ከወዲሁ እንዲጨርስ ነው።
Filed in: Amharic