” ህዝብ እውነቱን አውቆ ለምን በጋራ መፍትሄ አንፈልግም ? “
የኢሳት ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ
መከላከያ ሰራዊት ኮረምን እና አላማጣ ከተማን ለቆ ሲወጣ ለምን ለቆ ወጣ የሚል ጥያቄ ሲነሳ ስልታዊ ማፈግፈግ ነው ተባለ። ሰራዊታችን ቆቦ ከተማ ሆኖ የሽብርተኛው ቡድን ዞብል እና ጋቲራ የተባሉ ቀበሌዎችን ሲይዝ ይህም ወታደራዊ ስትራቴጂ ነው ተባለ።
ሰሞኑን ደግሞ ራያ ቆቦ ከተማን ፣ አራዱምን አቧሬን እና ሮቢትን አስረከብን። ዛሬ ደግሞ ከወልዲያ 25ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን ጎብዬ ከተማን ለመያዝ በር ላይ ቆመዋል። ይህስ ሲባል ስልታዊ ማፈግፈግ ተባለ።
ጥሩ ይሁን ። ግን ስልታዊ ማፈግፈግ ሲባል ታንክ እና ሌሎች ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ጥሎ መውጣትንም ይጨምር ይሆን ?
መከላከያ ሰራዊታችን እና ሲቪሉ እየተደበደበ ያለው በስልታዊ ማፈግፈግ በሚል ጥለነው ባፈገፈግነው መሳሪያ ነው።
ስልታዊ ማፈግፈግ ምን ያህል ኪሎ ሜትር ነው? እስካሁን ከሰባ ኪሎ ሜትር በላይ አፈግፍገናል። ሰራዊታችን እዚህ ደርሷል እዚያ ገባ የሚለው ምኞቱ ደስ ይላል። መሬት ላይ ያለው ግን የምኞታችንን ያህል አይደለም።
ይህንን ደግሞ ሕዝቡ እንጂ ያላወቀው መንግስት እና ታጣቂው ቡድንም ምን እየሆነ እንደሆነ ያውቁታል።
ባለቤቱ የሆነው ህዝብ እውነቱን አውቆ ለምን መፍትሄ በጋራ አንፈልግም ?
ይህንን የፃፍኩት በስፍራው እየሆነ ያለውን በማየት ነው።
ከኢሳት አዲስ አበባ ማኔጅመንት የተሰጠ መግለጫ
የመስሪያ ቤታችን ባልደረባ የነበረው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ቤተሰብ ለመጠየቅ 4 የስራ ቀናትን አስፈቅዶ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አቅንቷል።
ይሁን እንጂ በስም የተጠቀሰው ጋዜጠኛ በግል የፌስቡክ አካውንቱ ሙያዊ ስነምግባርን ያልተከሉ መረጃዎችን እያሰራጨ መሆኑን ደርሰንበታል።
በመሆኑም ጋዜጠኛው በፈቃድ ላይ መሆኑን እና በግል የፌስቡክ ገፁ የሚያሰራጨው መረጃ ኢሳትን የማይወክልና የግሉ ሀሳብ መሆኑን እንድታውቁት የኢሳት ማኔጅመንት ይህንን አጭር መግለጫ ማውጣት አስፈልጎታል።
ክቡራን ደንበኞቻችንም ከሀሰተኛና ካልተረጋገጡ መረጃዎች እራሳቸውን እንዲያቅቡ እናሳስባለን።