>

H.I.M የጠቅልን ልደት በማስመልከት ቁምነገር አዘል  ጨዋታዎችን እነሆ በረከት ... !!! (ኤፍሬም ጀማል አብዱ)

H.I.M የጠቅልን ልደት በማስመልከት ቁምነገር አዘል  ጨዋታዎችን እነሆ በረከት … !!!
ኤፍሬም ጀማል አብዱ

ምኒልክ እንደሞቱ ሰሞን ነው መኳንንቱ በየቤቱ አድማውን በእቴጌዋ ላይ አጧ ጡፈውታል። ለደጃዝማች ተፈሪም ከአድመኞቹ የ”ከእኛ ጋር ይሁኑ”ጥሪ ሲደርሳቸው የመለሷት መልስ ታስቃለች
“እኔ ልጅ ነኝ ለነገር ገና አልደረስኩም”
እቴጌ ይህን ሰምተው የአባታቸውን የሐረርጌን ግዛት መልሰውላቸዋል።
*********
ፕሬስ ኮንፍራንስ ላይ አንዱ ጃንሆይን ጠየቀ”ጥቁር አይደለንም ትላላችሁ ይባላል እውነት ነው? “
“መስታወት አለንኮ”
መልሰውለታልም አልመለሱለትምም!!
********
የነገስታቱ እና የመኳንንቱ ልጆች ተሰብስበው ጉግስ ሲጫወቱ ደጃዝማች ተፈሪ ከጥግ ሆነው ይከታተላሉ።ይህን የተመለከቱት ምኒልክ
“ተፈሪ ምነው አንተስ አትጫወት”
“ሁሉ ተጫዋች ከሆነ ማን ይመልከታቸው ጃንሆይ”
********
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የአሜሪካ አምባሳዶር የነበረው kory ተቀባይነት የነበረው ዲፕሎማት ሲሆን እሱ በቀረፀው the kory doctrine ነበር አሜሪካ ከመላው ምስራቅ አፍሪቃ ጋር ግንኙነትዋን የምታሰምረው።ኮሪ በዚህ ባወጣው ዶክትሪን ኩራት ተሰምቶት ልቡ አበጠ።የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዘንድ ሲገባ በጨዋ ዲፕሎማስያዊ መንገድ ሳይሆን HI በማለት ጠረጴዛው ላይ እግሩን አነባብሮ ይቀመጣል።ጃንሆይ ደብዳቤ ፅፈው ይህን ስድ ምሉክ ማስቀየር ሲችሉ አላደረጉትም ግዜ ጠበቁ።በአንድ ጉብኝት ወቅት የአሜሪካ ፕሬዚደንት እንግዳ ሆነው ሲሄዱ ኬሪ አጀቧቸው ተጓዘ።ከፕሬዝዳንቱ ጋር ሰላምታ እንደተለዋወጡ ወዲያው
“እባክዎ ሌላ አምባሳዶር ይላኩልን?ኮሪ የሚባል ስድ-አደግ ወደ ሀገራችን እንዳይመለስ”
*******
ይህቺን ጨዋታ የሚነግረን ስብሐት ከሰዎች የሰማሁት እውነተኛ ጨዋታ ናት ይለናል።
ጃንሆይን የሚጠላ አንድ ጀብራሬ ጠጅ ጠጥቶ ሞቅ ብሎት ሲወጣ የሳቸውን ፎቶ
አየው ቆመና በንቀት”አሁን ይሄ ሰው ነው?
አለ።
ደግነቱ በፍጥነት ነቃና አደጋ ላይ መሆኑ ሲታሰበው በታሪክ ከታዩት ታላላቅ
U-TURN አዟዟሮች መሃል አንዱን ዞረ!
“መልዐክ ነው እንጂ”
*******
ብዙ ግዜ ሰዎች ኃይለሥላሴን ፈሪ ነበሩ ይሏቸዋል።ከቴዎድሮስና ከዮሐንስ አንፃር
ብዙ አውደ-ውጊያዎች ላይ ባለመዋላቸው የተሰጣቸው ቅፅል መስሎ
ይሰማኛል።ለአብነት የአምባሳዶር ብርሃኑ ድንቄን የማይጨው ጦርነት ምስክርነትን
ማንበብ ይቻላል።ዲፕሎማቱ ከሀገር ወጥተው በመሃላቸው ቁርሾ እያለ እንኳን
ንጉሥ በጀግንነት መፋለማቸውን አልደበቁም።እናማ የ53 ግርግር ወቅት እንዲህ ሆነ መፈንቅለ መንግስቱ በሬድዮ
እንደተሰማ ጃንሆይ ብራዚል ነበሩ።
ከመኳንንቱ ጋር ተሰብስበው ቢመክሩ ሁሉም በአንድ ድምፅ ሁኔታው እስኪረጋጋ እዚሁ እንቆይ አሉ።ጃንሆይ
በተቃራኒው “ጫን!”ብለው ትዕዛዝ በመስጠት ጉዞው ተጀመረ።
አውሮፕላናቸው አዲስአበባ ክልል ስትደርስ አቅጣጫዋን ቀይራ ወደሌላ መብረር ጀመረች።
“ወዴት እያበረርክ ነው? “
“ወደ ቢሾፍቱ ግርማዊ ሆይ አየር ሃይል ጣብያ እረፍት እንዲያደርጉ”
“በል ወደ ከተማችን መልሰን”
“ለደህንነትዎ ይበጃል ብዬኮ ነው”
ጃንሆይ ሽጉጣቸውን መዘው እራሱ ላይ እየደገኑ
“በል ወደ መናገሻችን አዙር ለራስህ ደህንነት ይበጃል”አዞረ።
አዲስ አበባ ቦሌ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አውሮፕላን ማረፍያ ሲደርሱ ጥይት የማይበሳውን መርሴዲሳቸውን አቀረቡላቸው።
“ሌላ ግዜ መናገሻችን ስንገባ እንደዚህ ነው የምንሄደው?”
“አይደለም ጃንሆይ”
“በል የሁልግዜ መኪናችንን አምጣ”
ጣራው ክፍት የሆነ ሮልስ ሮይስ መጣላቸው።እንደገቡ ሹፌሩ በፍጥነት
ይነዳ ጀመር።
“ወደ መናገሻ ከተማችን ስንገባ በዚህ ፍጥነት ነው? “
“አይደለም ጃንሆይ”
“ሌላ ግዜ እንደምንሄደው ቀስ ብለህ ንዳ”
ልክ እንደወትሮው ሰላምታ እየሰጡ እጃቸውን እያውለበለቡ በሚሰማው ተኩስ መሃል አልፈው ቤተመንግስታቸው ደረሱ።
********
በአንድ ወቅት ከተማ ይፍሩ ከንጉሱ ጋር ይነጋገራሉ
“ጃንሆይ የአፍሪቃ ህብረት እንዲመሰረት አስተዋጽኦ አድርገዋል።የአልጄሪያ እና የሞሮኮ ብጥብጦችን አሸማግለዋል። ኤርትራን ከእናት ሀገሯ እንድትቀላቀል አድርገዋል ….በዘመኔ ይህ ቀረኝ ሳልሰራው የሚሉት ወይም ምነው ባልሰራሁት ኖሮ ብለው የሚቆጩበት ነገር አለ ካለስ ምን ይሆን?”
“እሚቆጨን አንድ ነገር ብቻ ነው።በላይ እንዲሰቀል መፍቀዳችን!”
*******
ወታደራዊ ሃይሉ ታሪካዊ ንግግሯን አድርጎ በፎክስዋግን መኪና ንጉሱን ወደ ማረፊያው ይዟቸው ሲወጣ ህዝቡ ሌባ!ሌባ!እያለ ሲጮህ ወታደሮቹ እርስ በእርሳቸው
“ህዝቡ ማንን ነው ሌባ እያለ የሚጮኽው?
ጃ”ታድያ ንጉሡን ስትሰርቁት ምን ይበል”
**********
ደጃች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) ጃ ስልጣን ለመያዝ በሚሟሟቱበት ወቅት ትልቁ ተግዳሮታቸው ነበሩ።በአንድ ወቅት ወደ ቤተመንግስት ሲያስጠሯቸው ጦራቸውን በሙሉ ይዘው መጥተው ፉሪ ተራራ ላይ ሰፈር አድርገው ጥቂት ምርጦችን ይዘው ወደ ቤተመንግስቱ ዘለቁ።ተበላ ተጠጣ ሞቅታ ሲመጣ ባልቻ ከነተከታዮቻቸው ተነስተው መፎከር ማቅራራት ጀመሩ።
አልጋወራሽ በዚህ ወቅት በጓሮ በር ወጥተው የባልቻ ጦር ወደሰፈረበት በመሄድ”ከእንግዲህ ጌታችሁ አልፈልጋችሁም ብሏችኋል”ብለው ለእያንዳንዱ ደሞዙን ሰጥተው ወደ ሀገሩ ያሰናብታሉ።ተመልሰው መጥተው ባልቻን ጦርነት ከፈለጉ መጋጠም እንደሚችሉ ነግረው ያሰናብቷቸዋል። ባልቻ ወደ ጦራቸው ሲመለሱ ሰፈሩ ወና ሆኖ ቢያኙት አንዲት የምትገርም ነገር ተናግረዋል
“ተፈሪ አካሉ የአይጥ ቢሆንም መንጋጋው የአንበሳ ነው “
*********
ካየሁት ከማስታውሰው ልዑል ራስ እምሩ
የትረካ ጥበብ ስብሐትለአብ ገብረእግዚአብሔር
እና ሌሎች ቃለ መጠይቆች በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ።
Filed in: Amharic