>

በ62 የሕወሓት ቡድን አመራሮች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መዝገብ ተከፈተ!!  EBC - ጥላሁን ካሣ 

በ62 የሕወሓት ቡድን አመራሮች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መዝገብ ተከፈተ!!
 EBC – ጥላሁን ካሣ 

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፣ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር፣ ዶ/ር አብረሃም ተከስተ፣ ጌታቸው ረዳ እና ሊያ ካሳን ጨምሮ በ62 የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አመራሮች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መዝገብ ከፍቷል።
በዚህ የሽብር ወንጀል ክስ መዝገብ ላይ የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ የወንጀል ተሳትፎ ተጠቅሷል።
በቀዳሚነት በመዝገቡ ውስጥ የተካተቱት 61 ግለሰቦች በትግራይ ክልል ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ ምርጫ ማካሄድ እና እሱን ተከትሎም የፌዴራሉን መንግሥቱን በኃይል ለማስወገድ የተለያዩ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በሌላ በኩል አጠቃላይ በክልሉ ያለውን የፀጥታ መዋቅር በመቀየር “የኃይል ዘርፍ” የሚል ስም የተሰጠው ጦርነት የሚያመቻች አዲስ መዋቅር በመዘርጋትም ተከሰዋል።
ይህ መዋቅር በሥሩ ያለውን አጠቃላይ የፀጥታ ኃይል በመምራት የተለያዩ እኩይ ተግባራትን ሲፈፅም እንደነበርም ነው የተገለጸው።
የኃይል ዘርፍ” የተባለው መዋቅር ጦርነትን ወይም አጠቃላይ በሀገሪቱ ላይ የተደራጀ ግጭትን ለመፍጠር የሚያስችል አደረጃጀት ካስተካከለ በኋላ መዋቅሩ “የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ” ወደሚል መቀየሩ ተገልጿል።
ከዚህ መዋቅር ውጭ ደግሞ “የኢኮኖሚ መከታ ኮሚቴ” ተቋቁሞ ሀብት ሲያፈላልግ ነበርም ተብሏል፤ በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት ለክልሉ የሚሰበሰብ የፌዴራል መንግሥቱ ሀብት 251 ሚሊዮን ብር እና ከደደቢት እና ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ 61 ሚሊዮን ብር በኃይል ተዘርፏል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል ያለውን የመንግሥት የነዳጅ ሀብት እና ሌሎች ሀብቶችን በመዝረፍ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ አደረጃጀት ሲጠቀምበት እንደነበር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
እነዚህ የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን አመራሮች አደረጃጀቶቹን ከፈጠሩ በኋላ ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም ወታደራዊ ትጥቆችን የመዝረፍ እና ቁጥሩ ይህ ነው ተብሎ የማይገለፅ በርካታ ወታደሮችን የመግደል እንዲሁም ሌሎችን ወንጀሎችን የመፈፀም ክስ ቀርቦባቸዋል።
ግለሰቦቹ መንግሥትን ለማስገደድ በማሰብም ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎችን ያስገደሉ እና አግተው ከቦታ ቦታ ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ በመሆኑ በፈፀሙት የሽብር ወንጀል እና በከባድ ሁኔታ በሕገ-መንግሥት እና በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ በሚፈፀም ወንጀል የተደራጀ ክስ ተዘጋጅቷል።
ለክሶቹም ከ5 ሺህ 300 በላይ የሚሆኑ የሠነድ ማስረጃዎች መደረጃታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ-ሽብር እና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ይህንን የወንጀል ተሳትፏቸውን የሚመለከት ክስ በማደራጀት የክስ መዝገቡን ከፍቷል።
ችሎቱ መዝገቡን ለመመልከት ለሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
Filed in: Amharic