ጦርነትን በቀጥታ ስርጭት…
ፍትሕ መጽሔት
ዓለም የደረሰበት ሥልጣኔና የቴክኖሌጂ ምጥቀት አያሌ ጉዳዮችን ማቅለሉ እሙን ነው፡፡ ከእነዚህ መሀል ዲጂታል ሚዲያው አንዱ ነው፡፡ ፌስ-ቡክ፣ ቲውተር፣ ዩ-ቲዩብ፣ ኢንስታግራምና የመሳሰሉት ፈጣን መረጃዎችን በቀላሉ በማሰራጨት እጅግ ጠቃሚ ‘ፕላት ፎርም’ ሆነዋል፡፡ በየትኛውም የፕላኔታችን ጫፍ ያሉ የሰው ልጆችን በማቀራረቡ ረገድም ወደር አይገኝላቸውም፡፡ ይሁንና፣ እነዚህ የማኀበራዊ ሚዲያ አውታሮች፣ የጠቀሜታቸውን ያህል አውዳሚነታቸውም እጀግ የበዛ እንደሆነ በተለያየ አገር ክሱት ከነበሩ ችግሮች በበቂ መረዳት ይቻላል፡፡ በተለይ ችግሮቹን የከፋ የሚያደርጋቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አልቦ-ተቋማት እና ድሃ አገራት ቀርቶ፤ ኃያላኑም የሚቋቋሙት አለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህም፣ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው አሸናፊ ሆነው እንዲወጡ የሀሰት ዜናዎችን እና መረጃዎችን በማሰራጨት ጣልቃ-የገቡ የውጭ አገራት እንዳሉ ተጠርጥሮ፣ ምርመራ ሲካሄድ የነበረበትን ጉዳይ በአስረጂነት ማስታወሱ በቂ ነው፡፡
ኢትዮጵያም የእዚህ ችግር ሰለባ እየሆነች ለመምጣቷ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አለቅጥ እየናረ በመሄዱ አያሌ አገራዊ ኪሳራዎች፣ የእርስ-በርስ ግጭቶች፣ የዜጎች መፈናቀል እና የመሳሰሉት ጉዳቶችን አድርሷል፡፡ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሕወሓት የቀሰቀሰው ጦርነት ደግሞ ይዘቱንና ቅርጹን ከማስፋቱ በዘለለ፤ አውዳሚነቱንም የበለጠ ጨምሮታል፡፡ ይህም ሆኖ፣ በማኀበራዊ ሚድያ እየተፈጠረ ያለው ችግር ከተወሳሰበበት ገፊ-ምክንያቶች አንዱ የመንግሥት ኃላፊዎችም ተሳታፊ በመሆናቸው እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የሆነው ሆኖ፣ የትግራዩን ጦርነት የከፈተው ሕወሓት ከስር-ሰደድ አፍራሽ እና አሸባሪ ባህሪው አኳያ፣ የሚያሰራጨው የሀሰት ወሬዎች የሚጠበቁ መሆናቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዋንኛው አሳሳቢ ጉዳይ የመንግሥት ተወካዮች፣ በተለይ የፀጥታ መዋቅሩን የሚመሩ የጦር መኮንኖች፣ ስልክ ለደወለላቸው አክቲቪስት እና ዩቲዩበር ወታደራዊ መረጃዎችን የመዘርገፋቸው ልማድ ነው፡፡ መቼም ይህ ድርጊት ከወታደራዊ ዲስፕሊን ያፈነገጠ፣ አገሪቱንም ወዳላስፈላጊ ችግር የሚገፋ፣ የተቋሙንም ገጽታ የሚያጠለሽ መሆኑ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በተለይ፣ በእንዲህ ዐይነቱ ግዙፍ ጦርነት ወቅት የመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ የክልሎች ልዩ ኃይል አዛዦች ጥብቅ ወታደራዊ ምስጢሮችን ሳይቀር፣ በዘፈቀደ የሚያሰራጩበት መንገድ በአጭር ካልተቀጨ፣ ለማይታረም ስህተት ሊዳርግ የሚችልበት እድል ከፍተኛ ነው፡፡
በየትኛውም ጦርነት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ፡- ‹እገሌ የተባለ ጄነራል ከግንባር ነገረኝ›፣ ‹እገሌ የተባለ ኮሎኔል ዛሬ ምሽት ልናጠቃ ነው አለኝ›፣ ‹እገሌ የተባለ አዛዥ ከምሽግ ደወለልኝ…› እያሉ አስከፊውን ጦርነት፣ በ“ቀጥታ ስርጭት› ለመዘገብ የሚደረገው እሽቅድድም እጅግ አደገኛ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ላይ መላው ሠራዊቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት የታዘብነው፣ የሠራዊት እንቅስቃሴና ስምሪት ሳይቀር፣ በፌስ-ቡክ እየተጻፈ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ ነው፡፡
እንዲህ ዐይነት ድርጊት የሚፈጽሙ አዛዦችም ሆኑ የሠራዊቱ አባላት በወታደራዊ ሕግ ሊያስጠይቅ የሚገባ ትልቅ ወንጀል መሆኑን መርሳት የለባቸውም፡፡ ማዕከላዊ መንግሥቱም ሆነ የተቋማቱ ኃላፊዎች በዚህ ተግባር የሚሳተፉት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እያደረጉ ተመጣጣን ርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ “ፍትሕ መጽሔት” ታሳስባለች፡፡
በሌላ በኩል፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን (ከመንግሥትም ሆነ ከሕወሓት ጎን የቆማችሁ) ከዚህ ዐይነቱ አገር አፍራሽ እና ሕዝብ አስጨራሽ የሀሰት መረጃ ማሰራጨት ተግባር ትቆጠቡ ዘንድ ይመከራል፡፡ በሁለቱም በኩል የሚወጡ ወሬዎች፣ ሰፊው ሕዝብ የሚወግነውን ቡድን ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጣ ጫና እንዳያደርግ የሚያዘናጉ ናቸው፡፡ እናም እስከ አሁን ከደረሰው አስከፊ ጉዳት የበለጠ ከመፈጠሩ በፊት፣ ሁኔታውን ከደም አፋሳሽ ውጪ ባሉ መንገዶች የመፍታት አማራጮችን መፈተሽ የሚቻለው፣ የሀሰት ወሬዎችን ከማሰራጨት ስንታቀብ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
በአጠቃላይ፣ የሠራዊቱ እና የልዩ ኃይሎች አዛዦች፣ ውድ ህይወታቸውን ገብረው ሕግ በማስከበር ዘመቻ የተሰለፉ ወንድም-እህቶችን ለአደጋ የሚያጋልጥ መረጃ ለአክቲቪስቱም ሆነ ለዩቲዩበር አሳልፎ ከመስጠት ልትታቀቡ ይገባል፡፡ መረጃዎቹ በእንዝላልነትና በምንግዴ የሚሰጣችሁ ወገኖችም፣ ጉዳቱን ሳታመዛዝኑ ከማሰራጨት ትቆጠቡ ዘንድ ይመከራል፡፡
በየትኛውም አገር ጦርነት እንደ እግር ኳስ ጨዋታ በቀጥታ ስርጭት ሲተላለፍ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ እንዲህ ዐይነቱ ድርጊት ከማሸለም ይልቅ፤ ለአገርም ሆነ ለሠራዊቱ ኪሳራ የሚያመጣ ነው፡፡ እናም ሁላችንም ካልተረጋገጠ የ“ሰበር መረጃ” ስርጭትም ሆነ በውጊያው ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ መረጃዎችን ከመልቀቅ ልንታቀብ ይገባል፡፡
ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግሥት፡- ዓለም ከደረሰበት የቴክኖሎጂ ውጤት አኳያ፣ ወደ ግንባር የሚላኩ አዛዦችም ሆኑ ተዋጊዎች የእጅ ስልክ ይዘው እንዳይሄዱ ቢደረግ ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ በእጅ ስልክ ውስጥ ያለ “ሲም ካርድ”፣ በራስ ላይ የተጠመደ ፈንጂ ከሆነ ውሎ-አድሯልና፡፡ ጦርነትም ቢሆን፣ ጠንካራና ተለዋዋጭ ኮድ ባለው የመገናኛ ሬዲዮ እንጂ፤ በሞባይል ተመርቶ እንደማያውቅ ሊዘነጋ አይገባም፡፡