ወንድወሰን ተክሉ
*…. አንድ-የማይጸብሪ አድርቃይ ግንባር ምስጢር -እውነተኛ ታሪክ
*… «የብአዴን ባለስልጣናት በ17ፓትሮል ተግተልትለው ከሸሹ በኃላ አድርቃይ በጠላት እጅ ወድቃለች»
ፋኖ አለባቸው ሲሳይ ከደባርቅ
« በመጀመሪያ የአካባቢው ባለስልጣናት አቶ ብርሃኑ ጣምያለው፣ አቶ የለአለም ይስማ አድርቃይ ከተማ በወያኔ ከባድ መሳሪያ ልትደበደብ ነው በሚል በይፋ ሲለፍፋ ህዝቡ በመሸበር ግልብጥ ብሎ ለመውጣት ትርምስ ማድረግ ጀመረ፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ሰዓት የብአዴን ባለስልጣናት በ17 ፓትሮል መኪና እየተንጋጉ አድርቃይን ለቀው ወደ ደባርቅ ሸሹ፡፡ በዚህን ጊዜ ፈንጠር ብሎ ያለው መከላከያ እና እኛም እያየን ወያኔዎች በአስፋልት መንገድ ያለአንዳች ጦርነት እየተዝናኑ ከተማዋን ተቆጣጠሩ..»በማለት ፋኖ አለባቸው ሲሳይ ቅዳሜ ምሽት ላይ ከደባርቅ ደውሎ አረዳኝ፡፡
ከደባርቅ የተደወለልኝን የአለባቸውን ስልክ ከማንሳቴ በፊት ቀደም ብሎ ከራያ ግንባር ከቆቦ ያገኘሁትን አሁናዊ ሁኔታን እያብላላሁ ያለሁበት ሰዓት በመሆኑ የስክክ ንግግሩን እንደቃጨሁ የተሰማኝን ጥልቅ ግን ኃያል የሆነ ምስቅልቅል ስሜት መግለጽ ይቸግረኛል፡፡ ንዴት?ቁጭት? ሀዘን? እልህ?? ምን ይደረግ?? እንዴት ነው የህዝባችንን እይታ ማንቃት እሚቻለው??? እንዴትስ ሆኖ ነው አንዳንድ ለአማራ ህልውና እታገላለሁ የሚሉ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን አስቃቂ እውነታን እንዳልተፈጠረና እንደሌለ በመቁጥር ሁሉም በአንድ መንግስት መራሹ ዘመቻ መስመር ውስጥ መሰለፍ አለበት እያሉ ሊያስተጋቡ ቻሉ እና ወዘተ አይነት ስሜቶችና ጥያቄዎች በእጅጉ ውስጤን አመሱት፡፡ በተለይ በተለይ የአማራ ህዝብ ህልውና የተጋረጠበትን ውጫዊ ሳይሆን ውስጣዊ የጠላት ኃይል አደጋ ምን ያህል አስከፊ መሆኑን ማየትና ማወቅ በእጅጉ እረፍትና ውስጣዊ ሰላምን የሚነሳ ሆኖብኝ አየሁት፡፡
አንባቢ ግር እንዳይል የአድርቃይ፣ማይጸብሪ፣አላማጣ፣ኮረም፣ዞብል፣ አበርገሌና መሰል ስፍራዎች በትህነግ ኃይል እጅ የመግባቱ ጉዳይ አይደለም ይህንን አይነት ስሜት ሊፈጥርብኝ የቻለው-በአንጻሩም የተጠቀሱት ስፍራዎች በጣላት እጅ የገቡበትን መንግስታዊ መሰሪ ሴራን ማወቁና በአንጻሩም የአማራው ድምጽና ተወካይ ነን የሚለው ፖለቲካ ክፍል ይህንኑ መሰሪ የሆነን መንግስት አጋር አድርጎ በአንድነት ሆነን ጦርነቱን እንዋጋ እያሉ ያሉበትን ጩህትና ቅስቀሳን አሰብና መለከትከት አድርጌ ነው ይህ ዘርፈ ብዙ ምስቅልቅል ስሜት ሊሰማኝ የቻለው፡፡
የአማራን ህዝብ እወክላለሁ ባዩ አዴፓ ተብዬው የዚህ ሴራ ዋና ተባባሪ ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆኖ መገኘት በአንድ በኩል -በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚ ነን የሚሉን እንደነ አብን አዴኃንና በዳያስፖራ ያለው የአማራ አንቂ ፖለቲከኛና አንዳንድ ጋዜጠኛም ጭምር «ይህንን ግዜ ከመንግስት ጋር ያለንን ልዩነት ወደ ጎን ትተን በአንድ በተባበረ ክንድ በአንድነት ጦርነቱን እንዋጋለን» እያሉ ማስተጋባትና አቋም መያዝን በሌላ ወገን እያየሁ ግን ከራያ ግንባር እስከማይጸብሪ ግንባር ድረስ እየተፈጸመ ባለ እጅግ አደገኛና መሰሪ መንግስታዊ ሴራና ሳቦታጅ ጦርነቱ እየተካሄደ መሆኑን ማወቅ እማይረብሸው ሰው ካለ የሴራው አካል የሆነን ብቻ ነውና የህዝባችን ህልውና በከባድ አደጋ ላይ መውደቅ በእጅጉ ውስጣዊ ሰላሜን የነጠቀ ሆኗል፡፡
ለመሆኑ የራያን ጉዳይ ያዝ አድርገን በማይጸብሪና አድርቃይ ግንባር ምን ተፈጠረ ወይም የትህነግ አሸናፊነት እንዴት ሊፈጸም ቻለ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ እነሆኝ የሚል ነው፡፡
የዜና ታሪክ መረጃ ምንጭና ባለቤት ፋኖ አለባቸው ሲሳይ ለቀናት ሲካሄድ በነበረው የማይጸብሪ ግንባር ላይ ከተሰለፉት የፋኖ ተዋጊዎች ውስጥ አንዱ የሆነ ሲሆን ትህነግ ከተከዜ ጀምሮ እንዴት እየተጓዘች ዛሬ አድርቃይ መድረስ እንደቻለች የነገረኝ እሱም ወደ ኃላ አፈግፍጎ ካለበት ደባርቅ ከተማ መሆኑን እየገለጽኩ ወደ ታሪኩ እሸጋገራለሁ፡፡
*.. 1ኛ- በማይጸብሪ ያለው የወገን አሰላለፍን በተመለከተ
በማይጸብሪ ግንባር በተከዜ ወንዝ ላይ ባለው የመጀመሪያ ምሽግ ላይ መሽጎ ጠላትን ሲጠባበቅ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ሲሆን ከጎኑም የአማራ ፋኖ እና የአማራ ሚሊሺያም ስፍራ ስፍራቸውን ይዘው ጎን ለጎን ተሰልፈው ባሉበት ሁኔታ የመከላከያ ሰራዊቱ ግን ከእነዚህ የግንባር ላይ ተሰላፊ ምሽጎች ጀርባ እጅግ በራቀ ርቀት ከእኛ ጦር ጀርባ ካትሞ ያለበት አሰላለፍ መሆኑን ልብ እንድትሉልኝ ያስፈልጋል፡፡
ይህ ማለት ድንበር ጠባቂውና ከህወሃት ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ የተዋጋውና እየተዋጋ ያለው ሰራዊት የእኛው የአማራ ልዩ ኃይል የአማራ ፋኖና የአማራ ሚሊሺያ ብቻ እንጂ መከላከያው ከበስተጀርባ ሆኖ ከመመልከት በስተቀር ምንም አይነት ውጊያ ፈጽሞ ያላደረገ ተመላች ሰራዊት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
* 2ኛ- የጦርነቱን ገጽታ በፍጥነት እየለወጠው ያለው የጦር መሳሪያ አይነትን በተመለከተ
ወያኔ እስካሁን ከልዩ ኃይላችን ፋኖ እና ሚሊሺያዎቻችን ጋር ፊት ለፊት ገጥማ በመዋጋት አሸንፋ ያስለቀቀችው አንድም ስፍራ የለም፡፡ በአንጻሩም እሷ በርቀት ሆኗ በታጠቀችው መድፍ ዲሽቃ ሞርታ ቢ ኤም ደብሊው ባዙቃና ወዘተ ከባድ መሳሪያዎች ተጠቅማ የወገኖቻችንን ምሽግ ስትቀጠቅጥ ተመሳሳዩን መሳሪያ ያለው መከላከያው -አንድ እራሱ የአጸፋ ሽፋን መስጠት ሲገባው የማይሰጥ-ሁለት እራሱ መተኮስ ባይፈልግ መሳሪዎቹን ግን ለልዩ ኃይሉ በመስጠት እንዲጠቀምበት ማድረግ ሲገባው ባለማድረግ ዝም ብሎ የወያኔን ከባድ መሳሪያ ድብደባን ይከታተልና ድንገት ብድግ ብሎ ልዩ ኃይሉ ፋኖና ሚሊሺያው እንዲያፈገፍጉ በማዘዝ ምሽጎቻቸውን ያስለቅቃል፡፡ ይህ በተፈጸመ ቅጽፈት ወያኔ ሰተት እያለች በመግባት ምሽጎቹን ከተሞቹን የመቆጣጠሩን ተግባር ትፈጽማለች፡፡
«ወያኔ የተከዜን ወንዝ እየተሻገረች ባለችበት ሰዓት ልዪ ኃይላችን ተኩስ ይከፍታል፡፡ እኛ ከልዩ ኃይሉ ኃላ ፈቀቅ ብለን መሽገን ስለነበረ ተኩሱን እያየን የተከዜ ወንዝ የወያኔ መቀበሪያ መሆኑ ነው እያልን ሳለ ድንገት የልዩ ኃይሉ አዛዥ ነው የተባለው ኮማንደር አርዓያ ተኩስ አቁሙ ብሎ በማዘዝ ልዪ ኃይሉን ያስቆማል፡፡ በዚህም ፋታ ያገኘችው ወያኔ መከላከያው በሰራላት አዲስ ተገጣጣሚ ድልድይ እየተንፈላሰሰች ከተሻገረች በኃላ ወዲያውኑ መድፍና ከባድ መሳሪያዎቿን ጠምዳ በርቀት የልዩ ኃይሉን ምሽግ የሚሊሺያውንና የእኛን የፋኖን ምሽግ ክፉኛ መደብደብ ጀመረች፡፡ በዚህን ግዜ መከላከያውና የልዩ ኃይሉ አዛዥ ኮማንደር አርዓያ ሁላችንም ስፍራችንን ለቀን እንድናፈገፍግ አስገዳጅ ትእዛዝ ይሰጣሉ፡፡
ልዩ ኃይሉ ግን ይህንን ትእዛዝ አልቀበልም በማለት እርሰበርስ እስከመታኮስና መዋጋት ደረጃ ይደርሳል፡፡ በርከት ያለ ልዪ ኃይል በዚሁ የእርሰበርስ ውጊያ ከተሰዋ በኃላ ምሽጋችሁን ልቀቁ ያለው አዛዥ ወገን አሸንፎ የልዪ ኃይሉ ሰራዊት እንዲወጣ ይደረጋል ፡፡ በወጣው ልዩ ኃይላችን እግር ተከትላ ነው ወያኔ ማይጸብሪን ለመቆጣጠር የቻለችው…» በማለት ፋኖ አለባቸው ሲሳይ የተናገረው፡፡
መከላከያውና የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች እጅግ እርሰበርስ በመናበብ በመመካከርና በመግባባት የሚሰሩ ሲሆን ይህ ቅንጅታዊ ስራቸው ግን እየተዋጋ ያለውን የአማራን ተዋጊ ኃይልን በሚደግፍ መልኩ ሳይሆን በሚያስበላ መልኩ ሆኖ መገኘቱ በእውነቱ ለመናገር በእጅጉ ያንገሸግሻል፡፡
* በማይጸብሪና በአድርቃይ አካባቢ ያለው የ24ኛ ክፍለ ጦር እና የአማራ ተዋጊ ኃይሎች ሁኔታ
«በማይጸብሪ ባለው ማይለሁ ተራራ ላይ የመከላከል ምሽግ ለመያዝ በሟይቧ ወንዝ ትይዩ ስፍራ ስፍራ እንድንይዝ ሆነ፡፡ የ24ኛ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ የሆነው ኮ/ል ታሪኩ እንደ አጋጣሚ እንደ እኛው የአማራ ልጅ ስለሆነ ቢያንስ ባይረዳንና ባያግዘን እንኳን አያስመታንም ብለን ሁላችንም በማመን ማይጸብሪን በመልሶ ማጥቃት ለመያዝ እየተዋጋ ላለውና ሰባት ኪሎ ሜትር ያህል ቀርቦ ያለውን ልዩ ኃይል ለመርዳት እኛ ፋኖዎች በማይላ ተረራ ላይ አዘገጃጀት እያደረግን ሳለ በሚደንቅ ሁኔታ ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ላይ ይህንን የአማራ ልጅ የሆነውን የጦሩን አዛዥ ኮ/ል ታሪኩን ከላይ በመጣ ትእዛዝ ተጠርተሃል ብለው በማንሳት አዲስ አዛዥ መደቡ፡፡ አዲሱ አዛዥ ወዲያውኑ በኦሮሚኛ ቋንቋ በመገናኛ ሲነጋገር ሰማነው፡፡ ሰራዊቱንም በማንቀሳቀስ በዚያው ለሊት አብሮን ከመሸግንበት ምሽግ አስለቅቆ ወደ ኃላ እንዲያፈገፍግ አደረገው፡፡ ይህ ከሆነ ሰዓት በኃላ መረጃው የደረሳት መሆኑን በሚያስታውቅ ሁኔታ ወያኔ ንጋት አስራ ሁለት ሰዓት ላይ በመድፍና ከባድ መሳሪያ የጠመደችን እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ጥይታችን እስኪያልቅ የሰዋነውን እየሰዋን ስንዋጋ ዋልን፡…»በማለት ፋኖ አለባቸው በግንባር እየሆነ እና እየተፈጸመ ስላለው መንግስታዊ መሰሪ የሆነ አሻጥርና ሸፍጥ በምሬት ይናገራል፡፡
ግን ለምን????
ለምንድነው አቢይ መራሹ የብልጽግና መንግስት (ዋነኛውን አዴፓ ተብዬውንም ጨምሮ) ይህንን ያህል ጸረ አማራ ሴራ አሻጥርና ክህደትን ለመፈጸም የፈለገው ??
እሺ አሻጥሩና ሳቦታጅ በሉት ክህደት በማይጸብሪ ግንባር ብቻ ነው እየተፈጸመ ያለው ወይንስ በራያ ግንባርም እየተፈጸመ ያለ ነው??
* ሁለት-ከራያ ግንባር ጥቂት የእውነተኛ ታሪክ ጭልፍታ፦
የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ከትንሽ እስከትልቅ ወንድ ሴት ሳይል እራሱን ለውጊያ አዘጋጅቶ በቅርብ ርቀት የሚሰማውን የተጧጧፈ ተኩስ ድምጽ እየሰማ በመጠባበቅ ላይ ባለበት ሁኔታ የሚያስተጋባው ድምጽ በመረረ ምሬታዊ ንዴት የተሞላ ሆኖ ይታያል፡፡
በንግድ ስራ ላይ ተሰማርቶ ቤተሰቡን እያስተዳደረ ያለው ይሁኔ አለነ የንግድ ቤቱን ዘግቶ እራሱን ለጦርነት ያዘጋጀ መሆኑን ሲናገር ምሬት በተቀላቀለ ሁኔታ ነው፡ «…መከላከያው እዚሁ አፍንጫችን ስር እያለ ነው የእኛ ልዩ ኃይል ብቻውን እያለቀ ያለው፡፡ ልዩ ኃይላችን አልቆ ከተማችንን በነጻነት ይረከቧታል ማለት ፍጹም ዘበት ነው፡፡ ሁላችንም እንደ ህዝብ ልንዋጋ ወስነን ተዘጋጅተናል» ሲል ለምን እራሱን ለውጊያ እንዳዘጋጀ ይናገራል፡፡
ይሁኔ የምሬቱን ምንጭ መንስኤ ሲናገር ደግሞ « ከኦሮሚያ መጡ የተባሉት ተዋጊዎች አንዳችም ውጊያ ሳያደርጉ ሰተት ብለው ወደ ትህነግ በመግባት ትጥቅና መሳሪያቸውን ካስረከቡ በኃላ ባዶ እጃቸውን ወደ እኛ ሲመለሱ መከላከያው ህዝቡ ጉዳት ያደርስባችኃል በማለት ሰብስቦ ካምፕ በማስገባት እየጠበቃቸው ነው፡፡ ከኦሮሚያ ድረስ ተንጋግተው የመጡት በእንዋጋለን ስም ለጠላታችን ትጥቅና መሳሪያቸውን ለማስረከብ ነው ??» በማለት በኦሮሚያ ልዩ ኃይል በኩል ስለተፈጸመው ትጥቅና መሳሪያን አስረክቦ የመመለስን ጉዳይ በምሬት ይናገራል፡፡
በቆቦ ሆስፒታል ከሚያገለግል የህክምና ባለሙያ ያገኘሁት መረጃ «ሆስፒታሉ ከኦሮሚያ በመጡ ልዪ ኃይልና በመከላከያው አባላት ቁስለኞች የተሞላ ሆኖ ሳለ ከመድሃኒት ጀምሮ ሁሉንም ነገር የሚሸፍነው የአማራ ክልል ብቻ መሆኑ በሆስፒታሉ ውስጥ የመድሃኒትና መሰል አስፈላጊ ነገሮች ከፍተኛ እጥረት እንዲገጥመው አድርጎታል» በማለት የፌዴራል መንግስቱን ባይተዋራዊ ሚናን ይገልጻል፡፡
የቆቦ ከተማ ህዝብ አብዛኛው ቤቱን ለቆ ወደ ወልዲያና አካባቢው ተሰዷል..…
(ይቀጥላል)