>

ጓድ መንግሥቱ አንድ የኮንዶሚኒየም ህንፃ ከነነፍሱ መጥፋቱን በሰሙባት ሰዓት! (አሳፍ ሀይሉ)

ጓድ መንግሥቱ አንድ የኮንዶሚኒየም ህንፃ ከነነፍሱ መጥፋቱን በሰሙባት ሰዓት!
አሳፍ ሀይሉ

— በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ አጭር ልብ ወለድ
ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሰሞኑ በረባ ባልረባው ሁሉ ይበሳጫሉ፡፡ ቁጣቸው አይሏል፡፡ በመሆኑም ያበሳጫቸዋል ተብለው የሚገመቱ ሰሞናዊ ሪፖርቶች ሊነገራቸው አመቺ ጊዜ እየተጠበቀ ነው፡፡ ከእነዚህ ሪፖርቶች አንዱ እዚሁ መዲናይቱ ውስጥ አንድ የኮንዶሚኒየም ህንፃ ከነነፍሱ ተወስዶ የገባበት እንዳልታወቀ የሚጠቅሰው ሪፖርት ነው፡፡ እስከዛሬ ተደብቋቸው ከርሞ ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬ ጓድ መንግሥቱ ማልደው ቁርስ እየበሉ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ውባንቺ ቢሻው ጋር በተቀመጡበት የስርቆት ፈገግታ ሲለዋወጡ በደህንነቱ ቢሮ ለግላቸው አብሳይ ሆኖ የተመደበው ሼፍ ተመለከታቸው፡፡
የጓድ መንግሥቱ የሥርቆት ፈገግታ ሪፖርት ለመረጃ አገልግሎቱ ተጠሪ ሲደርሰው፣ ዛሬ ደስ ባላቸው ሰዓት ሪፖርቱ ይነገራቸው ብሎ ወሰነ፡፡ እና የመዝናናት ስሜታቸው ሳይወርድ እንደምንም ተለሣልሶ ተነገራቸው፡፡ የኮንዶሚኒየሙ አንድ ብሎክ (ሕንጻ) ከሣይቱ ላይ ድራሹ ስለመጥፋቱ ዜና!
ኮሎኔሉ ይህን አስደንጋጭ ዜና ሲሰሙ ገና ከቁርሳቸው ላይ አልተነሱም፡፡ አይናቸውን እያጉረጠረጡ የጎረሱት ቃርያ የበዛበት ‹‹ኩንስ ፓኛ›› ከጉሮሯቸው አልወርድ ብሎ እየተናነቃቸው ሰሙት፡፡ ስቅ ሊላቸው ሁሉ ነበር፡፡ አጠገባቸው የተቀመጠላቸውን ውሃ አንስተው በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ አድርገው ጠጡ፡፡ አላወላወሉም፡፡ ሌላውን የተቀረውን ሪፖርትም አልሰሙም፡፡ ‹‹አሁኑኑ! አሁኑኑ ውሰዱኝ ወደ ሣይቱ!›› ብለው በቁጣ ተስፈንጥረው ተነሱ፡፡
በዛሬው ዕለት ሊሄዱበት የተያዘላቸውን ጉዳይ ትተው ወደ ኮንዶሚኒየም ሳይቱ በመሄድ ቆረጡ፡፡ ጓድ መንግሥቱ አንዴ ከወሰኑ ወሰኑ ነው፡፡ ማንም ሀሳባቸውን አያስቀይራቸውም፡፡ የደህንነት ተጠሪያቸው ትዕዛዙን ተቀብሎ አስቸኳይ ዝግጅቶችን ለማድረግ ተሰናብቷቸው ሲወጣ ጊዜ አላባከኑም፡፡ በቀጥታ ወደመኝታ ክፍላቸው ተንደርድረው ገቡ፡፡ እና የሚሊቴሪ ፋቲጋቸውንና መለዮአቸውን አወለቁና ወለሉ ላይ ጣሉት፡፡ በቅያሪው ፊትለፊታቸው በቁም ሳጥን ያዩትን የሲቪል ልብስ ጎትተው አወጡ፡፡
እንደ ወተት የነጣ የክት ሱሪ፣ በጉርድ የከረንቦላ ሸሚዝ አጥልቀው፣ ያንኑ የሚሊቴሪ ከስክስ ተጫምተው በችኮላ ተነሱ፡፡ በትረ-መንግሥታቸውን ሊይዙ ካነሱት በኋላ መልሰው ተዉት፡፡ በጭቁኑ ሕዝብ መሐል የንጉሣዊ ምልክቶችን መያዝ – በሕዝቡ ዘንድ የመደብ መከዳት ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል – የሚል እምነት አላቸው፡፡ እና ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ የሥራ ጉብኝቶች ሲንቀሳቀሱ ካልሆነ በቀር በትረ-መንግሥታቸውን ይዘው አይንቀሳቀሱም፡፡
የመንግሥቱ ልዩ ተጠሪዎችና አጃቢዎች ትዕዛዙ ደርሷቸው በተጠንቀቅ ቆመዋል፡፡ የሕዝባዊ ኑሮ እድገት አስተባባሪዎች በበኩላቸው ጠፋ የተባለው ኮንዶሚኒየም በሚገኝበት መንደር ያሉ ነዋሪዎችን ሁሉ ከያሉበት አድነው በፍጥነት ከጓድ መንግሥቱ ጋር ለስብሰባ የሚቀመጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የቻሉትን ያህል ተሯሯጡ፡፡ በተለይ ደግሞ የኮንዶሚኒየሙ መኖሪያ ቤት ሊሰጣቸው ሲገባ፣ በመጥፋቱ የታለፉት ነዋሪዎችም በሥፍራው እንዲገኙ ከቀበሌና ከከፍተኛ ጋር በፍጥነት ተደዋውለው በብርሃን ፍጥነት ማድረግ የተቻለው ሁሉ ተደርጎ ተመቻቸ፡፡
ጓድ መንግሥቱ ስኩዌር ጉርድ ሸሚዛቸውን ከነጭ ሱሪና ከስክስ ጫማቸው ጋር ለብሰው አኩርፈው ቁርስ በበሉበት ጠረጴዛ ለይ መልሰው ቁጭ ብለዋል፡፡ ምንም ቃል አይናገሩም፡፡ በዝምታ ማዶ ማዶውን እያዩ የሚፈላውን ጉድ እያሰቡ ይመስላል፡፡ በመጨረሻ የመንጌ መኪኖች ለጉዞ ተነሱ፡፡ እና በደቂቃዎች ውስጥ ብርር ብለው ወደ ተባለው ሥፍራ ደረሱ፡፡ መንጌ ከመኪናቸው ወርደው ወደ ኮንዶሚኒየም መንደሩ ሲገቡ በቀበሌና ከፍተኛዎች ቅስቀሳና ማስፈራሪያ የወጣው ነዋሪ ደማቅ አቀባበል አደረገላቸው፡፡
በቀጥታ ኮንዶሚኒየሙ ተነቅሎ ተፋ ወደተባለበት ሥፍራ ውሰዱኝ ባሉት መሰረት፣ ጓድ መንግሥቱን ወስደው አሳዩዋቸው፡፡ ባዶውን ያፈጠጠውን ረባዳ ሥፍራ፡፡ በጠፋው ኮንዶ ሜዳ ላይ፡- ‹‹ኮንዶሚኒየሙ በአንድ ወቅት እዚህ ቦታ ቆሞ ነበር!›› የሚል አጭር መግለጫ የያዘ የግንድ ምሰሶ ተተክሏል፡፡
ሁሉም በሥፍራው ያሉት ድንጋጤ ውጧቸዋል፡፡ መንጌን ከሚያስጎበኛቸው ሰው በቀር ማንም ቃል ትንፍሽ አይልም፡፡ ጓድ መንግሥቱ ነገሩን በገዛ ዓይናቸው ካዩ፣ እና የሆነውን አምነው ከተቀበሉ በኋላ፣ ሰዉን እዚያው በጅምር በቀሩ ግንባታዎች መሐል አቁመው በዙሪያቸው ላሉ ረዳቶቻቸው የትዕዛዞች መዓት ማዥጎድጎድ ጀመሩ፡፡ ‹‹በአስቸኳይ ከነነፍሱ የተሰወረው ኮንዶ ታስሶ በተገኘበት እንዲያዝ!››፡፡ ኮንዶሚኒየም ሰው አይደለም፡፡ አስሰህ የምትይዘው፡፡ ግን በዚህ ቅጽበት መጠየቅም ሆነ ማንገራገር አትችልም፡፡ እሺ ማለት ነው፡፡ ትዕዛዛቱ ቀጠሉ፡፡
‹‹ኮንዶውን ይዞ የተሰወረው መሃንዲስ… በመላ ሀገሪቱ ታድኖ በተገኘበት… እንዲያዝ›› አሉ አስከትለው፡፡ በእፎይታ ተያዩ ረዳቶቻቸው፡፡ ምክንያቱም ሰው ከሆነ ተመስጌን ነው፡፡ መያዙ አይቀርም፡፡ ለአፍታ አሰብ ካደረጉ በኋላ ትዕዛዛቸውን በማረም ‹‹ማለቴ.. በተገኘበት አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድበት…!›› ብለው ወደሚቀጥለው ትዕዛዝ ተሸጋገሩ፡፡ ‹‹ኮንዶው ሲሰለብ ዝም ብለው የተመለከቱት ካቦዎችስ? አሁን የት ናቸው? እያንዳንዳቸው ተለቅመው… በአፋጣኝ ወደ ማዕከላዊ ምርመራ ይላኩና ጥብቅ ምርመራ እንዲደረግባቸው!››፡፡ ረዳቶቻቸው ጭንቅላታቸውን በአዎንታ እያወዛወዙ አጎንብሰው ትዕዛዛቱን በማስታወሻቸው ይሞነጭራሉ፡፡
በመጨረሻም መንጌ በረጋ መንፈስ ዘወር ብለው ወደ ከበቧቸው ካድሬዎች እየተመለከቱ ‹‹የቀበሌውና ከፍተኛው አመራር የኮንዶውን መጥፋት አስመልክቶ ስላደረጉት ርብርብና በጉዳዩ ላይ ስለያዙት የማይቀለበስ አቋም አሁኑኑ ዝርዝር ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ…!›፣ ሌሎችንም ብዙ ተዕዛዞች አዥጎደጎዱ፡፡ ሲያበቁ… እዚያው የግድግዳ ፍራሾቹ መሐል በመሬቱ ላይ ቁጢጥ አሉ፡፡ እና አጎንብሰው መሬቱን በሌባ ጣታቸው መጫር ያዙ፡፡ ጓድ መንግሥቱ ሲቆዝሙ እንዲህ ያደርጋቸዋል፡፡ እየቆዘሙ ነው፡፡ ትዕዛዙን እየተቀበለ የሄደው ሄደ፡፡ የቀረው በዝምታ ተውጦ የሚሆነውን ይጠባበቃል፡፡
በመጨረሻ መንጌ እዚያው ባጎነበሱበት በኮንዶሚኒየሙ ሣይት ላይ ያገኟቸውን የግንባታ ድንጋይ ስርብባሪዎች… በግራ እጃቸው እፍስ አርገው… እንባ እየተናነቃቸው… ሊያስጎበኛቸው ወደ ወሰዳቸው የህዝባዊ ኑሮ እድገት ተጠሪ እና በሥፍራው ወደ ተገኙት የኢሠፓአኮ አባላት.. እንዲሁም የህዝባዊ ሚሊሺያ አስተባባሪዎችና የቀበሌው ሊቃነ መናብርት ፊታቸውን ቀና አድርገው… ሲቃና እልህ እየተናነቃቸው እንዲህ አሉ…፡-
‹‹አሁን ይህን ስብርባሪ ድንጋይ አጥቶ.. በየመንገዱ ዳር ላስቲክ እየቀጣጠለ .. ሐሩሩንና ቁሩን ችሎ ከሚኖር… ከዚህ ምስኪን ሕዝብ ላይ… የኮንዶ ህንፃን ያህል ነገር ይሠረቃል? ይሠረቃል ወይ? ሕዝቡ ተዘርፎ ተዘርፎ… በመጨረሻ.. እንትኑ (ከይቅርታ ጋር ‹‹ቆለጡ!›› ነው ያሉት) እስኪዘረፍ ነው እንዴ የምትጠብቁት ጓዶች? ንገሩኝ እንጂ?! አሁን የማን ጥፋት ነው ልትሉ ነው ይሄን?! የእናንተ የራሳችሁ ጥፋት አይደለም? የማንን ጎፈሬ ስታበጥሩ ነው አንድ የነዋሪዎች ህንጻ ተነቅሎ የበረረው? እናንተ ራሳችሁ አይደላችሁም እጃችሁን በሶ ጨብጣችሁ.. ‹‹እንካ  ይኸውልህ!›› ብላችሁ ያስረከባችሁት? በሉ እንጂ…! እናንተ አይደላችሁም ወይ.. ‹‹መኖሪያ ቤት ሥሩለትና ድሃውን አኑሩበት ብለን – ተበድረን ተለቅተን የሰጠናችሁን የልመና ገንዘብ… አዲስ ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ሠራን ብላችሁ ስታበቁ፣ ከነነፍሱ እንካ ውሰድ እንዳሻህ ብላችሁ ለህንጻ ሰላቢ ያስረከባችሁት? ተናገሩ እንጂ? እናንተ አይደላችሁም ወይ?!››
ጓድ መንግሥቱ እያንዳንዷን ቃል ሲናገሩ በኃይለቃል ነው፡፡ አመልካች ጣታቸውን በፊታቸው በቆሙት ሁሉ ላይ እየሰበቁ፡፡ አኳኋናቸው ሁሉ ያስፈራል፡፡ የኒውክሊየር ቁልፍ የጠፋባቸውን ያህል ነው በቁጣ የነደዱት፡፡ ሁሉም በአንድ ድምጽ ተደምረው፡— ‹‹አዎ እኛ ነን!›› አሉ፡፡
‹‹እና ጥፋተኛው ማን ነው.. ማነው ነው የምትሉት?!?? ራሳችሁ አይደላችሁም?››
‹‹አዎ ነን..! ራሳችን ነን!››
ሰዉ ሲያምንላቸው መንጌ አሁን ገና በፊታቸው ላይ የእርካታ ስሜት ተነበበባቸው፡፡ እኚህን ሰው ከምንም በላይ አቅላቸውን የሚያስታቸው ባለቤት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ የፈለገው ነገር ተሠራ ቢባል.. አንድ ለድርጊቱ ጥፋተኛ የሚሆን ሰው ይፈልጋሉ፡፡ እና ጥፋቱ የሚላከክበት ሰው ከተገኘ ደስተኛ ናቸው፡፡ ለተፈጠረ ጥፋት ተጠያቂ የሚሆን ሰው ከሌለ ግን፣ ባገኙት ላይ ነው ብስጭታቸውን የሚያስወነጭፉት፡፡
በዚያም የተነሳ.. ጥፋተኛው ያልተገኘለት ጉዳይ ሲገጥም በእርሳቸው አጠገብ መገኘት የሚፈልግ የለም፡፡ ነገሩን መናገርም ጭምር፡፡ ጓድ መንግሥቱ በንዴት እዚያው በዚያው ምን ጉድ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ከአንድዬ ፈጣሪ በቀር የሚያውቅ ማንም የለምና፡፡ አሁን ግን መንጌ ቢያንስ ትንሽ እርጋታ ተላበሰዋል፡፡ እና ሰላም ነው ማለት ነው፡፡ ብለው ደምድመዋል የቅርቦቻቸው፡፡ በመጨረሻ መንጌ የጨበጡትን ስብርባሪ ቁልቁል በትነው እጃቸውን እያራገፉ ብድግ አሉ፡፡ ሞገሳቸው እና ዓይናቸው እና ከንፈራቸው… ሁለመናቸው – እንደ ጥቁር አንበሣ ያስፈራል፡፡ እርሳቸው ግን የሰዉ ጥፋተኝነቱን ማመን አርግቧቸው ስለነበር የሚያስፈሩትን ያህል ብዙም የሚያስፈራራ ቃል አልወጣቸውም፡-
‹‹በጣም ጥሩ! አሁን የናንተን መርበትበት ማየት አንሻም፡፡ መበርታት ነው መፍትሄው፡፡ ሥራችሁን በርትታችሁ ሥሩ! የተሰጣችሁን ግዳጅ በኃላፊነት እስከተወጣችሁ ድረስ.. ሀገራችሁ በቻለችው ሁሉ ከጎናችሁ ነች…! ደሞ የምመክራችሁ ነገር.. የጠፋ ጠፋ ነው! በቃ! ስለጠፋ ኮንዶሚኒየም አትጨነቁ! ምንድነው ኮንዶሚኒየም?! ‹ኢት ኢዝ ነቲንግ› እኮ! አልማዝ አይወጣበት ኮንዶሚኒየም..! ወይ ወርቅ አይቆፈርበት… ! ጤፍ አይመረትበት… ወይ ነዳጅ አይወጣበት..?! በቃ ነቲንግ ነው ኮንዶ..! ነቲንግ!
‹‹የሸክላ ስብርባሪ ነው! እንደዚህ ጨብጬ እንደበተንኩት ስብርባሪ…!  ተሰባሪ ድንጋይ! እና.. ብናኝ…! በቃ ይሂድ ወደፈለገበት ጦሱን ይዞ! እናንተ የጠፋ ሊያስጨንቃችሁ አይገባም!… ብቻ የናት ሀገራችሁን ነገር አጥብቃችሁ ያዙ! የጠፋውን ለኛ ተዉት፡፡ እኛ ድንጋይና ሲሚንቶ ይዞ የተሰወረውን.. ሰላቢም ይሁን መጋኛ (ፈገግ አሉ መንጌ ይህን ሲናገሩ፣ ሰዉም አብሮ ፈገግ አለ) የገባበት ገብተን ዋጋውን እንሰጠዋለን…! እስቲ የናቱ ሆድ ገብቶ ይደበቀን እንደሆን እናየዋለን!?!››
ካሉ በኋላ ለአፍታ ጉሮሯቸውን ጠራርገው ቀጠሉ ንግግራቸውን፡-
‹‹አሁን በጠፋው ምትክ .. ለእያንዳንዳችሁ የኪራይ ቤት.. ወይም የቁጠባ ቤት.. ወይም እንዳቅማችሁ የቀበሌ ቤት ይፈለግላችኋል..! ተፈልጎ ሊገኝላችሁ ላልቻላችሁት ግን… ለምሣሌ (አሉ ፊት ለፊታቸው ቆሞ የተስፋ ንግግራቸውን በንቃት የሚከታተለውን ልጅእግር ወጣት እየተመለከቱ) አንተ.. ወገብህን ይዘህ የቆምከው ለምሳሌ! አሁን ላንተም ሆነ አንተን ለመሰሉት ወጣቶች ሁሉ… በጠፋው ምትክ ለመጠለያ የሚሆናችሁ ምትክ ቤት ከጠፋ.. ምንም ማድረግ አንችልም..! እናዝናለን! እንግዲህ ወይ ቤት ልጅ አይደለ.. አምጠን አንወልደው ነገር – ምን እናድርግ?! እናንተ እናንተ – ያው የምታድሩበት ቤት ከታጣ… ሁላችሁም… ለናት ሀገራችሁ እንድትዘምቱ ይደረጋል! ያ ደሞ ክፋት አይምሰላችሁ፣ ክብር ነው…!
‹‹እዚህ ህንፃ ላይ ተዘፍዝፋችሁ ምንድነው ስታደርጉ የቆያችሁት? ስንት እኩዮቻችሁ ከጠላት ጋር አንገት ላንገት በሚተናነቁበት በአሁኑ ሰዓት… እንቁላል ታቅፋችኋል ከዚህ የመኖሪያ ካምፕ ገብታችሁ ንቅንቅ የማትሉት?! ይሄ ማቆም አለበት! ጠላቶቻችን.. ከትንሽ እስከትልቅ ተነቃንቀው… የ6 ዓመት ልጅ ሳይቀር እያዘመቱ ቀንና ሌሊት ሲተገትጉን… እናንተ… እዚህ ኮንዶሚኒየም ላይ ተኝታችሁ ‹‹ኮንዶ… ጠፋ አልጠፋ›› እያላችሁ እርስ በርስ ትተጋተጋላችሁ..፡፡
‹‹ለመሆኑ እናንተ ግን ምን ዓይነት ትውልዶች ናችሁ??! ለእናት ሃገራችሁ ተብሎ የተከሰከሰው የአያቶቻችሁ አጥንት.. ትንሽ ..! ትንሽ እንኳ! አይጎረብጣችሁም?.. ማለቴ አጥንታቸው አይወጋችሁም?!! ሀገራችሁ እዚያ ነፍስ-ግቢ-ነፍስ-ውጪ ላይ ነች… እናንተ እዚህ ኮንዶሚኒየም መኝታ ቤት ነፍስ-ግቢ-ነፍስ-ውጪ ላይ ናችሁ! እንግዲህ ..ወይ ታሪክ ዋሽቷል… ወይ ወኔያችሁን… ሸጣችሁታል… ማለቴ ሸንታችሁታል!!… መራሩ እውነታ እንደዚያ ነው የሚመስለኝ ጓዶች! እንደዚያ አይደለም?!!!? አይደለም.. ነው??!!››
አሁን የተፈራው ደረሰ፡፡ ታግሰው ቆይተው ቆይተው… ድንገት ተቆጡ ሊቀመንበሩ!! ሁሉም ባንድ ድምፅ፡- ‹‹ነው!›› አሉ፡፡ መንጌ ይህን ሲሰሙ ወዲያው ደግሞ መልሰው የተረጋጉ መሰሉ፡፡ ወይም ይናደዱ ወይም ይስከኑ የማለይበት የስሜት ሁኔታ ላይ ደረሱ፡-
‹‹እሺ ሁላችሁም በሠላም ዋሉ! አደራ ኢትዮጵያን ጠብቋት! ደሞ አንተኛው.. ላለመዝመት ጣትህን አስቆርጠህ ጠብቀኝ አሉህ! እኔን እጎዳለሁ ብለህ… ግብታዊ ሆነህ ራስህን አትጉዳ…!! አሁን እንደ ድሮው ጣት የለህም፣ ጥርስ የለህም፣ እያልን የምንተውበት ታሪካዊ ነባራዊ ሁኔታ ላይ አይደለም የምንገኘው! ጦርነቱ እስከፈቀደ ድረስ… ማንኛዋንም የሀገር ሃብት… ማንኛውንም አካል… ለጦርነቱ እናውላለን… !! ያንተ ጣት ቢቆረጥም ባይቆረጥም… መዝመት አይቀርልህም፡፡ ጣትህን ካጣነው… ወደ ኦርቶቲክስ ፕሮስቴቲክስ የሰውነት አካል ማምረቻ ማዕከል ትላካለህ… እና በልክህ ጣት እንዲሠራልህ ተደርጎ… ያቺኑ አርቴፊሻል ጣት አጥልቀህ… ወደ ጦር ሜዳ ትዘምታታለህ… !!!
‹‹ጥርስ የለኝም ብሎም መቅረት የለም! ወደ ዶን የጥርስ ኦርቶዴንቲክስ ማዕከል እንድትላክ ተደርጎ… በልክህ ጥርስ ይሰራልሃል…! ከዚያ የቦምብ ቀለበት ከመግመጥ አልፎ.. ከፈለግህም ቦምቡን ከነነፍሱ የሚቆረጥምልህ… የአሣ-ነባሪ ጥርስ ይተከልልህና ባስቸኳይ እንድትዘምት ትደረጋለህ! እና… እያንዳንድሽ… መንግሥቱን ጎዳሁ ብለሽ… እንዳትሞክሪው! እንዳትሞክረው..! እንደማይቀርልህ አውቀው… ከነሙሉ አካልህ… የእናት ሀገርህን ጥሪ… ዝግጁ ሆነህ ተጠባበቅ..! ዳይ እንቀጥል ጓዶች! ጨርሰናል! ጊዜ የለንም! ማዕከላዊ የሚገቡት ካቦዎች የዕምነት-ቃል … ከምሳ በፊት.. ቢሮ በጠረጴዛዬ ላይ ተቀምጦ እንዲጠብቀኝ..!››
ብሎ እየተቻኮለ ኮንዶሚኒየም ከጠፋበት ሥፍራ ሊወጣ.. እግሩን አነሣ፡፡
‹‹የዕምነት ቃል ይምጣልኝ.. ነው ያሉን ጓድ ሊቀመንበር..?? እ… ካቦዎቹ ባያምኑስ ግን… ??››
‹‹ምን አልክ? ምን አልክ አንተ ደፋር? ይኸው ሀገር ምድሩ የሚያውቀው ከነነፍሱ ተነቅሎ የጠፋ ኮንዶሚኒየም ባለበት ሀገር ላይ ነው አላምንም የሚለው? እንዴት ቢደፍረን ነው አላምንም ማለት?!!! ልኩን ማስገባት ነዋ! ለምን ገልብጣችሁ አትገርፉትም! ወፌ ላላ ምንድነው ጥቅሙ?! ካሻችሁ ማዕረጉን በመቀስ፣ መቀመጫውን በሳንጃ ለምን አትወጉትም…??!! እንዴት ተደርጎ ነው የማያምነው?! ጓዶች! አሁን… ላለመተማመን ጊዜ የለንም! ማመን ግዴታ ነው፡፡ እያመንን፣ እየተማመንን፣ እና በእምነታችን መሠረት አብዮታዊ እርምጃ እየወሰድን ነው ወደፊት መጓዝ ያለብን! ተግባባን ጓዶች?!››
‹‹አዎ ጓድ ሊቀመንበር!››
‹‹ጥሩ!.. አሁን ቀጣዩ ጉብኝቴ ተሠርዞ… ቀጥታ ወደ ቤተመንግሥት!››
‹‹ለምን ጓድ ሊቀመንበር? እዚያ እኮ ሕዝቡ ይመጣሉ ብሎ እርስዎን እየጠበቀዎት ነው!››
‹‹አልሄድም! ተናገርኩ እኮ የምንሄድበትን! ንገራቸው እንደማልመጣ! ቤተመንግሥትም የጠፋ አንበሣ አለ ሲባል ስለሰማሁ! በቀጥታ ወደ ቤተመንግሥት! እናንተ ሰዎች… ስንቱን ነገር አስወስዳችሁ… አሁን ኮንዶሚኒየም በቁሙ አስወስዳችሁ.. የቤተመንግስቱን አንበሳ በቁሙ አስወስዳችሁ.. ምን እስኪቀን ነው እጃችሁን አጣጥፋችሁ የምትጠብቁት??! በስም ካልሆነ የለንም እኮ! በቁመናችን ተቀብረናል! ወረውናል! ደፍረውናል! የለንም!››
መቼም ተናደዱ ያላቸው ናቸው እርሳቸው፡፡ የሆነ ያልሆነው ሁሉ ያናድዳቸዋል፡፡ ጓድ መንግሥቱ ንዴታቸውን ሲጨርሱ በአጃቢዎቻቸውና በቅርብ ተጠሪዎቻቸው ተከበው.. ኮንዶሚኒየም ሣይቱን ታክኮ ወደሚያልፈው ወደ ዋናው አስፋልት ወጡ፡፡.. እና በመንገዱ ዳር ከተደረደሩት ሁሉም አንድ ዓይነት የሚመስሉ አረንጓዴ ሩሲያ ሠራሽ ዋዝ መኪኖች… ወደ አንደኛው.. በአጃቢያቸው እየተመሩ ገቡ፡፡ ሌሎቹም እርሳቸውን ተከትለው በየሁሉም ውስጥ ተደረገሙ፡፡ እና መንጌ በመኪናው ኋላ መቀመጫ ተደላድለው እንደተቀመጡ… ከፊት ጋቢና የተቀመጠውን ልዩ የደህንነት ሰዋቸውን እንዲህ አሉት፡-
‹‹እናንተ ግን.. ከአሁን በኋላ.. በምንም ተዓምር… በዚህ ሰዓት መንግሥቱ ይሄን ይጎበኛል.. ከዚህ ቀጥሎ ያንን ያስመርቃል.. ከዚያ ቀጥሎ በዚህ ሰዓት ጉብኝቱን በእዚህ ሥፍራ ያሣርጋል… ምናምን.. እያላችሁ ዝርዝር ፕሮግራሜን በየሜዳው የምትረጩትን ነገር… ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ እንድታቆሙ..!! በፍፁም ይህ ነገር እንዳይደገም!››
‹‹ለምን ጓድ ሊቀመንበር? ህዝብን ተዘጋጅቶ እንዲጠብቅዎት ማድረግ የለብንም ነው የሚሉት? ህዝቡስ በሥፍራው እየተገኘ ለእርስዎ አቀባበል ቢያደርግልዎት፣ የእርስዎን የቅስቀሳ መልዕክቶች ቢሰማ… ምንድነው ክፋቱ?››
‹‹ክፋት ኖረውም አልኖረው.. አሁን ይቁም ይሄ ብያለሁ! ከአሁን በኋላ ይቁም! ተግባባን??!!››
‹‹እሺ ይቆማል ጓድ ሊቀመንበር! ግን ምክንያትዎት እንዳልገባኝ እንዲያውቁት እፈልጋለሁ… ሊነግሩኝ ይችላሉ?››
‹‹ምንም ድብቅ ምክንያት የለውም… ግልፅ እኮ ነው!!! እዚህ.. እዚህ ዓይናችን ሥር… በዚህ ሁሉ ነዋሪ መሐል.. እዚህ ስንት ሰው በሚመላለስበት አውራ ጎዳና አጠገብ… አንድ ሙሉ.. ኮንዶሚኒየምን ያህል ህንፃ… ከነነፍሱ ነቅሎ የወሰደ ሰው… እዚህች ሀገር ላይ እየተነፈሰ በማናውቀው ሥፍራ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለት ምንድነው ለናንተ የሚሰጣችሁ ትርጉም!?? ንገረኝ እንጂ?!!!
‹‹… መንግስቱ በዚህ ሥፍራ ገባ፣ በዚህ ሰዓት ይገኛል፣ በዚህ ሰዓት በዚህ በኩል ያልፋልና ቀድመህ ጠብቀው፣…. እያልን ስንናገር ሲሰማ…፣ አይደለም እኔን… ቤተመንግሥቴንስ… ከነነፍሱ የመውሰድ ዝግጅት አድርጎ አይጠብቀንም ነው የምትለኝ?! በል እንጂ ንገረኝ! ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ከነነፍሱ የወሰደ… አንድ እኔን መንግስቱን አይወስደውም ነው የምትለው?! ወይስ ይወስደዋል!?? ተናገር እንጂ? እያናገርኩህ እኮ ነው፣ ጓድ!!??››
‹‹አዎ ይወስደዋል.. ጌታዬ!››
‹‹በጣም ጥሩ! ሳይወስደው በገባበት ገብታችሁ ያዙት! ሳይቀድመን እንቅደመው! ለምሳ ሲያስበን ለቁርስ እናድርገው! አየህ.. ሰውን ማዕከላዊ የምልከው… እንዲህ ከሰዉ ሁሉ ቀድሜ… በግንባር ቀደምትነት ለዚህች እናት ሀገር በማሰብ ነው…! እንጂ ለክፋት ተፈጥሬ አይደለም! እና ምን ክፋት እንዳለው አትጠይቀኝ! አሁን… ይሄ ሰው ካለበት ታድኖ ካልተያዘ… ምን ጉድ ሊያመጣብን እንደሚችል ታየህ?! ታየህ አሁን ምክንያቴ አይደል ወለል ብሎ?!››
‹‹አዎ.. ጓድ ሊቀመንበር!››
‹‹በጣም ጥሩ! አሁን መንገዳችንን መቀጠል እንችላለን! ግን በዚህኛው በኩል አይደለም! በዚያ በኩል! … ሰውዬ! የምልህ አይሰማህም? በዚያ በኩል እኮ ነው የምልህ! በዚያ…! አ….ዎ!!! በዚያ በኩል!!!! ኡፍፍፍፍ….!!!! ሰሞኑን ቀልቤ የሆነ ነገር ይነግረኛል! ሥጋት የሌለበት ቀን መች ነው የማሳልፈው?! ሠላም ሆይ በየት በኩል ላግኝሽ?!!… አንተ ሰውዬ ዛሬ ጤና የለህም? ወይስ… ?? በዚያ በኩል እኮ ነው ያልኩህ!! አዎ… በእሱጋ! በጣም ጥሩ!!!››
ይህን ብለው ጓድ መንግሥቱ ራሳቸውን በመኪናው ወንበር ላይ ጣል አድርገው በረዥሙ ተነፈሱ፡፡ ‹‹እፎ…ይ….! እስኪ ይሁን! ተቃጠልን እኮ!››፡፡ ሹፌሩ በስፖኪዮው መስታወት እያያቸው ቃል ሳይተነፍስ በተነገረው አቅጣጫ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ጉዞው አያልቅም፡፡ ሁሉም ቀን የሩጫ ነው፡፡ እፎይታ የሌለው ቀን፡፡ ሁሌ፡፡
‹‹አስራ ሰባት ዓመት ሙሉ ስቀን አናውቅም!››
      — ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም

ፎቶግራፉ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
‹‹ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም የሙገር ሲሚንቶ ማስፋፊያ ቁ.2ን በሥፍራው ተገኝተው እየጎበኙ፣ ከአዲስ ዘመን የኢኮኖሚ ዘገባዎች ድረገጽ፣ ታሪክ በዛሬው ዕለት፣ ጁን 2016››፡፡
Assaf Hailu – July 7, 2018  • Shared with Public
Filed in: Amharic