>

የሀገር ክህደትና አሸባሪነት ኢትዮጵያን ከባድ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል የምእራቡ አለም መገንዘብ አለበት ( ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የሀገር ክህደትና አሸባሪነት ኢትዮጵያን ከባድ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል የምእራቡ አለም መገንዘብ አለበት

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


በእኔ የግል ምልከታ ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ የምትገኝ ሀገር ሆና ትታየኛለች፡፡ የኢትዮጵያን ዳርድንበር እና ሉአላዊነት  ማስከበር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሃላፊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የሄደችበትን የቁልቁለት መንገድ ማለትም የባልካናይዜሽንን መንገድ አንደ ባለፉት አመታት ሁሉ ከቀጠለችበት  አንድም ጎሳ ወይም ብሔረሰብ የሚጠቀም አይሆንም፡፡

የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት፣ እንዲሁም ሌሎች በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አንዳንድ የመንግስት አካላት የሚፈጽሙትን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መገንዘብ፣መመርመር፣ ማወቅና እውነታውን መገንዘብ አስከትሎም በማስረጃ እና በገለልተኝነት አቋም የሰብዓዊ መብት ሁኔታን መመስከር ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም  የደህንነት መጠበቅን ፣ሰላም እና  መረጋጋትን የሚያስገኘው፡፡ለአፍሪካው ቀንድም ሆነ ለቀሪው አለም ሰላምና ደህነነት የሚበጅ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የሀገር ክህደትና አሸባሪነት በየትኛውም አለም ቢሆን የመከላከያ ክትባት ከተገኘለት የኮሮና ቫይረስ በሽታ ከሚያመጣው ጉዳት በላይ አስከፊ መዘዝ ያስከትላል፡፡ ለአብነት ያህል አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ማሊ እና ሞዛምቢክ  በሀይማኖት ጽንፈኛ አሸባሪዎች ፍዳቸዋን እንደሚቆጠሩ ማወቁ ብልህነት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ያም ሲያማህ፣ያም ሲያማህ ወገኔ ለኔ ብለህ ስማ የሚለውን የዝነኛውን ድምጻዊ ጋሼ ጥላሁን ዘመን አይሽሬ ዜማ ያስታውሰናል፡፡

ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢትዮጵያው የተወካዮች ምክር ቤት ( ፓርሊንሜንት) በመጨረሻ በቅርብ ግዜ ውስጥ የተግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት እና ኦነግ ሸኔ በመባል የሚጠረውን ታጣቂ ቡድን በአሸባሪነት ፈርጇቸዋል፡፡ ስለሆነም ወይም በእኩል ደረጃ አለም አቀፉ ህብረተሰብ፣ የብይነ መንግስታቱ ልዩ ተወካይ፣አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ምሁራን የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪ ሲል የሰየማቸውን ቡድኖች ማውገዝ ወይም አሸባሪ ስለመሆናቸው ለመቀበል የሞራል ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በውጤቱም በኢትዮጵያ ሰላም እና የህዝብ ደህንነት እንዲከበር አለም አቀፉ ህብረተሰብ በቅን መንፈስ እና ከወገናዊነት በጸዳ መልኩ መተባበር ያለበት ይመስለኛል፡፡ የአለም አቀፉ ህብረተሰብ በህሊና ሚዛን ላይ ተቀምጦ በኢትዮጵያ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ መፈለግ እንጂ ለአንዱ ቡድን ወገንተኛ መሆኑ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ለአሸባሪዎች፣አክራሪዎች፣የሃይማኖት ጽፈኞች፣ ለሙሰኞች እና ለሌቦች ገነት መሆን የለባትም፡፡

የኢትዮጵያ እድገት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም አርአያ ሊሆን ይቻለዋል

ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሆነ ዲሞክራቲክ እና የበለጸገች ሀገር ለመሆን ሰፊ እድል ያላት ሀገር ናት፡፡ ይህ እውን ሊሆን እንዲቻለው ግን የሚከተሉት ቁምነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡

  • በሀገር ውስጥ የተከፋፈሉና የማይተማመኑት የፖለቲካ ሀይሎች ተቀራርበው በሰለጠነ መንገድ መነጋገር ይኖርባቸዋል፡፡
  • የኢትዮጵያ ወዳጅ ሀገራት በኢትዮጵያ ነጻነት፣እኩልነት እና ፍትህ እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጉ ጠቀሜታው ጉልህ ነው፡፡
  • ኢትዮጵያን ከልብ የሚወዱ የሀገር ቤት ልጆችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያ ከጎሳ ፖለቲካ አጣብቂኝ ስለምትወጣበት መንገድ የሰለጠነ ፖለቲካ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
  • አንዱ የጎሳ አካል ለሌላው ባይተዋር እንዲሆን የሚፈቅደውን የጎሳ ፖለቲካ ኢትዮጵያውያን በምን አይነት መልኩ ማለትም እንዴት በሰለጠነ መንገድ፣ በመነጋገር፣በመወያየት መፍታት እንዳለባቸው መንፈሳዊ ወኔ መታተቅ ከቻሉ፣ ለኢትዮጵያ እድገት ስልጣኔ ማምጣት እዳው ገብስ ይሆናል፡፡( ነጻነት፣ትምህርት፣ሀብት….ለማምጣት መንገዱ ቀና ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ በሰውነት ደረጃ ለመቆም መንፈሳዊ ወኔ እንታጠቅ፡፡)

በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ በጎሳና ቋንቋ መሰረት ላይ በቆመ ህገመንግስት ከሚተዳደሩ አራት ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ፓኪስታን ሌላኛዋ ሀገር ስትሆን ከባድ ዋጋ ክፍላበታለች፡፡ ባንግላዴሽ ከእናት ሀገሯ ፓኪስታን ተገንጥላ ሌላ አዲስ ሀገር ሆናለች፡፡ በተፈጥሮ ሀብት እጅግ የበለጸገችው ደቡብ ሱዳን በውስጣዊ ግጭት ትታመሳለች፡፡ ኔፓል ከግጭት አዙሪት መውጣት ያቃታት በኤሽያ አህጉር የምትገኝ ሀገር ስትሆን በድህነት የምትደቆስም ናት፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ የባህር በሯን አጥታ ከባድ ዋጋ መክፈል እጣ ፈንተዋ ሆኗል፡፡

ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሀይል በሚገጥሙ ጫናዎች ምክንያት አንድን ነገር ደጋግሞ መሞከሩ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ለማየት ሩቅ መሄድ አያስፈልገንም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ከባድ ጥፋት እንደሚያስከፍል አፍንጫችን ስር ያሉት ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ትምህርት ሊሆኑን ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ምድርም የተከሰቱት ጎሳ ተኮር ግጭቶች ያስከተሉት ዳፋ ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ ከፊደል መማር ካቃተን ከመከራ እንማር፡፡

በተመሳሳይ ግዜ ኢትዮጵያውያንና አለም አቀፍ ህብረተሰብ ልጃቸውን ወደ ውሃ ገንዳ ውስጥ መጨመር የለባቸውም፡፡ አንዳንድ ጠቃሚ እሴቶችና የታወቁ ተቋማት መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የኢትዮጵያ አንዲት ሀገር ሆና መቀጠል በምንም አይነት ጥያቄ ውስጥ መዶል የለበትም፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ የድንበር መከበርና ሉአላዊነት መከበር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሙሉ ሊደግፈው የሚገባ ነው፡፡ ወይም የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያ ተከትላው የነበረውን የመከፋፈል መንገድ ከተጓዘችበት የሚጠቀም ማንም የለም፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊዜጎች ሁሉ ተጎጂ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ግብጽ የመሰሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ እንዲህ አይነት እንዲሆኑ ሌት ተቀን እንደሚባዝኑ ማወቁ ተገቢ ነው፡፡

ለምንድን ነው ትልቁ ስእል ላይ ትኩረታችን ማረፍ ያለበት ?

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያገኘችውን የውሃ ሀብቷን ከ116 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ህዝቧ በሚጠቅም መልኩ ማዋል አለባት፡፡ 60 ፐርሰንቱ የሚጠጋው ህዝቧ በጨለማ ውስጥ በሚዳጅረው ኢትዮጵያ፣በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝቧ ንጹህ ውሃ በማያገኝባት ኢትዮጵያ፣በ10 ሚሊዮን የሚገመት ወጣት ትውልዷ ስራፈት በሆነባት ኢትዮጵያ ወዘተ ወዘተ መሰረታዊ ችግሮችን መፈታት ካልተቻለ የተጠቀሱትን ችግሮች ከቶውንም ማስወገድ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮቿን መፍታት ካልሆነላት የውሃ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም አይሆንላትም፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተገንብቶ ማለቅ ብሔራዊ ቅንጦት አይደለም፡፡ የዚህ ግድብ ተሰርቶ መጠናቀቅ ብሔራዊ የመኖር ጥያቄ ነው፡፡ (. It is a matter of national survival.)

ሁላችንም እንደምናውቀው የታላቁ አባይ ግድብ ግንባታ ወጪ በኢትዮጵያ ህዝብ የሚሸፈን ነው፡፡ ደሃ ገበሬዎች፣ጫማ ጠራጊዎች( ሊስትሮ)፣ ወዘተ ገንዘብ አዋጥተዋል፡፡ ገብጽ የሃሰት ትርክት እንደምታቀርበው ሳይሆን ይህ ታላቅና ክብር ያለው ፕሮዤ የናይል ወንዝ ውሃ መጠንን አይቀንሰውም፡፡ በእኔ በኩል ግብጽ የቅኝ ገዢዋን የታላቋ ብሪታኒያ የውሸት ትርክት ይዛ የምትነዛው ዲስኩርና ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን እኔን እጅጉን እንቅልፍ የሚነሳኝ ጉዳይ የኢትዮጵያ የውስጥ አንድነት መላላት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ ምድር የውክልና ጦርነትና ግጭት እንዳይቀሰቀስ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡ኢትዮጵያውያን ስለአንድነት ሲሉ ብዙ እርቀት መጓዝ አለባቸው፡፡ ለግዜውም ቢሆን ያላቸውን ቁርሾና ልዩነት ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ የሕብረት ፍልስፍና መከተል አለባቸው፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የብዙ ሰው ሕይወት ስለቀጠፈውና እጅግ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ስላወደመው ያላቋረጠ ረብሻና ሁከት በኢትዮጵያ ምድር ስለመከሰቱ ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ በቅርቡ እንኳን በሰሜናዊት የኢትዮጵያ ክፍል በትግራይ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት በቢሊዮን ብር የሚገመት የመገናኛ አውታሮች እና ኢንቨስትመንቶች ወድመዋል፡፡  በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ያለው ያለመረጋጋት አስቸኳይ እና ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀለት ዳፋው ለአፍሪካው ቀንድ፣ለምስራቁ የአፍሪካ ክፍል፣ለሰሜን አፍሪካ እንዲሁም ለመካከለኛው ምስራቅ ሊተርፍ ይችላል፡፡

የእኔን የግል አስተያየት በተመለከተ የማቀርበው በቀጥታ ነው፡፡ የአለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይም የምእራቡ አለም ዴሞክራሲና አጋሮቹ አለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ አኳያ ካላቸው አቋም የተነሳ በሞራል እና ህሊና ሚዛን እንዘጭ እምቦጭ ብለው ወድቀዋል፡፡ በትግራይ ባለው የሰብዓዊ ቀው አኳያ ካላቸው አቋም የተነሳ ስለ ጎጻ ማጽዳት፣ የዘር ማጥፋትና የህዝብ መፈናቀል ወዘተ በተመለከተ በሞራል ደረጃ ላይ ሆነው የህሊና ምስክርነታቸውን ማስቀመጥ አልቻሉም፡

በነገራችን ላይ ዛሬ የሚታየው ውድቀት የተከሰተው በአንድ ለሊት አይደለም፡፡ ለዛሬው ብሔራዊ ውርደት እርሾ የሆኑ በርካታ ተራጄዲክ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡ ለአብነት ያህል፡-

  • ድምጽ አልባ የጎሳ ማጽዳት (Silent ethnic-cleansing )
  • ለይቶ መግደል
  • የዘር ማጥፈት የሚመስሉ ግድያዎች
  • በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች እትብታቸው ከተቀበረበት መሬት መፈናቀልና በሀገራቸው ኢትዮጵያ ምድር ባይተዋር መሆን ወዘተ ወዘተ በኢትዮጵያ ምድር ባለፉት ሰላሳ አመታት በነቢብም በገቢርም የተከሰቱ መራር እና ጎምዛዝ ሁነቶች ናቸው፡፡ እነኚህና ሌሎች እኔ ያልጠቀስኳቸው ተራጄዲክ ሁነቶች ተጠራቅመው ነው ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት አስጊ ሁኔታ ያበቋት፡፡

ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እንደቀደመው ዘመን የነበራት የክብር ስፍራ የቀነሰ ይመስላል፡፡የዚህ ምክንያቱ የጎሳ አምበሎች ከኢትዮጵያዊ ስሜት ይልቅ ጎሰኝነት እና ጎጠኝነት እንዲያቆጠቁጥ በብርቱ ስለተጉ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ ለርስበርስ ጦርነትና ለውጭ  ሀገር ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጥቃት ያጋለጠን መሆኑን ማወቁ ተገቢ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ምድር የሚከሰቱት ግጭቶች ሁሉ ከአካባቢው ፖለቲካ ሁኔታ ጋር የሚገናኝ  መሆኑን መረዳት ብልህነት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ግብጽ የታላቁን የኢትዮጵያ ግድብ ስራ 

ለማስተጓጎል በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት  ከራሷ ጥቀም አኳያ ለመጠቀም  ስትል የማትጎነጉነው የሴራ ፖለቲካ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪከ ውስጥ ግብጽ አንድም  ቀን ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና የሚደማ ልብ ኖሯት አያውቅም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም  ዝግጁ ነኝ፡፡ የግብጽ ምኞትና ፍላጎት እንዲሁም የብዙ ዘመናት ውጥኗ በኢትዮጵያ ምድር ተድላና ደስታ እውን እንዲሆን ሳይሆን አርማጊዶ እንዲፈጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከብዙ አመታት በፊት አቅዳ የነበረችው የመስኖ ልማት ፕሮዜዎች ለማሳካት

ደፋ ቀና ስትል ከአለም ባንክና ከአፍሪካ ልማት የገንዘብ ብድር እንዳታገኝ  የግብጽ ዲፕሎማቲክ ሴራ እረጅም እጅ ነበረው፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ

የክፋት ሃዋርያ አልሆነችም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል አጼ ሀይለስላሴ በዘመነ መንግስታቸው ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገሮች  (ግብጽና ሱዳን) የተፈጥሮ ውሃዋን በእኩልነት ካፍላቸዋለች  በማለት  ለአለሙ ህንረተሰብ ህብረተሰብ በግልጽ አሳውቀው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከሁለቱም ሀገራት መሪዎች የተሰጠ ቀና ምላሽ አልነበረም፡፡

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ስሜት መውደቅ የጋራ ችግር ስለሆነ የጋራ መፍትሔ ያስፈልገዋል

የኢትዮጵያ ዜጎች የሃይማኖትና የጎሳ ልዩነት ሳይደረግባቸው ለልጆቻቸው ስራ የሚሰጥ  መንግስት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለልጆቻቸው ጥይትና መሳሪያ 

የሚያስታጥቅ መሪ አይሹም፡፡ ዛሬውኑ የሚጨበጥ መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎታቸው እንዲሟሉላቸው ፍላጎታቸው ነው፡፡ በህይወት የመኖር መብታቸው እንዲከበርም ይጠይቃሉ፡፡

እንደ አውሬ መታደን አይፈልጉም፡፡ ሴት ልጆቻቸው በአጉራ ዘለል ታጣቂዎች ክብራቸው እንዳይደፈር የሚጠብቅ መንግስትን ይፈልጋሉ፡፡ለይቶ መግደለም ይሁን የዘር ማጥፋት ወይም የጎሳ ማጽዳት ወንጀል በአንዱ የኢትዮጵያ ጎሳ ወይም ብሔር ላይ ቢፈጸም ውረደቱና ሀዘኑ ለኢትዮጵያውያን ነው፡፡ የጎሳ ማንነታችን በሌላው ወንድማችን ላይ የሚደርሰው እከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳያመን ሊያደረገው አይቻለውም፡፡ የአንዱ ቤት ሀዘን ለሌላው ሰርጉ ሊሆን አይገባውም፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ችግር ግልጽ ብሎ ወጥቷል፡፡ ተራ ዜጎች በሰው ሰራሽ ምክንያት የተከሰተውን የዋጋ ግሽፈት መቋቋም አልቻሉም፡፡ 30 ወይም 40 ፐርሰንት የሚጠጉት ኢትዮጵያዊ ወጣቶች  ስራ የላቸውም ወይም የስራ እድል ማግኘት አልቻሉም፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት 30 አመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ሀገር እርዳታ ብታገኝም በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ በድህነቷ የምትታወቅ ሀገር ናት፡፡ ያሳዝናል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ የከተማ ርሃብ አለ፡፡

ጸሃፊው በአዲስ አበባ ከተማ የሚንከራተቱ በርካታ ሰዎች አነጋግሮ በሰጡት መልስ በቀን አንድ ግዜ ብቻ የሚመገቡ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ለማወቅ ችሏል፡፡ ይህን ጽሁፍ በማጠናቅረበት ግዜ አንድ ፒያሳ መሃል ያገኙሁት የሰፈሬ ልጅ የነበረ ሰው ዛሬ ቁርስና ምሳ አልቀመስኩም ሲለኝ ክፉኛ አዘንኩ፣ደነገጥኩም፡፡ ያዘንኩትም ሆነ የደነገጥኩት ለግለሰቡ አልነበረም፡፡ ለኢትዮጵያ ነበር ያዘንኩት፡፡ እንዴት የሰው ልጅ በቀን አንድ ዳቦ እንኳን ያጣል በሚል ነበር ልቤ የደማው፡፡ 

ግለሰቡ አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገና የዩነቨርስቲ ትምህርቱንም በ1970ዎች የጨረሰና በሱስየተጠመደ የነበረ ሲሆን በርካታ የስራ እድሎቹንም በሱሰኝነቱ ምክንያት ያመከነ ግለሰብ ሲሆን፣ ከአመታት በኋላ ግን ሱሰኝነቱን በመተው ስራ ለማግኘት ቢፈልግም አልሆነለትም፡፡ግራም ነፈሰ ቀኝ ይህ ግለሰብ እናቱ ከዚች አለም ሲለዩ በሰጡት የቀበሌ ቤት እየኖረ ይገኛል ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) ውድ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ የዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያቶች ስግብግብ ነጋዴዎች ቢሆኑም እኛ ሸማቾችም ተጠያቂዎች ነን ብዬ አስባለሁ፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት ሁሉ  በቀንድ ከብት ብዛት አንደኛ በሆነች ሀገር እንደየ ደረጃው በሚለያይ ዋጋ ስጋ ተገቢ ባልሆነ ዋጋ  እየገዙ የሚመገቡ ሰዎች ቁጥር የትዬሌሌ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ስጋ እስከ 1000 ብር እያወጡ  የሚመገቡ ሰዎች አሉ ይባላል፡፡ ይህ አግባብ አይደለም፡፡ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድማችንም አለማሰባችንን ያመላክታል፡፡ እኛ እኮ አንገዛም በማለት ለሶስት ቀን ወይም ለአንድ ሳምንት  ፊታችንን ወደ ቆስጣና ቲማቲም ብንመልስ የስጋ ነጋዴዎች ልካቸውን ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ 

እስቲ ሁላችንም እናስብበት፡፡ በየቤቱ ይሄ መንግስት እያልን ማማረሩ አይጠቅመንም፡፡ ኢትዮጰያን ካስቀደምን እድገታችን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ እና ቀጣይነት ይኖረዋል ይህ ርእስ ወደ አንድ ነጥብ እንደወስዳችሁ እረድቶኛል፡፡ በአክሱም ትግራይ ተፈጸመ የተባለውን  የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የምእራባውን የዜና አውታሮች ወገንተኝነት የምታስታውሱ  ይመስለኛል፡፡በነራችን ላይ በደምቢዶሎም ሆነ ነኮምቦልቻ፣አጣዬም ሆነ ጉራፈርዳ የተፈጸሙ  ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እኩል ሊሰሙን ይገባል፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር  ኖቬምበር 20 2020 ላይ በማይካድራ ከተማ ሳምሪ በመባል የሚጠሩ ኢመደበኛ ወጣቶች  የፈጸሙትን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ ዝማታን መርጦ የነበረው  የምእራቡ አለም በአክሱም ከተማ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ግን ከፍተኛ ወቀሳ አሰምቷል፡፡ እባካችሁ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ስለሚጸፈመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ትኩረት እንድትሰጡ እንማጸናለን፡፡ ትላንትም ሆነ ዛሬ  ኢትዮጵያውያንና የአለም አቀፉ ህብረተሰብ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡

እውን ሁለት አይነት ትርጉም አለውን ? የጎሳ ማጽዳት፣አስገድዶ መድፈር፣ሰዎችን ማፈናቀል  ወዘተ ዘወተ አስከፊ የሰብዓዊ መብት  ጥሰት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም እንዲህ አይነት የሰብዓዊ  መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች  ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በማያካድራ እና በአክሱም ከተማ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት  ጥሰቶችን በተመለከተ የምእራቡ አለም የያዘው አቋም እኔን ያሳዝነኛል፡፡ በማይካድራ ለተፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዝምታን የመረጠው የምእራቡ አለም በአክሱም ከተማ የሰብዓዊ መብት የጣሱት አካላት ሁሉ በፍትህ አደባባይ ላይ መቆምአለባቸው በማለት ሲሟገት ማየት የምእራቡ አለም ለፍትህ መከበር የሚደማ ልብ እንደሌለው ነው፡፡

 

እውን ግጭት ለኢትዮጵያ አዲስ ክስተት ነውን ?

  1. በመጨረሻም ምንም የማያውቁ ሲቪል ዜጎች በኢትዮጵያ ምድር ላይ በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያቶች የተነሳ ህይወታቸውን ማጣታቸው እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለአብነት ያህል ላለፉት 46 አመታት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ብቻ በሚጭራቸው የግጭት አዙሪቶች ንጹሃን ኢትዮጵያውያን ( በተለይም የትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻችን) ህይወት እንዲቀጠፍ አድርጓል፡፡ ስለሆነም የአለም አቀፉ ህብረተሰብ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትና ሌሎች ከትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ጋር የትግል አጋርነት ላላቸው ድርጅቶች መርዳት የለበትም የሚል አስተያየቴን አቀርባለሁኝ፡፡ የምእራቡ አለምም ሆነ ኢትዮጵያ ከጦርነት የሚጠቀሙ አይመስለንም፡፡
  2. የምእራቡ አለም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚሰፈው የኢትዮጵያውያን ወንድማማቾች ደም ምንም ግድ የሚሰጠው እንዳልሆነ በገቢርም በነቢብም የሚታይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ለማእከላዊው መንግስት እና ለትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ያለው አመለካከት የተለያየ ነው፡፡ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት በተለያዩ መንገዶች ድጋፉን እያሳየ ይገኛል፡፡ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ ዝምታን ይመርጣል፡፡ በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የተከለከለውን ሕጻናትን በጦር ሜዳ የማሰለፍ ህግ በመጣስ እንደ አንድ ጀብዱ ህጻናት ወታደሮችን ማሰለፉን የሚሳዩ ፎቶግራፎች በማህበራዊ ሚዲያ ቢለቅም ማንም የምራአብ አለም አልጠየቀውም፡፡ ለምን እስቲ በያላችሁበት ተወያዩበት፡፡
  3. የምእራቡ አለም ዴሞክራሲ ኢትዮጵያን ሊረዳት የሚቻለው ሰላም ለማስፈን፣ብሔራዊ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ ምድር እንዲዘጋጅ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን ይገባዋል፡፡
  4. በግጭቶችና ጦርነቶች ምክንያት (ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረውበት) ኢትዮጵያን የድሆች ደሃ ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ስለሆነም የምእራቡ አለም በኢትዮጵያ አሸባሪነት እንዲሰፍን የሚረዱ ሀገራትን መቆጣጠርና ሃይ ማለት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በተለይም የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትን በመሳሪያ እና ትጥቅ የሚረዱ ሀገራትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መከልከል አለበት ፡፡ ኢትዮጵያ የጦርነት ቋያ ብትሆን የምእራቡ አለም ምኞትና ፍላጎትም ቢሆን ገቢራዊ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
  5. ታሪክ እንደሚያስተምረን የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ድርቅና ችጋርን ወደ ፖለቲካ መሳሪያነት፣ለራሱ ለድርጅቱ መጠቀሚያነት እንደሚቀይረው ነው፡፡ የትግራይ ነጻ አውቺ ድርጅት በትግራይ ህዝብ ድርቅና ጠኔ መጠቃት ለብዙ ግዜ እንደነገደ ዛሬም በሰብዓዊ ጋሻነት ስለመጠቀሙ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የምእራቡ አለም በተለይም ህዝቡን በከባድ ሀዘን ውስጥ በመጣል መጠቀሚያ በማድረግ የምእራቡን አለም ለማሳሳት ችሎታ አላቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በውሸት ተካኑ ሰዎች ስለሆኑ ነው፡፡ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ራሳቸው ውሸት ይመስሉኛል፡፡ ስለሆነም የምእራቡ አለም የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት አመራሮችን ውሸት የሚቀበሉ ከሆነ የኢትዮጵያ ስቃይና መከራ የሚራዘም ይመስለኛል፡፡
  6.  በኢትዮጵያ ምድር አንድ አይነት ጦርነት ወይም ግጭት ወይም ሌላ መከራ ሲከሰት ጉዳዩን አጋነው የሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃን አሉ፡፡ እነኚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም የምእራቡ አለም በኢትዮጵያ ምድር ለሚከሰቱ ሁነቶች ሚዛናዊ መረጃ እንዲቀበል፣ኢትዮጵያን በተመለከተ የውሸት መረጃ እንዳይቀበል እንማጸናለን፡፡ በአጭሩ ግራና ቀኙን አስተውሎ ( ከመንግስትና ተቀናቃኝ ሀይሎች አኳያ እንዲመዝን እንማጸናለን፡፡)
  7. በሚያሳዝን ሁኔታ የአለም አቀፉ ልዩ ወኪል ሳይቀር የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት የሚያቀርብላቸውን የውሸት ድሪቶ ብቻ በመቀበል ኢትዮጵያን በአለም አደባባይ ለማሳጣት ሞክሯል፡፡ አሁን ይህን ከባድ ስህተት በማረም ሚዛናዊ እንዲሆኑ እንማጸናለን፡፡ በማእከላዊ መንግስትም ሆነ በትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በህሊና ሚዛን ላይ ሆኖ በማጣራት ለሰብዓዊ መብት መከበር እንዲቆሙ ታሪክ ግድ ብሏቸዋል፡፡
  8. በምእራቡ አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ግዜ በላይ የምእራቡን አለምና የተባበረችውን አሜሪካ  ከኢትዮጵያ ጋር እንደ ድልድይ ሆነው ማገናኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ግን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጎሳና እምነት አጥር ሳይገድበው መገናኘት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ የታላቁ አባይ ግድብ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በምእራቡ አለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መተባበር ግዴታው ነው፡፡በተረፈ በጎሰኝነት ስሜት መሰባሰብ እንደማበጀን መታወቅ አለበት፡፡
  9. የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ሰትራቴጂክ እቅድ በማውጣት ከአፍሪካው ቀንድ ሀገራት ከአፍሪካ ህብረት ዋነኛ አባል ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያጠናክር በአክብሮት አስታውሳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አኳያ ከግብጽና ሱዳን ጋር ላለው እሰጥ እገባ በአፍሪካ ህብረት ዳኝነት ይታይ ማለቱ በብዙ ኢትዮጵያውያን ቅቡልነት አስገኝቶለታል፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ አቋም ከአፍሪካ አባል ሀገራት አኳያ ያላትን ግንኙነት ያሻሽልላታል ብዬ አስባለሁ፡፡ የአፍሪካ ህብረት ዳኝነት በተመለከተ ከፍትህ ያዘነብላል ብለን ባንገምትም የምእራቡ አለም ተጽእኖ ግን በግዴለሽነት የሚታይ ስላልሆነ አሁንም ቢሆን የተማሩና ኢትዮጵያን በእውነት መሰረት ላይ ሆነው የሚወዱ ኢትዮጵያዊ ተከራካሪ ምሁራንን መንግስት እንዲጋብዝ  ጸሃፊው ያስታውሳል፡፡
  10.  የምእራቡ አለም በተለይም በተባበረችው አሜሪካ አጋፋሪነት እየተመራ በኢራቅ፣ሶሪያ፣አፍጋኒስታን፣ የታላቁ ብሮዝ ቲቶ ሀገር የነበረችውን ዩጎዝላቪያ  ወዘተ ወዘተ የፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ ከገባ በኋላ ሀገራቱን የደም ጎርፍ እንዲጎርፍ አደረገ እንጂ ሰላምን አላመጣላቸውም፡፡ ሀገራቱን የአክራሪ ጽንፈኛ ቡድኖች መራኮቻ አደረጋቸው እንጂ ያመጣው ፋይዳ አልነበረም፡፡ ሀገራቱን ምድራዊ ሲኦል አደረጋቸው እንጂ ገነት አልፈጠረላቸውም፡፡ ምስጋና ለአምባገነኖችና በየሀገራቱ የበቀሉ የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች ይሁንና የምእራቡ አለም ወታደሮች ቀዳዳ ስላሚያገኙ ወደየሀገራቱ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ በመግባት ያሻቸውን ለመስራት አልተቸገሩም፡፡ በሶማሊያ አሜሪካ ወታደሮች፣ በማሊ የፈረንሳይ ወታደሮች፣በኮንጎ በአብዛኛው የምእራቡ አለም ወታደሮችና የሌሎች ሀገራት ወታደሮች ጣልቃ መግባት ሰላምን እንዳላመጣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰከነ መንፈስ መመርመር አለብን፡፡ በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በትምህርት ጥራት፣ በኑሮ ደረጃ ወዘተ ወዘተ በላቀ ደረጃ ላይ ትገኝ በነበረችው ኩባ የውስጥ ጉዳይ ላይ የተባበረችው አሜሪካ ጣልቃ በመግባት በምታደርገው መሰሪ ተንኮል ተነሳ ኩባን እንዳልጠቀማት በመረዳት እኛ ኢትዮጵያውያን በመስማማት በመተባበር መንፈስ በራችንን ለውጭ ሀይላት መግቢ ቀዳዳ መክፈት የለብንም፡፡ ይህን ለማድረግ ከመከራ ለመማር መጠበቅ የለብንም፡፡ ከፊደልም እንማር፡፡ ከዚህ ባሻግር ለእኔ ብቻ፣ እኛ እና አነርሱ፣ የጨቋኝና ጨቋኝ ትርክት ከሆነው  የጎሳ አስተሳሰብ በፍጥነት መውጣት አለብን፡፡ ጎበዝ የምንድነው ከሆነልን በሰውነት ደረጃ በመቆም ካልሆነልን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ደረጃ ላይ ስንወጣ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አጠገባችንም ሆነ ከሩቅ ሆነው እኛ በጎሳ ተከፋፍለን ስንጫረሰ ለማየት እና ጣልቃ ለመግባት ላሰፈሰፉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በራችን መከፈት የለበትም፡፡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተፈጠረውን ጦርነት በቅድሚያ በሰለጠነ መንገድ፣በወንድማማችነት መንፈስ በእውነተኛ ሽማግሌዎች አመሃኝነት በውይይት መፍታት አለብን፡፡ በቅርቡ የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ፕሬዜዴንት ለህዝባቸው ያስተላለፉት መልእክት ህዝባቸው ለአንድነት እንዲነሳ ጥሪ አስተላልፈው ነበር፡፡ የናይጄሪያው ፕሬዜዴንት በበኩላቸው ከአፍሪካ ሀገራ ሁሉ በህዝብ ቁጥር ሁለተኛ የሆነችው ሀገር ኢትዮጵያ አንድነቷን እንድትጠብቅ የወዳጅነትና ወንድምነት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያንም ብንሆን ከገባንበት ጥልቅ ጉድጓድ መውጣት የምንችለው በአንድነት፣በአንድነት፣እና አሁንም በአንድነት መንፈስ ነው የሚለውን መልእከት በታላቅ ትህትና አስተላልፋለሁ፡፡
  11. በመጨረሻም በኢትዮጵያ ምድር ለምትኖሩና ከኢትዮጵያ ውጭ እንደ ጨው ዘር ለተበተናችሁ ኢትዮጵያዊ ወንድሞች የማስታውሰው ጉዳይ ቢኖር ዛሬ የደረሰንበት ግዜ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማቆየት ደረጃ ላይ መሆኑን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከተከፋፈለች ማንም የሚጠቀም የጎሳ ወይም እምነት ቡድን የለም፡፡

 

ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዜአብሔር ትዘረጋለች

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

  1. Finally, for Ethiopians within and outside the country, the current foremost priority is to preserve Ethiopia as a country. No single ethnic or faith group or elite will benefit from a Balkanized Ethiopia.

Ethiopia shall prevail!!!

May 8, 2021

Filed in: Amharic