>
5:33 pm - Friday December 5, 9952

የተሳካ የኦሮሙማ እቅድ:- (ዘመድኩን በቀለ)

የተሳካ የኦሮሙማ እቅድ:-

የዐማራና የትግሬ ህዝብ በጦርነት፣ በረሃብ፣ በበሽታ፣ በስደት… እየተቀነሰ ነው…!!!
ዘመድኩን በቀለ

*…. በአፋር ግንባር አንድ ፍሬ ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች በመከላከያ ሠራዊቱ ተጨፍጭፈው፣ ተጨፍጭፈው በየተራራው ተረፍርፈው ወድቀው የሚያሳይ ቪድዮ ደርሶኝ አይቻለሁ
… የሃገር መከላከያ ሠራዊቱ እንደሚለው ከሆነ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍሎች ከህወሓት ጋር በማደርገው ጦርነት በውጊያው ሜዳ የገጠሙኝ አንድ ፍሬ ህጻናት ናቸው። ያውም በሐሺሽ ያበዱ ህጻናት። እናም እንዴት ብዬ ጨክኜ እነዚህ አንድ ፍሬ ህጻናት ላይ ልተኩስ? ጨነቀኝ፣ ጠበበኝ እያለ ነው የሚነግረን።
… በዚህም ምክንያት የማየጨውን፣ የኮረምን፣ የአላማጣና የቆቦን፣ የአዲአርቃይን፣ ጠንካራ ምሽጎች ለቅቆ ሸሽቶ አሁን በወልድያ ዙሪያ መክተሙ እየተነገረ ነው። መከላከያ ለህጻናቱ ማዘኑ፣ መራራቱም፣ መንሰፍሰፉም፣ ሰብዓዊነቱን ያሳያል ብንል እንኳ እሺ መተኮስ ካልፈለገ እንዴት እንደ ታንክ፣ መድፍ እና ዙ23 የመሳሰሉ ከባድ መሣሪያዎችን “ለህጻናቱ” አስረክቦ ወደ ኋላ ይሸሻል። ለህጻናት ታንክ አስረክቦ መሸሹ ምን ይባላል? ህጻናቱ በታንኩ ምን እንዲያደርጉበት አስቦ ነው? ይሄ ምን ዓይነት፣ ምን ይሉትስ “ስልታዊ ማፈግፈግ” ነው የሚባለው ??
… አዲአርቃይ፣ ማይጨው፣ አላማጣ፣ ቆቦም ገብተው ፎቶ ተነስተው ተቆጣጥረነዋል ብለው በየፌስቡኩ ላይ የሚለጥፉት ግን ጎሮምሶች ናቸው። ወጣቶች፣ ጎልማሶች ናቸው። ከታንኩም ጋር፣ ከመድፉም ጋር ኦራሉም ላይ ተጭነው ፎቶ ተነሥተው የሚለጥፉት ግን ወጣቶቹ ናቸው። ህጻናቱ የተባሉት ለመከላከያው ብቻ ነው የሚታዩት ማለት ነው? ስላልገባኝ ነው። ዘንድሮ መከላከያ ባልተለመደ መልኩ አንድም ጋዜጠኛ ወደ ጦር ግንባሩ እንዲሄድ አልፈቀደም። የዐማራ ክልልም እንደዚያው። የዐማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ በአዲአርቃይ መስመር መከላከያው ራሱ አስከብቦአቸው የዐማራ ኃይሎች ከበባውን ሰብረው እንደወጡም እየተናገሩ ነው። መከላከያው አፈግፍጉ፣ አፈግፍጉ ከማለቱም ባሻገር የዐማራ ኃይሎችን በመድፍና በመትረየስ ከጀርባ እየመታቸው መቸገራቸውንም የዐማራ ኃይሎች እየተናገሩም ነው። ይሄ ከባድ ነው። አጅሬው አፈግፍጉ እያለ ለአዲስ አበባ 521 ኪሎ ሜትር በቀረው ስፍራ ላይ እንዲከትሙ አድርጓል። ህጻናቱም ወደ አዲስ አበባ ወደፊት መግፋታቸውን፣ መከላከያውም ወደ ፊኒፊኔ ወደኋላ መገፋቱን፣ ማፈግፈጉንና  መሸሹን አላቆመም።
… በዐማራ ክልል በሚደረገው ውጊያ ስልታዊ ማፈግፈግ የሚጠቀመው የዐቢይ አሕመድ መከላከያ ሠራዊት ይሄንኑ ወደ ኋላ የማፈግፈግ ስልቱን በአፋር ክልል በኩል ለመተግበር ያልፈቀደውስ ለምንድነው? የጅቡቲን መስመር ለመቆጣጠር የተመሙትን የህወሓት ህጻናት ለምንስ አልራራላቸውም? አላዘነላቸውምም? በይልማ መርዳሳ የአየር ኃይል ጄት እና ሂሊኮፕተር ጭምር ነው እኮ የፈጃቸው። ይሄ ታዲያ በዐማራ ክልል ብቻ ከሚከተለው ከላይ ከጠቀስነው ስልታዊ ማፈግፈግ ጋር አይጋጭም ወይ? በአፋር በኩል የጅቡቲን መስመር ለመቆጣጠር የተመሙትን የህወሓት የህጻናትና ወጣት ሴት ተዋጊዎችን የደመሰሰው የዐቢይ መንግሥት በዐማራ በኩል ለሚገቡት ወደኋላ የሚሸሸው ምን አስቦ ነው? ስላልገባኝ ነው?
… በአፋር ግንባር አንድ ፍሬ ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች በመከላከያ ሠራዊቱ ተጨፍጭፈው፣ ተጨፍጭፈው በየተራራው ተረፍርፈው ወድቀው የሚያሳይ ቪድዮ ደርሶኝ አይቻለሁ።
… የድጋፍ ሰልፍ ጦርነቱን አያስቆመውም። ለዘመቻ፣ ለውጊያ የሚሆንም ሰው አልጠፋም። ስንቅ ሳይኖርህ አፈር እየበላህም ልትዋጋ ትችል ይሆናል። 5ፍሬ ጥይት ይዘህም ትንሽ ልትታኮስ ትችላለህ። ለሁሉም ግን አዋጊ፣ መሪ ከሌለህ ግን ተሸናፊ ነህ? መሃል ከተማ ፎቶ እየተነሡ በመለጠፍ ድል የለም። ዐማራ አሁን መሪ ነው ያጣው። ፋኖና የዐማራ ልዩ ኃይል ሲያዩ የሚናደዱ፣ ንዴታቸውን መደበቅ የማይችሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ስታይ ደግሞ ጉዳዩ ሌላ እንደሆነ ትረዳለህ። ያለ ስንቅ፣ ያለ መሪ፣ ከፊት ህወሓትን፣ ከኋላ መከላከያን እየተዋጋህ ለማሸነፍ የመለኮት እርዳታ ብቻ ነው የሚያስፈልገው።
… እነዚያ በሞርታር፣ እነዚህ በቆመህ ጠብቀኝ፣ ለስብሰባ ብለህ ጠርተህ መኪና ላይ የጫንከውን ገበሬ ማግደህ ምን እንደምትጠቀም ነው ያልገባኝ። ህዝብ የሚያዋጣው ገንዘብ 84 ሚልዮን ደርሷል። ፋኖና የዐማራ ልዩ ኃይል ስንቅ ጠይቀው የሚሰጣቸው ቢያጡ ግለሰቦች ይረዷቸው ጀምሯል። የዝናብ ልብስ እንኳ የሚያቀርብላቸው ነው የጠፋው። 84 ሚልዮኑ ብር ባንክ ቁጭ ብሏል። አሁንም እየገባ ነው። ፈራሚው አይታወቅም። ከህዝቡ ላይ ብሩን፣ ከኗሪው ላይ እህሉን ዐሟጠው እየጨረሱት ነው። መከላከያ ሲሸሽ እነዚያ ያራቁቱታል። መከላከያ ባለበት ደግሞ ህዝቡ ላይዋጋለት ሌማቱን ደፍቶ ይቀልበዋል።
… ከጦርነቱ ዐማራና ትግሬ በኪሳራ አፈር ከደቼ እየበሉ ነው። የትግሬም የዐማራም ህዝብ በተለይ ወንድ ወንዱ እየተቀነሰ ነው። በረሃብ፣ በበሽታም እየተቀነሰ ነው። የህዝብ ቅነሳው በተሳካ መንገድ እየሄደ ነው። የትግሬ ሱቆች፣ ድርጅቶችም በሙሉ ተዘግተዋል። በኢኮኖሚ እንዲደቁ ተደርገዋል። ዐማራውም በመዋጮ፣ ትግሬው እየተነጠቀ እንዲደቁ ተደርገዋል። ሴረኛው አድፍጦ ሁለቱንም እያደቀቃቸው ነው። ውቅጥ እንደ ጌሾ። የአንተን መጨረሻህን ብቻ ያሳየኝ።
… ሃገሪቷ እንዲህ በቋፍ ላይ ሆና የሃገሪቷ መሪ ደብዛው የለም። የት እንደገባም አይታወቅም። ችግኝ እየተከለ ፎቶ ተነሥቶ መለጠፉንም ትቶታል። ገራሚ ነው። ህዝቡም መከላከያ አንድ ከተማ ሲገባ ከተማውን ለቅቆ መውጣት ጀምሯል። በመከላከያ ሠራዊቱ ህዝቡ እንዳይተማመን ነው ያደረጉት። ደሴ ላይ መከላከያው ብቻውን እየተንጠራወዘ “አዋጊ አጣን፣ በእግራችን ነው የመጣነው፣ እያለ ከተማ ለከተማ እየዞረ ህዝቡን ሲያሸብረው ስታይ ተልእኮአቸው ከባድ መሆኑን ትረዳለህ። “ጦር ከፈታው፣ ወሬ የፈታው” እንዲሉ ራሱ መንግሥት አስቀድሞ ህዝቡን በወሬ ሲያሸብረው ታያለህ። መንግሥት ተብዬው ዝም ጭጭ።
… አሁን ለህወሓት ከአልውኃ ምላሽን እንዲይዙ ስላደረጋቸው ዐቢይ አሕመድ በቃችሁ የያዛችሁትን ይዛችሁ እንደራደር ሊላቸው ሁሉ ይችላል። መጨረሻው ባይታወቅም ብቻ የሚሆነውን መጠበቅ ነው።
… ይሄ የእኔ ሃሳብ ነው። ደግሞ ስደቡኝ አሏችሁ። ማታ በመረጃ ቲቪ ከአዳዲስ መረጃዎች ጋር እስክንገናኝ ሰላም ዋሉ አምሹልኝ።
Filed in: Amharic