>

ከህወሀት መንደር ሰሚ ባይኖርም እንኳ   ተግሳጽ ወ-ምክር ልንለግስ ወደድን...!!! (አሳፍ ሀይሉ)

ከህወሀት መንደር ሰሚ ባይኖርም እንኳ   ተግሳጽ ወ-ምክር ልንለግስ ወደድን…!!!

አሳፍ ሀይሉ

 

*..    አይ ግዜ መኖር ደጉ ብዙ ያሳያል። ሀቂቃ እኮ ነው፥ ለሰው ጉድጓድ ስትቆፍር አታርቀው ማን እንደሚገባበት አይታወቅም ይባል የለ። ሀገር ምድሩ በመዳፋችሁ በነበረ ግዜ ልዩ ኃይል በማለት በየክልሉ ስታዋቅሩ ዋናው ዓላማው እናንተ በፈለጋችሁት ሰዓት እርስ በርስ እንዲባላ እግረ-መንገዱንም ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅድ ነበራችሁ ነገር ግን ይሄ ቅኔ የሆነ ሕዝብ ዛሬ ልዩ ሀይሉን ዳር እስከዳር አስተባብሮ እናንተኑ ሊውጣችሁ በአንድነት ቆሟል… !!!
 
እኔ በበኩሌ ህወሃቶች (እና ከጎናቸው የተሰለፈው የትግራይ ህዝብ) ይሄን የ«መሬት እናስመልሳለን» ጦርነት አቁመው፣ ከጎናቸው የቀረበላቸውን ዓለማቀፍ እገዛ በአግባቡ ለሠላም፣ ለተሻለ ለውጥ፣ እና ከኦሮሙማው መንግሥትና ከአማራ ክልል ጋር ወደ ጠረጴዛ ውይይት ወደሚያመራ የጋራ የመፍትሄ ውይይት ለመብቃት አተኩረው ቢሰሩ ለሁሉም የሚበጅ ይመስለኛል! 
 
በአንዱ አቅጣጫ መሬት አስመልሳለሁ ሲባል፣ በሁሉም አቅጣጫ በትግራይ ህዝብ ላይ ከሚከፈትበት ጥቃት መትረፍ የማይታሰብ ነው! አሁን ያለውን status quo ካላከበርክ፣ ሌላውም አያከብረውም፡፡ አንተ ራያ ላይ ግንባር ስትከፍት ሌላው በእልፍ አቅጣጫ የእኔ ነው ብለህ በያዝከው መሬት ላይ መቶ ኪሎሜትሮች ገብቶ ይጠብቅሃል! እና ይሄ የማያቋርጥ ጦርነትን የመጥራትና የመውደድ ነገር አደብ ቢሰጠው! ልክ ቢኖረው! ለትግራይም ሆነ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም የሚበጅ ይመስለኛል! 
 
የትግራይ ህዝብ ብዙ የወደመ የልማት አውታሮችን ታቅፎ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ ከመሠረታዊ መንግሥታዊ አገልግሎቶችና አቅርቦቶች ውጪ ሆኗል፡፡ አስተማማኝ የምግብ ዋስትና የለውም፡፡ ነገና ከነገ ወዲያ በቂ ስንቅና ትጥቅም አይኖርም፡፡ በዚያ ላይ ከወገንህ ጋር ነው የምትገዳደለው፡፡ ዛሬ በከፋኸው ልክ – ነገ ያቺን መስመር በፍቅር አታቆራርጣትም፡፡ በዚያው ህዝብ መሐል፣ እና ከዚያው ህዝብ ጋር ተጎራብተህ ነው የምትኖረው፡፡ ክፋትን ማብዛት፣ በራስ ላይ በቀልንና ቁጣን ማብዛት ይሆናል፡፡ አሁንን ብቻ ሳይሆን ነገንም ማሰብ መልካም ነው!
 
ስለሆነም የህወሃት የአሁን አመራሮች – ለህዝቡ በእንቅርት ላይ ጆሮ-ደግፍ ባያተርፉለት – እና የሚጠይቁትን በሠላምና በድርድር ቢጠይቁ – ወደ እነርሱ ያዘነበለላቸውን ዓለማቀፍ ሀይል ጫና በስልትና በጥበብ ይገባናል ለሚሉት ግብ ለመጠቀም ተግተው ቢሰሩ – ከጦርነት ይልቅ የሠላምን መንገድ አጥብቀው የሙጥኝ ቢሉ – መልካምም አዋጪም ይመስለኛል! አለዚያ የህወሃት የ‹‹መሬቴን አስመልሳለሁ!›› ሁለተኛ ዙር ጦርነት መዘዙ ብዙ ነው! 
 
ነገሮች የተለዋወጡ ዕለት – ይሄ መዘዝ – በተከዜና ኮረም አውደ-ውጊያዎች ብቻ የሚቆም አይሆንም! አንድ ህዝብ ባለው አቅም የሚችለውና የማይችለውም ልክ አለው! ይሄ ሊታወቅ ይገባል! ብዙ ሲከርሩና ሲያከሩ፣ መበጠስ ነው ትርፉ፡፡ የትግራይ ህዝብ የመጣበትን ወራሪ አሳፍሮ መልሷል! አንገቱን ቀና አድርጓል! ለጊዜው ተመስገን ብሎ ህመምን ማስታገስ ላይ ማተኮር የሚሻል መሰለኝ! አለዚያ መዘዙ የከፋ ነው! አተርፍ ባይ አጉዳይ መሆንም አለ! ለሠላም እና ለሠላም ቅድሚያ ቢሰጥ ለሁሉም ይበጃል! ይኸው ነው!
 
እናት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በፍቅር ትኑር!
Filed in: Amharic